ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንቶኒን በቫቲካን ተቀብለው አነጋግረዋል ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንቶኒን በቫቲካን ተቀብለው አነጋግረዋል  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንቶኒን በቫቲካን ተቀብለው አነጋገሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሩስያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የቮሎኮልምስክ ከተማ ሊቀ ጳጳስ እና በሞስኮ ፓትርያርክ ጽ/ቤት የውጭ ግንኙነት ጽ/ቤት ኃላፊ ሆነው የተመረጡትን ብጹዕ አቡነ አንቶኒን በቫቲካን ተቀብለው አነጋግረዋል። ብጹዕ አቡነ አንቶኒ በሩስያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የቮሎኮልምስክ ከተማ ሊቀ ጳጳስ እና በሞስኮ ፓትርያርክ ጽ/ቤት የውጭ ግንኙነት ጽ/ቤት ኃላፊ ሆነው ያገለገሉትን ብጹዕ አቡነ ሂላሪዮንን በመተካት ከሰኔ ወር 2014 ዓ. ም. ጀምሮ ቤተ ክርስቲያናቸውን በማገልገል ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሩስያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንቶኒ በቤተ ክርስቲያኒቱ የውጭ ግንኙነት ጽ/ቤት ሃላፊ ሆነው ከተመደቡበት ከሰኔ ወር ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ቫቲካንን መጎብኘታቸው ታውቋል። በሞስኮ የመንበረ ፓትርያርክ የውጭ ግንኙነት ጽ/ቤት ሃላፊ እና በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መካከል የተካሄደው ያሁኑ ውይይት፣ በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እና በሞስኮ ፓትርያርክ በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ኪሪል መካከል የተጀመረው የአብያተ ክርስቲያናት አንድነት ውይይት አካል ሲሆን፣ ባለፈው መጋቢት 7/2014 ዓ. ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በሞስኮ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ መካከል የተደረገ ውይይት ቀጣይ ክፍል መሆኑ ታውቋል።

ሁለቱ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ባለፈው መጋቢት ወር ላይ የቪዲዮ ኮንፈረንስ ባደረጉበት ወቅት ብጹዕ አቡነ አንቶኒ ከብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ኪሪል ጋር እንደነበሩ ተመልክቷል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሞስኮ ፓትርያርክ እና ለመላው የሩሲያ ሕዝብ ያላቸውን እምነት በመግለጽ ባስተላለፉት መልዕክት በዩክሬን በመካሄድ ላይ ያለውን ጦርነት በተመለከተ የክርስቲያኖች እና ሐዋርያዊ አባቶቻቸው ግዴታ “ሰላምን ለማውረድ የሚቻላቸውን ሁሉ ማድረግ ነው” በማለት ያላቸውን እምነት መግለጻቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በማከልም ጦርነት ባስከተለው ስቃይ ውስጥ የሚገኙትን መርዳት እና ጦርነቱንም ማስቆም እንደሚገባ አሳስበው በጦርነቱ ወቅት ከፍተኛ የሕይወት መስዋዕትነት የሚከፍሉት የሰው ልጆች መሆናቸውን ማስረዳታቸው ይታወሳል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መጋቢት 7/2014 ዓ. ም. ከሞስኮ ፓትርያርክ ከብጹዕ ወቅዱስ ኪሪል ጋር ካደረጉት የቪዲዮ ውይይታቸው በኋላ በምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የቀን አቆጣጠር መሠረት የብርሃነ ትንሳኤ በዓላቸውን ሚያዚያ 17/2014 ዓ. ም. ያከበሩትን የካቶሊክ እና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት ምዕመና በማስታወስ ለፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ኪሪል የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት መላካቸውም ይታወሳል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በዚህ መልዕክታቸው “መንፈስ ቅዱስ ልባችንን በመለወጥ እውነተኛ የሰላም ፈጣሪዎች ያድርገን” ብለው፣ በተለይም በጦርነት ለምትሰቃይ ዩክሬን ሰላም እንዲወርድ፣ በአመፅ፣ በጦርነት እና በፍትሕ እጦት የሚሰቃዩ የሰው ልጆች ከባድ መከራ እንደሚሰማቸው መግለጻቸው ይታወሳል።

06 August 2022, 16:39