ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የዩክሬን እህል እንደ የጦር መሣሪያ መጠቀም የለበትም ማለታቸው ተገለጸ! ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የዩክሬን እህል እንደ የጦር መሣሪያ መጠቀም የለበትም ማለታቸው ተገለጸ!  (AFP or licensors)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የዩክሬን እህል እንደ የጦር መሣሪያ መጠቀም የለበትም ማለታቸው ተገለ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት በዓለም ዙሪያ የእህል እጥረት በከፍተኛ ደረጃ እየተከሰተ መምጣቱን የሚያመልክት ዜና እና ማስጠንቀቂያዎች ከፍተኛ ስጋት እንደ ፈጠረባቸው ገልጸው “አለም አቀፍ የምግብ መብትን ለማረጋገጥ ሁሉም ዓይነት ጥረት እንዲደረግ” ተማጽነዋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከዩክሬን ወደ ውጭ የሚላኩ የእህል ምርቶች እገዳ እንዲቆም የተማጸኑ ሲሆን ቅዱስነታቸው ይህንን ተማጽኖ ያቀረቡት ደግሞ በግንቦት 24/2014 ዓ.ም ላይ በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ሳምንታዊውን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማጠቃለያ ላይ ባስተላለፉት መልእክት እንደ ነበረም ተገልጿል።

“በጣም የሚያሳስበኝ ጉዳይ ነው” ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ከዩክሬን ወደ ውጭ የሚላኩ የእህል ምርቶች እገዳ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት በተለይም በድሃ አገሮች ውስጥ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል” ብለዋል።

አለማቀፋዊ መብትን ለማረጋገጥ የተደረገው ጥረት

“ይህን ችግር ለመፍታትና ዓለም አቀፋዊውን ምግብ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ ጥረት እንዲደረግ አጥብቄ እጠይቃለሁ” ያሉት ቅዱስነታቸው "እባካችሁ ስንዴ፣ ዋና ምግብ ስለሆነ እንደ የጦር መሣሪያ አትጠቀሙ!" በማለት ጥሪ አድርገዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ባካሄደችው ወረራ ምክንያት የተከሰተውን የእህል እጥረት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እንዳሉት አለም አቀፍ የምግብ ቀውስ ማስከተሉ ተገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአለም የምግብ ቀውስ እያንዣበበ መሆኑን አስጠንቅቋል። የምዕራባውያን መሪዎች የዩክሬንን ወደቦች በመዝጋት ዓለምን የምግብ ቀውስ እንዲከሰት አድርጋለች በማለት ሩሲያን ቢወቅሱም የዩክሬንን የእህል ምርት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ እየተሞከረ ነው።

ጦርነቱ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት የእህል፣ የምግብ ዘይት፣ የማዳበሪያ እና የኃይል አቅርቦት ዋጋ ጨምሯል፣ እናም በዩክሬን ወረራ ምክንያት ምዕራባውያን ሀገራት በሩሲያ ላይ ማዕቀብ ሲጥሉ ቆይተዋል።

ቀውሱን ለመታደግ ዩክሬን ያላትን ሰፊ የእህል ክምችት በመንገድ፣ በወንዝ እና በባቡር ወደ ውጭ ለመላክ እየጣረች ቢሆንም፣ የግብርና ባለስልጣናት ግን ሩሲያ በዩክሬን ጥቁር ባህር ወደቦች ላይ የጣለችውን እገዳ ካላነሳች ኢላሟን የመምታት እድል እንደሌላት ይገልጻሉ።

እ.ኤ.አ. በ2021 ዓ.ም ዩክሬን እና ሩሲያ አንድ ላይ ወደ 30 በመቶ የሚጠጋውን የዓለም የስንዴ የወጪ ንግድ የያዙ ሲሆን ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ የስንዴ ዋጋ ከ50 በመቶ በላይ ጨምሯል።

ለሰላም እና ጦርነትን ለማስቆም የጳጳሱ ጸሎቶች

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጦርነት በምትታመሰው አገር ሰላም እንዲሰፍን፣ እንዲሁም በዩክሬን ያለው ጦርነት እንዲቆም እና በዓለም ዙሪያ ለሚደረጉ ጦርነቶች ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ጥሪዎች እና ተማጽኖዎች አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ማክሰኞ ምሽት ግንቦት 23/20014 ዓ.ም የማርያም ወር በመባል የሚታወቀው የግንቦት ወር ማብቂያ ላይ በሮም ከተማ በሚገኘው የታላቂቷ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ  በመገኘት በመላው ዓለም በቀጥታ መስመር የተላለፈ የመቁጠሪያ ጸሎት በማድረግ ለእነዚህ ዓላማዎች በመጸለይ ሰላም በምድር ላይ ይስፈን ዘንድ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን አማላጅነት መማጸናቸው ይታወሳል።

01 June 2022, 11:58