ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የንግድ ድርጅቶችን በጸሎት ማስታወስ እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ወርሃዊ የጸሎት ሐሳባቸውን ለካቶሊካዊ ምዕመናን በሙሉ ይፋ አድረገዋል። በነሐሴ ወር ውስጥ በጸሎት እንዲተባበሯቸው ባሳሰቡን የጸሎት ሃሳባቸው፣ አነስተኛ የንግድ ድርጅቶችን በጸሎታችን እንድናስታውሳቸው አደራ ብለውናል። ቅዱስነታቸው በማሳሰቢያቸው በአነስተኛ እና መለስተኛ የንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ድርጅቶች ዛሬ በምንገኝበት ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ ጥረታቸውን ሳያቋርጡ ለዕለታዊ ሕይወት የሚያስፈልጉ የፍጆታ ምርቶችን ለማኅበረሰቦቻቸው ማቅረብ እንዲችሉ በጸሎት ልናግዛቸው ይገባል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአነስተኛ እና መለስተኛ የንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙት ሰዎች የሚያደርጉትን ጥረት፣ ያላቸውን ብርታት እና የሚከፍሉትን መስዋዕትነት የተገነዘቡት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ይህ የሥራ ዘርፍ ጦርነቶች እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውሶች ምክንያት ክፉኛ የተጎዱ መሆናቸውንም አስረድተዋል። እ. አ. አ. የ 2021 ዓ. ም. የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከአራት የንግድ ተቋማት መካከል አንዱ ዓለማችንን ክፉኛ ባጠቃው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ግማሽ የሽያጭ መጠን ማጣቱን አስታውቋል። እውነታውን ይበልጥ የሚያባብሰው ደግሞ በቂ የሕዝብ ዕርዳታን ካለማግኘት የተነሳ መሆኑንም አክሎ አስታውቋል።

የንግድ ተቋማቱን ለማገዝ ዘላቂ መስዋዕትነት እና ትጋት ሊኖር ይገባል

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በነሐሴ ወር የጸሎት ሃሳባቸው፣ በንግድ ድርጅቶቻቸው እና የገበያ ማዕከላት ውስጥ ለሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድልን በመክፈት ሕይወታቸውን በሰላም እንዲመሩ ላደረጉት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የንግድ ተቋማቱ የማያቋርጥ ጥረት እና ትጋት ለማኅበራዊ ጥቅም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ መሆኑንም ገልጸዋል።

የዕቃ ማከማቻ መጋዝኖች፣ የጽዳት ሥራዎች፣ የመጓጓዣ አገልግሎቶች እና ሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ማኅበራዊ ጥቅምን ለማሳደግ እንደሚረዱ፣ ከሰፋፊ የንግድ ተቋማት ሌላ ጎልተው የማይታዩ ጥቃቅን የንግድ ድርጅቶች፣ በዚህ አስቸጋሪ ወቅትም ለሰዎች የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ማኅበራዊ ሃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ እንደሚገኙ ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለነሐሴ ወር እንዲሆን ብለው ባቀረቡት የጸሎት ሃሳብ፣ አነስተኛ እና መካከለኛ የንግድ ድርጅቶች ለማኅበረሰብ የሚያበረክቱትን ድጋፍ በማስታወስ፣ በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ ቀውስ የተጎዱትን አነስተኛ እና መካከለኛ የንግድ ድርጅቶችን በጸሎታችን እንድናግዛቸው አደራ ብለው፣ ለማኅበረሰባቸው የሚያቀርቡት አገልግሎቶች ዘላቂ እንዲሆን ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል።

የአነስተኛ ንግድ ድርጅቶች ጠቀሜታ

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ በበኩላቸው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እንደገለጹት ሁሉ፣ ያጋጠሙን ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውሶች ከባድ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ቀውሱ ከችግር መውጣት የሚቻልበትን አዲስ ዘዴን ለማግኘት ዕድል የሚሰጥ ነው ብለው፣ ከዚህ አንፃር፣ አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ድርጅቶች የፈጠራ አቅማቸውን በማሳደግ እና የመፍትሄ ሃሳቦችን በማቅረብ ደሃውን ማኅበረሰብ ከችግር ለማውጣት ያላቸው ጥቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።  ያለ እነዚህ የንግድ ድርጅቶች ዘላቂ ጥረት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቀውስን መሻገር የማይቻል እንደሆነ የተናገሩት ክቡር አባ ፍሬደሪክ፣ እነዚህን ድርጅቶች በጸሎታችን ማገዝ ያስፈለገበት ምክንያት ይህ መሆኑን አስረድተዋል።

የር. ሊ. ጳ ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ እና የቪዲዮ መልዕክት

የር. ሊ. ጳ ዓለም አቀፍ የጸሎት አውታረ መረብ ከቫቲካን ፋውንዴሽን ድርጅቶች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ዓላማው የሰውን ልጆች ለሚያጋትሙ ተግዳሮቶች እና ለቤተክርስቲያን ተልዕኮ ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል በመላው ዓለም የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናንን በጸሎት እና በተግባር የማሰባሰብ ተልዕኮ ያለው መሆኑ ይታወቃል። በ 1836 ዓ. ም. የተቋቋመው የር. ሊ. ጳ ዓለም አቀፍ የጸሎት አውታረ መረብ በአሁኑ ጊዜ በ 89 አገሮች ውስጥ የሚገኝ እና ከ 22 ሚሊዮን በላይ ካቶሊካዊ ምዕመናንን ያቀፈ መሆኑ ታውቋል። ወርሃዊ የቪዲዮ መልዕክቱ የቅዱስነታቸውን የጸሎት ሃሳቦችን ወደ መላው ዓለም የማሰራጨት ዓላማ ያለው ኦፊሴላዊ ዓለም አቀፍ ተነሳሽነት ያለው መሆኑ ይታወቃል።

06 August 2022, 16:28