ፈልግ

የምግብ እህል የጫነ የመጀመሪያው መርከብ ከዩክሬይን ወደብ ሲነሳ የሚያሳይ ምስል የምግብ እህል የጫነ የመጀመሪያው መርከብ ከዩክሬይን ወደብ ሲነሳ የሚያሳይ ምስል 

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የዩክሬን የእህል ስምምነት የሰላም ተስፋ ምልክት አድርገው አደነቁ!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የምግብ እህል የጫኑ መርከቦች ከዩክሬን ወደቦች እንዲወጡ በመፈቀዱ የተሰማቸውን እርካታ ገልጸው ስምምነቱ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም እንዲኖር የተስፋ ምልክት ይሰጣል ብለዋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

"ከዩክሬን ወደቦች ለመጀመሪያ ጊዜ እህል የጫኑ መርከቦችን ሲነሱ በደስታ መቀበል እፈልጋለሁ" ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህንን የተናገሩት ደግሞ በእለተ ሰንበት በተካሄደው የመልአከ ሰላም ጸሎት ላይ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ይህንን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስምምነቱ ወደ ሰላም የሚወስደውን መንገድ ያሳያል ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን "ይህ እርምጃ ውይይት ማድረግ እና ተጨባጭ ውጤቶችን ማምጣት እንደሚቻል ያሳያል፣ ይህም ሁሉንም ሰው ይጠቅማል። ስለዚህ ይህ ክስተት የተስፋ ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፤ ይህንን መንገድ በመከተል ትግሉን አቁመን ፍትሃዊና ዘላቂ ሰላም ላይ መድረስ እንደምንችል ከልቤ እመኛለሁ” ማለታቸው ተገልጿል።

የእገዳው ፍጻሜ

ቱርክ እና የተባበሩት መንግስታት የዩክሬን ምግብ በጥቁር ባህር በኩል ወደ ውጭ ለመላክ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል በሐምሌ ወር ላይ ስምምነት አድርገዋል።

በስምምነቱ ለወራት የዘለቀው የዩክሬን ወደቦች እገዳ አብቅቷል፣ ይህም በዓለም ዙሪያ የእህል ዋጋ መናር አስከትሏል።

የዩክሬን እህል ጭነት ባለመኖሩ በተለያዩ ቦታዎች የረሃብ ወረርሽኝ ሊከሰት እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስጠንቅቋል።

ከጦርነቱ በፊት ዩክሬን እና ሩሲያ አንድ ሦስተኛ የሚጠጋውን የዓለም አቀፍ የስንዴ ምርት ወደ ውጪ አገር ልከዋል።

የጋራ ቁጥጥር ጥረቶች

የኢስታንቡል የጋራ ማስተባበሪያ ማዕከል (ጄሲሲ) የተቋቋመው የዩክሬን እህል ጭነትን የሚቆጣጠር ሲሆን በሩሲያ፣ ዩክሬን፣ ቱርክ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞች የሚሰሩበት ማዕከል ነው።

የዩክሬን የባህር ወደቦች ባለስልጣን እንዳስታወቀው እሁድ እለት ወደብ የለቀቁት አራቱ የጅምላ እቃዎች አጓጓዢ መርከቦች ወደ 170,000 ቶን የሚጠጋ በቆሎ እና ሌሎች የምግብ እቃዎችን ይዘው ነበር ጉዞዋቸውን የጀመሩት።

በየካቲት ወር ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የሌላ የውጪ አገር ባንዲራ የሚያውለበልብ መርከብ እህል ለመጫን ወደ ዩክሬን የገባ የመጀመሪያ ጊዜ ቅዳሜ  ሐምሌ 30/2014 ዓ.ም ነው።

የዩክሬን የመሠረተ ልማት ሚኒስትር እሁድ ነሐሴ 01/2014 ዓ.ም እንደተናገሩት ሀገሪቱ በቅርቡ በየወሩ ወደ 3 ሚሊዮን ቶን ዕቃዎችን መላክ እንደምትችል ተስፋ እንዳላት ተናግረዋል ።

የዩክሬን የመሠረተ ልማት ሚኒስትር የሆኑት ኦሌክሳንደር ኩብራኮቭ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልእክት "ቀስ በቀስ ወደ ትላልቅ ስራዎች እንሸጋገራለን" ያሉ ሲሆን  "ወደቦች በወር ቢያንስ 100 መርከቦችን የማስተናገድ አቅምን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማረጋገጥ አቅደናል" በማለት አክለው ገልጸዋል።

07 August 2022, 13:36