ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ እርጅና ስለ ኢየሱስ የምንመሰክርበት ፍሬያማ ጊዜ መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ነሐምሴ 4/2014 ዓ. ም. በጳውሎስ ስድስተኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለተሰበሰገኙት ምዕመናን ከዮሐ. 14:1-3 ተወስዶ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ሳምንታዊ አስተምህሮአቸውን አቅርበዋል። ከልዩ ልዩ አገራት ለመጡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎብኚዎች ባቀረቡት አስተምህሮ፣ የእርጅና ዘመን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የምንመሰክርበት ፍሬያማ ጊዜ መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ስለ አረጋውያን ሲቀርብ በነበረው አስተምህሮ የመጨረሻው ክፍል ላይ እንገኛለን። በዛሬው አስተምህሮ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ በሰፊው ወደተገለጸው እና ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ ያደረገውን የስንብት ንግግር እንመለከታለን። የስንብት ንግግሩ የሚጀምረው ‘ልባችሁ አይታወክ’ በሚለው የማጽናኛ እና የተስፋ ሐረግ ነው። (ዮሐ 14፡1) ሄጄ ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ፣ እኔ ባለሁበት እንድትኖሩ መጥቼ እወስዳችኋለሁ” (ዮሐ 14፡3)

ይህን ከማለቱ ጥቂት ጊዜ አስቀድሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ለጴጥሮስ እንዲህ አለው፥ ከዚህ በኋላ ስምዖን ጴጥሮስ ኢየሱስን ‘ጌታ ሆይ! ወዴት ነው የምትሄደው?’ ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም ‘እኔ ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፤ በኋላ ግን ትከተለኛለህ’ ሲል መለሰለት። (ዮሐ 13፡36) ይህን በማለት ደካማ የእምነት ጉዞውን አስታወሰው። የደቀ መዛሙርቱ የሕይወት ዘመን፣ በምስክርነት ደካማነት እና በወንድማማችነት ሕይወት ውስጥ ፈተናዎች ያሉበት መሆኑ የማይቀር ነው። ነገር ግን አስደናቂ በሆኑ የእምነት በረከቶች ውስጥ የሚያልፉበትም ጭምር ነው። ‘እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን ሥራ ይሠራል፤ እንዲያውም ከዚህ የበለጠ ይሠራል፤’ (ዮሐ. 14፡12)። እንግዲህ ይህ ምን ዓይነት ቃል ኪዳን እንደሆነ አስቡት! ሙሉ በሙሉ የምናስበው ወይም ሙሉ በሙሉ የምናምነው ከሆነ አላውቅም።

የእርጅና ጊዜ ስሜት ቀስቃሽ እና ከአስደሳች ምስክርነት ጋር የሚስማማ ጊዜ ነው። በእርጅና ወቅት የሚከናወኑ የእምነት ሥራዎች እኛን እና ሌሎችን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚያቀርቡት ከጉልበት፣ ከቃል እና ከወጣትነት ኃይል በላይ ናቸው። በትክክል በዚህ መንገድ የእውነተኛውን የሕይወት መድረሻ ቃል ኪዳንን የበለጠ ግልጽ ያደርጋሉ። ከእግዚአብሔር ጋር በአንድነት በአንድ ቦታ እንድንሆን ያደርጉናል። በቁምስናችን ውስጥም ወደዚህ ልዩ ስፍራ የምንሄድበትን ጊዜ የምንጠባበቅበት፣ የአረጋውያንን እና የማኅበረሰቡን ባህሪያት ለማነቃቃት የታሰበ ልዩ አገልግሎት ያለ ከሆነ የሚያስደስት ነው።

በሕይወት ዘመን የተለያዩ ዕድሎችን ሳይጠቀሙባቸው ካለፉ በራስ እና በሌሎች ላይ ተስፋ የመቁረጥ ስሜትን ይፈጥራል። በየዋህነት እና በእውነተኛ ሕይወት የኖሩት የእርጅና ዘመን ተከብራ የኖረች ቤተ ክርስቲያን ራሷን ከዓለማዊ ሁኔታዎች ጋር በማስማማት፣ ይህን ብታደርግ ወደ ፍጽምና ያደርሳታል ከሚል የተሳሳተ አመለካከት ነጻ ያደርጋል። ራሳችንን ይህን ከመሰለ ግምት ነፃ ስናወጣ፣ እግዚአብሔር የሚሰጠን የእርጅና ጊዜ ኢየሱስ ከተናገራቸው ‘ታላላቅ’ ሥራዎች መካከል አንዱ ይሆናል። በመሠረቱ እነዚህ ታላላቅ ሥራዎች ኢየሱስ ክርስቶስ እራሱ እንዳይፈጽም ከተደረጉት ሥራዎች የሚቆጠሩ ናቸው፥ እነርሱም ሞቱ፣ ከሞት መነሳቱ እና ወደ ሰማይ ማረጉ ናቸው። ይህን በማድረጉ እኛም የሞቱ እና የትንሳኤው ተካፋዮች እንድንሆን አድርጎናል። "ጊዜ ከቦታ ይበልጣል" የሚለውን ሕግ እናስታውስ። ሕይወታችን ምናባዊ በሆነ ምድራዊ ፍጽምና የተገደበ አይደለም። ሞትን ተሻግረን እንድናልፍ ተወስኗል። በእርግጥም ቋሚ መኖሪያችን፣ መድረሻችን በዚህ ምድር አይደለም፣ ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላለም የምንኖርበት ያ ቋሚ መኖሪያችን ነው።

