ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ በሰሜን ኮሪያ ወንድማማችነትን ለመመስከር ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ሰላም ዘወትር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ስጦታ ነው!
በሕዝቦች ዘንድ ወንድማማችነት ከሌለ ጦርንርት ይከሰታል ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነትን፣ መቀራረብን፣ ደስታን እና እርስ በእርስ መቀራረብን ለመፍጠር እያንዳንዳችን መተባበር ያስፈልጋል ብለዋል። አለመታደል ሆኖ በሳለፍናቸው መቶ ዓመታት ውስጥ ሦስተኛው “የዓለም ጦርነት” እያጋጠመን መሆኑን ገልጸው፣ ለጦር መሣሪያ ምርት የሚመደበው የአንድ ዓመት ገንዘብ ረሃብን ከዓለማችን ለማስወገድ እንደሚችል፣ የሕጻናትን የትምህርት እጥረት ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል አስረድተዋል። ዓለማችን ጦርነት ውስጥ እንደሆነች የገለጹ ቅዱስነታቸው፣ በሶርያ እና በየመን ውስጥ ተረስተው የቆዩ ግጭቶችን በማስታወስ፣ ለሰላም መሥራትን ማቆም እንደሌለበት፣ ለሰላም መሥራት ስጦታ እና የብፅዕና ጥሪ መሆኑንም እስረድተዋል።
የእስያ አህጉር ካህናት እና ወጣቶች
በዚህ ረገድ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ኮሪያውያን ካኅናት ሃይማኖታዊ ድጋፍ በሚያስፈልግባቸው አካባቢዎች በመሄድ የሰላም ፈጣሪዎች እንዲሆኑ ግብዣቸውን አቅርበውላቸዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቃለ ምልልሳቸው ወቅት ፣ በቅድስት መንበር የቤተ ክኅነት ጉዳዮችን የሚከታተል ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት መሪ የሆኑት እና አዲስ የካርዲናልነት ማዕረግ የተቀበሉት ብጹዕ ጳጳስ አቡነ አልዓዛር ዩ ሄንግ-ሲክ ለካኅናቱ ትልቅ ቅርበት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቃለ ምልልሳቸው ወቅት፣ የኮርያ ወጣቶች መሠረታቸውን እንዳይረሱ አደራ ብለው፣ የአረጋውያንን ውድ ልምድ እንዲጠቀሙበት፣ ከሥሩ ገንቢ ምግብን ማግኘት እንደሚቻል፣ ፍሬውን እንደሚሰጥ መልካም ዛፍ እንደሆነ ለወጣት ኮሪያውያን አስረድተዋል። የተሻለ ዓለምን መገንባት የሚቻለው ሳይደክሙ በመጓዝ፣ ፈጠራን በመጠቀም እና ድንበር በሌለው ሰፊ ልብ በመመራት መሆኑን አስረድተዋል።