ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለአርጄንቲና የወንጌል ልኡካኑ መልዕክት በላኩበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለአርጄንቲና የወንጌል ልኡካኑ መልዕክት በላኩበት ወቅት 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “የወንጌል ተልዕኮ የእግዚአብሔር ስጦታን ለሌሎች ማድረስ ነው” አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በአርጄንቲና በሚገኙ ቀደምት ነዋሪዎች መካከል ወንጌልን ለመስበክ የተጓዙ የቁምስና ሚሲዮናዊ ቡድን የማበረታቻ መልዕክት ልከዋል። ቅዱስነታቸው ነሐሴ 4/2014 ዓ. ም. ለአርጄንቲና የወንጌል ልኡካኑ በላኩት መልዕክት "ለወንጌል ተልዕኮ መሄድ" ማለት ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን ስጦታዎች ለሌሎች ማድረስ ማለት እንደሆነ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአርጄንቲና ከሚገኝ የሪዮ ኳርቶ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቁምስና ተነስተው ቀደምት ነዋሪዎች ወደሚገኙባቸው አካባቢዎች ለሄዱት ወጣቶች እና ጎልማሳ የወንጌል መልዕክተኞች ከሰላምታ ጋር የማበረታቻ መልዕክት ልከዋል። የቀደምት ተወላጆቹ የሚኖሩት ሳልታ እና ቪክቶሪያ ኤስቴ በተባሉ የኦራን ሀገረ ስብከት ውስጥ መሆኑ ታውቋል። “ህልሞች እውን የሚሆኑት በኅብረት በመሥራት ነው” የሚል መሪ ሃሳብ በመያዝ የተነሱት የወንጌል ልኡካን በቁጥር ሰላሳ ሲሆኑ፣ በማኅበረሰቦቹ መካከል በሚያደርጉት የአንድ ሳምንት ቆይታ ቤተሰቦችን ማስተማር፣ በጋራ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን በመሳተፍ የእግዚአብሔርን ቃል ለተወላጆቹ እንደሚያካፍሉ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ነሐሴ 4/2014 ዓ. ም. ልኡካኑ በላኩት የቪዲዮ መልዕክት  ለሚያበረክቱት አገልግሎት ምስጋናቸውን ቅርበው ተልዕኳቸውን እንዲቀጥሉ አደራ ብለዋል።

የአርጄንቲና የወንጌል ልኡካን
የአርጄንቲና የወንጌል ልኡካን

"የወንጌል ተልዕኮ" ያስደስታል!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “በወንጌል ተልዕኮ መሰማራት” ማለት ሌሎችንም የሚጠቅም እና ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን ስጦታ ለሌሎች ለማካፈል ራስን መስጠት ማለት እንደሆነ አስረድተው፣ ይህም በሕይወት ደስታን የሚሰጥ መልካም የአገልግሎት ተግባር መሆኑን አስረድተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለልኡካኑ በላኩት መልዕክት ልኡካኑን ለመሩርት የቁምስና መሪ ካህን ክቡር አባ ማሪያኖ ኮርዴሮ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ል ኡካኑ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው ጠይቀው ለልኡካኑ በሙሉ የእግዚአብሔርን በረከት ከለመኑላቸው በኋላ በሚሲዮናዊ አገልግሎታቸው ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

ልኡካኑ በወንጌል ተልዕኮ ወቅት
ልኡካኑ በወንጌል ተልዕኮ ወቅት

“ህልሞች እውን የሚሆኑት በኅብረት ሲሰሩ ነው!”

የተልዕኮው መሪ ቃል የመነጨው “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” ከሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን እንደሆነ ያስረዱት ክቡር አባ ማርያኖ ኮርዴሮ፣ የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎታቸውን በማኅበረሰቦች መካከል ለሦስት ዓመታት ያህል ሲያበረክቱ መቆየታቸውን ገልጸው ዓላማው ከሀገረ ስብከቱ ቀደምት ተወላጆች ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ለማሳደግ በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚጎበኟቸው ተናግረዋል።  ማኅበረሰቦቹ በቦሊቪያ እና በፓራጓይ ድንበሮች አካባቢ እንደሚኖሩ ገልጸው ወደ ስፍራው ለመድረስ ከ5,000 ኪሎ ሜትር በላይ መጓዛቸውን አስረድተዋል። በተራራማ አካባቢዎች በሚኖሩት ማኅበረሰቦች ውስጥ ያለውን ሁኔታን ሲገልጹ በርካቶች የምግብ እጥረት፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረት እና ከማንኛውም ዓይነት የሕክምና አገልግሎት የራቁ መሆናቸውን ክቡር አባ ማርያኖ አስረድተዋል። "ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የሆኑት የአርጄንቲና ቀደምት ተወላጆችን በሰብዓዊ ዓይን የሚመለከታቸው ክፍል አለመኖሩ እጅግ ያሳዝናል" ያሉት ክቡር አባ ማርያኖ፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ድሃ ማኅበረሰብ መካከል አንዱ እና በሁሉ ረገድ ተረስተው የቆዩ መሆናቸውን አክለው አስታውሰዋል።

አባ ማርያኖ በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ወቅት
አባ ማርያኖ በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ወቅት

ለቀደምት ተወላጆች የወንጌል ተልዕኮ ማድረስ

ክቡር አባ ማርያኖ የሚስዮናዊነት ተሞክሮ በተራራማ አካባቢዎች ከሚኖሩ ማኅበረሰቦች ባሕል ጋር ለመተዋወቅ ያገዘ፣ በድህነት ሕይወት የሚገኙት ሰዎች እራሳቸውን እንዲያበለጽጉ ዕድል የሚሰጣቸው መሆኑንም ተናግረዋል። በአካባቢው ማኅበረሰብ ውስጥ ባበረከቱት የወንጌል ተልዕኮ አማካይነት ኢየሱስ ክርስቶስን ለማየት መቻላቸውን ገልጸው፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ የተመለከቱት አስከፊው የድህነት ሕይወት የሚጎዳ እና አቅመ ቢስነትን እንዲረዱ ያደረጋቸው መሆኑን ክቡር አባ ማርያኖ ተናግረዋል።

ማኅበረሰቡ ከሚያሳየው ፈገግታ አማካይነት "ኢየሱስ ክርስቶስን መመልከት ችለናል” ያሉት ክቡር አባ ማርያኖ፣ ተስፋን በተሞላ መግለጫቸው እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደማይተው፣ በተራራማ አካባቢዎች በሚኖሩ ቀደምት ተወላጆች ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ ቀላል እና ምስጢራዊ በሆነ መንገድ በእርግጥ መኖሩን የወንጌል ልኡካኑ ያስተዋሉ መሆኑን ክቡር አባ ማርያኖ አስረድተዋል። በወንጌል ተልዕኮ ላይ የተሳተፉት ወጣቶች በተስፋ ተሞልተው መመለሳቸው የገለጹት ክቡር አባ ማርያኖ፣  በዚህ ተነሳስተው ወንድሞቻቸውን፣ እህቶቻቸውን እና ጎረቤቶቻቸውን ለማስተማር እግዚአብሔር እንደሚቀሰቅሳቸው አስረድተዋል።

የወንጌል ተልዕኮ ተካፋዮች ለአካባቢው ድሃ ቤተሰብ ያላቸውን አጋርነት ሲገልጹ
የወንጌል ተልዕኮ ተካፋዮች ለአካባቢው ድሃ ቤተሰብ ያላቸውን አጋርነት ሲገልጹ
11 August 2022, 16:51