ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በካናዳ የንስሐ ንግደት ባደረጉበት ወቅት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በካናዳ የንስሐ ንግደት ባደረጉበት ወቅት  (Vatican Media) ርዕሰ አንቀጽ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በካናዳ የፈጸሙት የንስሐ ንግደት አባታዊ ቡራኬ እና ስጦታ ነው!

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በካናዳ ወደሚገኙ የቀደምንት ነዋሪዎች ምድር ያደረጉትን የንስሐ ንግደት የሚያሳዩ ምስሎች በርካቶች ናቸው። ምስሎቹ በእውነቱ ብዙ ስቃይ በደረሰባቸው እና ዛሬ በቤተ ክርስቲያኗ አዲስ ገጽታን ባገኙ ሕዝቦች የፈውስ እና ዕርቅ መንገድ ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዛሬው ማኅበረሰብ ውስጥ ልዩ ልዩ እውነታዎችን በቅጽበት ወደ ሁሉም የዓለማችን ክፍሎች ማሰራጨት የሚቻልባቸው፣ እንደ የእጅ ስልክ እና ኮምፒዩተር የመሳሰሉ የማኅበራዊ መገናኛ መሣሪያዎች ተበራክተዋል። በቁጥር በርካታ የሆኑ፣ በሚሊዮኖች፣ እንዲያውም ተጋነነ አይባል እንጂ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ሳያውቁት ተመሳሳይ መረጃዎችን በማኅበራዊ መገናኛ መሣሪያዎች በኩል በቅጽበት ያገኟቸዋል። የተለያዩ ምስሎችን፣ የድምጽ መልዕክቶች በመጋራት አዙሪት ውስጥ የደረሱበትን ሥፍራ ሳያውቁ እንዲሁ የሚጠፉ፣ ሌሎች ደግሞ በመረጃነት ሲታወሱ የሚኖሩ፣ ሌሎችም በተቀባዮቻቸው በልብ ውስጥ የሚቀመጡ ናቸው። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በካናዳ ከሐምሌ 17 - 24/2014 ዓ. ም ድረስ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚገልጹ ምስሎች ወይም ፎቶግራፎች በርካቶች ሲሆኑ፣ ምስሎቹ እንደ መረጃነት ሰፊ የሃሳብ አድማስን በመክፈት፣ ጸጥታን በማስፈን፣ ሕመም እና ስቃይ ከመቀስቀስ ሌላ አጋርነትን የሚፈጥሩ፣ ግንዛቤን የሚያስጨብጡ፣ ኅብረትን የሚፈጥሩ እና ተስፋን የሚሰጡ ናቸው።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እራሳቸው እንደተናገሩት፣ በወቅቱ በካናዳ የነበረው መንግሥት ሕዝቦችን ያለ ፍላጎት በመዋሃድ ፖሊሲው ወላጆች ልጆቻቸውን በግፍ ወደ ተነጥቁበት የሰማዕታት ምድር የንስሐ ንግደትን አድርገዋል። በዚህ የንስሐ ንግደት የክርስቶስን ብርሃን፣ የሰዎችን ስቃይ እና መከራን በቅርብ የምትመለከት፣ እውነትን ሳትፈራ ይቅርታን የምትለምን፣ ያለ ምንም እንቅፋት ሁሉን የምታቅፍ እና የምታዳምጥ ቤተ ክርስቲያንን ወደ ሥፍራው ይዘው ሄደዋል።

ቅዱስነታቸው በካናዳ በቆዩባቸው ስድስት ቀናት ውስጥ ሩቅ የአገሪቱ አካባቢዎች ተጉዘው ከፍተኛ ቁጥር ያለው  የቀደምት ማኅበረሰብ የሚገኙበት የኢኑይት ክፍለ ሀገርን ጎብኝተዋል። በዚህ አካባቢ በካናዳ ውስጥ ከተመሠረቱ አራት የአንደኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤቶች መካከል በአንዱ ውስጥ ትምህርታቸውን ተከታትለው የነበሩ የቀድሞ ተማሪዎችን ለማግኘት ችለዋል። ትምህርት ቤቶቹ ከወላጆቻቸው በግድ ተነጥቀው የተወሰዱ ልጆችን ለማስተማር የተቆረቆሩ አስፈሪ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ነበሩ። ቅዱስነታቸው ይህን አዳሪ ትምህርት ቤት በአካል ተገኝተው በተገበኙበት ወቅት የተመለከቱት ነገር ቢኖር፣ ጠባብ ቀዳዳ የተሰራላቸው፣ በነጭ ቀለም የተቀቡ ትላልቅ ሣጥኖችን ነበር።

