ፈልግ

በኩባ የነዳጅ ማከማቻ መጋዝን ላይ የደረሰ የእሳት ቃጠሎ አደጋ በኩባ የነዳጅ ማከማቻ መጋዝን ላይ የደረሰ የእሳት ቃጠሎ አደጋ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በኩባ ነዳጅ ማከማቻ መጋዘን ቃጠሎ የተጎዱትን በጸሎታቸው አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ካቀረቡት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው በመቀጠል በኩባ ውስጥ በማታንዛስ የነዳጅ ማከማቻ መጋዝን ላይ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ የተጎዱትን በሙሉ በጸሎታቸው አስታውሰዋል። እጅግ ከባድ በተባለው በዚህ አደጋ ቢያንስ አንድ ሰው መሞቱ፣ 14 ሰዎች መጥፋታቸው፣ ሌሎ አምስት ሰዎች በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል። ቅዱስነታቸው የአደጋው ሰለባ ከሆኑት ሰዎች በተጨማሪ ቤተሰቦቻቸውንም በጸሎታቸው አስታውሰዋል። የአደጋው ሰለባዎችን በማስታወስ ባቀረቡት ጸሎት፣ የሰማይ ንግሥት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአደጋው ተጎጂዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን እንድትጠብቅ በማለት ተማጽነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"በኩባ ታሪክ እጅግ የከፋ የእሳት ቃጠሎ ነው"

አርብ ምሽት የተነሳው የማታንዛስ የነዳጅ ማከማቻ መጋዘን ቃጠሎ በኩባ ታሪክ ውስጥ እጅግ ከፍተኛ እንደነበር ተገልጿል። የአደጋው ምክንያት በነዳጅ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ላይ በወደቀው መብረቅ እንደሆነ ታውቋል።

እሳቱ ቅዳሜ እለትም ወደ ሁለተኛው የነዳጅ ማጠራቀሚያ በመዛመት ተጨማሪ ፍንዳታዎችን ካስከተለ በኋላ በቁጥጥር መዋሉ ታውቋል። በዚህ የቃጠሎ 40% በላይ የሚሆነው የኩባ ደሴት ዋና የነዳጅ ማከማቻ ተቋም መውደሙ ሲነገር፣ በብዙ የአገሪቱ ክፍሎች የመብራት አገልግሎት መቋረጡ ተመልክቷል። የእሳት አደጋ ተከላካዮች ማክሰኞ ዕለት ከ 100 በላይ የሜክሲኮ እና የቬንዙዌላ የእሳት አደጋ ተከላካዮች፣ ሄሊኮፕተሮች እና የእሳት አደጋ ጀልባዎች በመታገዝ እሳቱን ለመቆጣጠር መቻላቸው ተነግሯ።

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ምላሽ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሰኞ ነሐሴ 2/2014 ዓ. ም. በቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ በሆኑት በብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን አማካይነት ለኩባ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ለብጹዕ አቡነ ኤሚሊዮ አራንጉረን የቴሌግራም መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው አደጋውን በማስታወስ ለኩባ ሕዝብ ያላቸውን መንፈሳዊ ቅርበት ገልጸው በአደጋው የተጎዱትን ቤተሰቦች በጸሎታቸው እንደሚያስታውሱ መግለጻቸው ይታወሳል። በዚህ የሕመም ጊዜ እሳቱን ለማጥፋት እና የጠፉትን በመፈለግ ላይ ለሚገኙት የእግዚአብሔርን እርዳታ መለመናቸው ይታወሳል። የአደጋው ሰለባ ቤተሰቦችን በጸሎታቸው አስታውሰው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሳኤው የተስፋ ቃል መጽናናትን እንዲሰጣቸው በመለመን ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን መላካቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬ ዕለታ ያቀረቡትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮን ከማጠቃለላቸው በፊት በዩክሬን እና ሩስያ መካከል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በድጋሚ አስታውሰው ምዕመናኑ ቤታቸውን ለቀው የሚሰደዱትን በሙሉ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል።

10 August 2022, 17:01