በዚህ ምድር ላይ ስንኖር የእኛ የ ‘አዳጊነት’ ሂደት ይጀምራል። በምድር ላይ ስንኖር በሺህዎች በሚቆጠሩ ችግሮች መካከል እንገናኛለን። በዚህም ምድራዊ ሕይወትን እንለማመዳለን። የእግዚአብሔር ስጦታ ማድነቅን መማር ያስፈልጋል። ስጦታችንን ለሌሎች የማካፈል ሃላፊነታችንን በማክበር፣ ሁሉም ሰው መልካም ፍሬ እንዲያፈራ ማድረግ ያስፈልጋል። በምድር ላይ ያለን ሕይወት የዚህ ልዩ ጸጋ ክፍል ነው። ጊዜ ወደ ፊት እንዳይራመድ የማድረግ እሳቤ፣ ማብቂያ የሌለው የወጣትነት ዕድሜ ምኞት፣ በደህንነት ተደላድሎ መኖር፣ ስልጣን፣ እነዚህን በሙሉ ለማግኘት ማሰብ የማይቻል ብቻ ሳይሆን ሞኝነትም ጭምር ነው።

ምድራዊ ቆይታችን ፍጻሜው ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ የሚገኝበት የሕይወት መጀመሪያችን ጊዜ ነው። እኛ በምድራዊ ሕይወታችን ገና ከጅምሩ አንስቶ ፍጹም አይደለንም፤ እስከ መጨረሻው ድረስም ፍጹም አይደለንም። የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ሲፈጸም ነገሮች በሙሉ ይለወጣሉ፡- ኢየሱስ ክርስቶስ በከፍተኛ ጥንቃቄ ያዘጋጀልን የእግዚአብሔር ሥፍራ ከሟች ሕይወታችን ይበልጣል። ስለዚህም የእርጅና ጊዜያችን ወደዚህ ፍጻሜ የምንቀርብበት የተስፋ ጊዜ ነው። እርጅና የጊዜን ትርጉም እና የምንኖርበትን ቦታ ውስንነት በሚገባ በትክክል ያውቃል። ጊዜ ባለፈ ቁጥር ወይም ዕድሜ በጨመረ ቁጥር ሁሉ ደስ እንዲለን የሚጋብዘን ለዚህ ነው። ይህም ማስፈራሪያ ሳይሆን ቃል ኪዳን ነው።

የእምነትን ጥልቀት እንደገና የሚረዱበት የእርጅና ጊዜ አንዳንዶች እንደሚሉት የተፈጥሮው ሕግ አይደለም። እግዚአብሔር በፈጠረው ዓለም ውስጥ የቦታ ገደብ የለውም። የጊዜ ክብደትም የሚለካ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻው እራት ላይ ለደቀ መዛሙርቱ በተናገረ ጊዜ ወደዚህ ግብ ራሱን ያቀረበው ትክክል ነበር። ‘በአባቴ መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ ጭማቂ ከእናንተ ጋር እስከምጠጣበት ቀን ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ከዚህ የወይን ፍሬ ጭማቂ ዳግመኛ አልጠጣም እላችኋለሁ።’ (ማቴ. 26:29) በስብከታችን ውስጥ፣ ምድረ ገነት ብዙውን ጊዜ በበረከት፣ በብርሃን እና በፍቅር የተሞላች እንደሆነች እንመሰክራለን። ምናልባት ይህ አባባል ትንሽ ሕይወት ይጎድለው ይሆናል። ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌዎቹ ውስጥ የበለጠ ሕይወትን በማስገባት ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ተናግሯል። ይህን ማድረግ እኛስ አንችልም ወይ?

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፤ እግዚአብሔርን ለማየት የምንጠባበቅበት የእርጅና ዘመን፣ ለእያንዳንዳችን የእምነታችን ሙላት የሚገለጥበት እና የተስፋ መሠረት ሊሆነን ይችላል። ‘ጌታ የሆነውን ክርስቶስን በልባችሁ አክብሩት፤ በእናንተ ስላለው ተስፋ ምክንያት ለሚጠይቃችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዝግጁዎች ሁኑ።’ (1ኛ ጴጥ. 3:15) የእርጅና ዘመን የኢየሱስ ክርስቶስን የተስፋ ቃል ግልጽ ያደርገዋል። በዮሐንስ ራዕይ ምዕ. 21-22 ላይ እንደተጻፈው፣ ወደ ከተማይቱ መቅደስ ለመግባት የምንጠባበቅበት ጊዜ ነው። የእርጅና ሕይወት የአዲስ ሕይወት መጀመሪያ፣ የተሻለ ሕይወት እንደሚጠብቀን የምንናገርበት ልዩ የሕይወት ምዕራፍ ነው። ለዚህ የምንበቃበትን ዕድሜ እግዚአብሔር ይስጠን!”

10 August 2022, 16:54