የካናዳ ቀደምት ሕዝብ የደረሰበትን ስቃይ በልቅሶ ሲገልጽ
የካናዳ ቀደምት ሕዝብ የደረሰበትን ስቃይ በልቅሶ ሲገልጽ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከእነዚያ ትላልቅ ሳጥኖች መካከል ወደ አንዱ ውስጥ ሲገቡ የተቀበሏቸው ሰልፍ ላይ የነበሩ፣ የባሕል ልብሳቸውን የለበሱ በአብዛኛው አዛውንቶች ነበሩ። ቅዱስነታቸው የተቀበሉት በሐዘን ልብ፣ ፊቶቻቸውን ሸፍነው በእንባ ነበር። ይህን የመሰለ አቀባበል ቅዱሰነታቸው በካናዳ ውስጥ በጎበኟቸው ካባቢዎች ሁሉ ተደጋግሞ ይታይ ነበር። በጎበኙባቸው አካባቢዎች ሁሉ ሰዎች ከዓመታት በፊት ያሳለፉትን የመከራ ሕይወት እያስታወሱ ብሶታቸውን በለቅሶ ይገልጹላቸው ነበር። በወቅቱ በነበረው አዳሪ ትምህርት ቤቶች ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ አንዳንድ ካቶሊካዊ ምዕመናን ያደረሱትን በደል የሚያስታውሱት ሰዎች ቅዱስነታቸውን በመንደራቸው በተቀበሏቸው ጊዜ ከማልቀስ ሌላ ቅዱስነታቸው የተሰማቸውን ሐዘን እና ጸጸት ከመገንዘብ በተጨማሪ ለእርሳቸው ያላቸውን ልባዊ ፍቅር እና ክብር በመተቃቀፍ ሲገልጹ ታይተዋል። የሚፈሱ እንባዎች ያለፉትን ስቃዮች የሚገልጹ ቢሆንም በስፋት የተዘረጉ እጆች የመልካም አቀባበል ምልክት ከመግለጽ በተጨማሪ ወደ ፊት የሚጠብቃቸውን የወንድማማችነት እና የእህትማማችነት ተስፋንም የሚገልጹ ነበሩ።  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ ካናዳ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የእርቅና የፈውስ መንገድ መሆኑን በግልጽ አሳይተዋል። ከጥቂት ወራት በፊት በቫቲካን ለተቀበሏቸው፣ ኢንዊት እና ሜቲስ ተብለው ለሚታወቁ የካናዳ ቀደምት ብሔረሰቦች የእርቅ እና የፈውስ መንገድን አሳይተዋቸው ነበር። ወደ እዚህ የእርቅ እና የፈውስ ጎዳና ለመድረስ የሚያስችል የፍትሕ ሂደት እንዲጀመር በማለት ሁኔታዎችንም አመቻችተዋል።

ይህን በማስታወስ ንግግር ያደረጉት የአገሩ ቀደምት ነዋሪዎች ዋና ተጠሪ ክቡር አቶ ዊልተን ሊትልቻይልድ፣ ቅዱስነታቸው በካናዳ ምድር ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው "በረከት እና ስጦታ" ነበር በማለት አፅንዖት ሰጥተው "ሥራው መጀመሩንም" አብስረዋል። የብሔረሰቦቹ ዋና ተጠሪ የሆኑት ክቡር አቶ ዊልተን በካናዳ ውስጥ ከተቋቋሙ አዳሪ ትምህርት ቤቶች መካከል በአንድ ውስጥ የነበሩ መሆናቸው ታውቋል። ዛሬ የ70 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት አቶ ዊልተን ለቅዱስነታቸው ባሕላዊ ባርኔጣን በስጦታ አበርክተውላቸዋል።

