ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ቤተክርስቲያን እንደ መልካሙ ሳምራዊ ሆና ቤተሰብን እንድታገለግል እፈልጋለሁ አሉ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ቤተሰቦች ዓለምን ለመለወጥ የሚችሉ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን ቅዱስነታቸው ይህንን የተናገሩት ከሰኔ 15 እስከ ሰኔ 19/2014 ዓ.ም በመካሄድ ላይ በሚገኘው የአለም የቤተሰብ ቀን ስብሰባ መከፈቻ ላይ እንደ ነበረም ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

አሥረኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀን ስብሰባ ረቡዕ ምሽት ሰኔ 15/2014 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን ይህ 10ኛው የዓለም የቤተሰብ ቀን ስብሰባ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተገኙበት በእለቱ መጀመሩ ይታወሳል።

የዘንድሮው የዓለም የቤተሰብ ቀን ስብሰባ ከቀደሙት ዓመታት በተለየ መልኩ " ከአንድ በላይ ማእከል ያለው እና ሰፊ" በሆነ መልኩ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ አህጉረ ስብከት እና አድባራት እየተካሄደ ነው። በተመሳሳይ ከ120 ሀገራት የተውጣጡ ከሁለት ሺህ የሚበልጡ ልዑካን ወደ ሮም መጥተዋል ለአምስት ቀናት የሚቆየውን ዝግጅት በመካፈል ላይ የሚገኙ ሲሆን ይህም ጋብቻ እና ቤተሰብ በዛሬው ዓለም ያለውን ውበት ለማጉላት ታስብ እየተካሄደ ያለ ስብሰባ ነው።

ስለቤተሰብ ህይወት ደስታ እና ተግዳሮት መመስከር

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዘመናዊው ዓለም ስላለው የቤተሰብ ሕይወት ደስታን፣ ጭንቀቶችን፣ ችግሮች እና ተስፋዎችን ያካፈሉ በርካታ ቤተሰቦች የሰጡትን ምስክርነት በማዳመጥ በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ  ስድስተኛ አዳራሽ በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቶች ላይ ተሳትፈዋል።

ከካንሰር ጋር ስትዋጋ እምነቷን የጠበቀች የእግዚአብሔር አገልጋይ ኪያራ ኮርቤላ ፔትሪላ በመባል የሚታወቁ የህይወት ደጋፊ ወላጆችን ያካተተ ስብሰባ ሲሆን ዩክሬናዊ የሆነች እናት እና ሴት ልጇ በዩክሬን ጦርነትን ሸሽተው በመጡበት ወቅት በእንግድነት የተቀበሏቸው ከጣሊያን ቤተሰብ ጋር በስብሰባው ላይ የተሳተፉ ሲሆን በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢጣሊያ አምባሳደር የነበሩት እና የስበዓዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ በነበረበት ወቅት የተገደለው ሰው ባልቴት የሆነችው ሙስሊም ሴት በስብሰባው ላይ ምስክርነት ከሰጡ ሰዎች መካከል ይገኙበታል።

አብሮ መጓዝ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለምስክርነታቸው ምላሽ ሲሰጡ፣ በዓለም ዙሪያ ላሉት ባለትዳሮች እና ቤተሰቦች በተጨባጭ ሁኔታቸው ከእነሱ ጋር ያለውን ቅርርብ አረጋግጠዋል። የማበረታቻ ቃላቶችቸውም እንዲህ በማለት ተንግረዋል “ካላችሁበት ጀምራችው እና ከዚያ ከምትገኙበት ቦታ ተንስታችሁ ለመጓዝ ሞክሩ፡ እንደ ባለትዳሮች፣ አንድ ላይ ከገዛ ቤተሰባችሁ፣ በአንድነት ከሌሎች ቤተሰቦች ጋር፣ ከቤተክርስቲያን ጋር ወደ ፊት ለመጓዝ ሞክሩ” ማለታቸው ተገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የደጉ ሳምራዊን ምስል በማስታወስ “እኔ የምፈልገው ቤተክርስቲያን ለሁላችሁም እንድትሆን ነው፣ እንደ ደጉ ሳምራዊ ወደ እናንተ የምትቀርብ  በጉዞአችሁ እንድትቀጥሉ እና አንድ እርምጃ ወደፊት እንድትወስዱ የሚረዳችሁ በዚህ መልኩ የምታግዛችሁ ቤተክርስቲያን እንድትኖር እሻለሁ” ብለዋል።

ቀደም ሲል ቤተሰቦች የሰጡትን ምስክርነት በመጥቀስ፡- ለትዳር ግልፅነት ወደፊት መሄድ፣ መስቀሎችን ማቀፍ፣ ወደ ይቅርታ፣ ሌሎችን መቀበል እና ወንድማማችነትን ማጎልበት በማለት ከእርምጃዎች መካከል ጥቂቶቹን ጠቁሟል።

ተልዕኮ እና ለአለም ምስክር መሆን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ እያንዳንዱ ቤተሰብ “በዓለማችን ውስጥ የሚያከናውነው ተልእኮ አለው፣ ይህም ምስክርነት መስጠት ነው” በማለት በአፅንዖት ተናግረዋል።

 “ጌታ በህይወታችን ውስጥ ለምናገኛቸው ሁሉ ሊናገር የሚፈልገው ቃል ምንድን ነው? ዛሬ ቤተሰባችንን ምን ‘እድገት’ እየጠየቀ ነው?” የሚለውን ጥያቄ እንዲመልሱ ይህንን ጥያቄ ቤተሰቦች እራሳቸውን እንዲጠይቁ ጋብዟቸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ቤተሰቦች አንዴ “ቆም እንዲሉ እና እንዲያዳምጡ” እናም እራሳቸውን “በእሱ እንዲለወጡ እንዲፈቅዱ ጥሪ አቅርበዋል፣ ስለዚህም እናንተም ዓለምን እንድትለውጡ እና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እንዲሰማችው እና እናንተም በተራችው በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖራችሁ ከክርስቶስ ጋር እንድትገናኙ እርሱ እናንተን እንደ ሚወዳችሁ ማወቅ አለባችሁ ብለዋል።

የዓለም የቤተሰብ ቀን ስብሰባ እስከ መጭው እሁድ ሰኔ 19/2014 ዓ.ም ድረስ እንደ ሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን ቅዳሜ ምሽት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በሚያሳርጉት መስዋዕተ ቅዳሴ እንደ ሚጠናቀቅ፣ ከእዚያም እሁድ ሰኔ 19/2014 ዓ.ም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በሚደርገው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሚያደርጉት ንግግር በይፋ እንደ ሚፈጸም ተገልጿል።

24 June 2022, 14:37