ር. ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በካናዳ ባደረጉት የንስሐ ንግደት ወቅት ልብን የሚነኩ ፎቶ ግራፎችን ተነስተዋል። ከአልባሳት መካከል ባሕላዊ ባርኔጣን አጥልቀው የታዩበት ምስል አንዱ ነው። ይህም የሕዝቡ ባሕል ለመጋራት ያላቸውን ፍላጎት የገለጹበት ብቻ ሳይሆን ባሕላቸውን ለማወቅ የሚያደርጉትን ጥረት የገለጹበት እንደነበርም ተመልክቷል። ከዚህም በተጨማሪ ለሕዝቡ ባሕል እውቅና መስጠትንም ያካትታል። የብሔረሰቡ ዋና ተጠሪ የሆኑት ክቡር አቶ ዊልተን በዕድሜ ምክንያት ከዚህ በፊት በድጋፍ የሚንቀሳቀሱ ቢሆንም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተቀመጡበት ቦታ ለመድረስ ደረጃውን ብቻቸውን ለመውጣት ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባሰሙት ንግግር፣ የካናዳ ቀደምት ነዋሪዎች ልባቸውን እና ጆሯቸውን ለወንጌል ዳግመኛ በመክፈት፣ የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን እውነታ ቀድሞ ከነበረችበት በእጅጉ የተለየች ሕያው ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች መረዳታቸውን በይፋ ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው ባሕላዊ ስጦታዎች ተበርክተውላቸዋል
ቅዱስነታቸው ባሕላዊ ስጦታዎች ተበርክተውላቸዋል

ለቅዱስነታቸው ከቀረበላቸው ስጦታዎች መካከል አንዱ፣ በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ውስጥ መከራ ያጋጠማቸው ተማሪዎች ስም በዝርዝር የተጻፈበት ጨርቅ እንደነበር ተመልክቷል። ይህ ልዩ ስጦታ ለቅዱስነታቸው ሲቀርብ በሥፍራው የተገኙት ሰዎች ልባቸው በሐዘን ውስጥ ሆኖ የአገሪቱን ብሔራዊ መዝሙር ሲዘምሩ ተደምጠዋል። ይህ ሥነ ሥርዓት ከተከናወነ በኋላ ቅዱስነታቸው በተዘጋጀላቸው የመጓጓዣ ወንበር ተቀምጠው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የአገሩ ተወላጆች በየዓመቱ መንፈሳዊ ንግደት ወደ ሚያደርጉበት የቅድስት ሐና መቅደስ ሲደርሱ ከአዛውንት እና ወጣቶች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በካናዳ ያደረጉትን የንስሐ ንግደትን የሚያመላክቱ ምስሎችን በምናስታውስበት ጊዜ፣ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ያለፈውን ስቃይ የሚያስታውስ፣ ስሜትን የሚቀሰቅስ፣ ማንነትን የሚገልጽ፣ የውስጥ ስሜትን በመዝሙር፣ በጽሞና፣ በጸሎት እና በለቅሶ እንድንገልጽ የሚጋብዝ ሲሆን፣ ከዚህ የንስሐ ጉዞ ጋር ተያይዞ አዲስ እይታን የሚጀምር፣ ግለሰቦች እና ተቋማት ሊያከናውኑ ለተዘጋጁበት ተግባራት ግቦችንም ያስቀመጠ፣ የአንዱ እግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን የምንገነዘብ በሙሉ የወንድማማችነትን መንገዶች እንድንከተል፣ እርስ በእርስ በመደማመጥ እና ያለንን ከሌሎች ጋር በመጋራ እይታችንን ወደ ሰው ልጆች እና ወደ ፍጥረት እንድንመልስ የሚጋብዙ መሆናቸውን ተመልክተናል በማለት ርዕሠ አንቀጹ መልዕክቱን ደምድሟል።       

04 August 2022, 16:30