ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ለአደጋ ለተጋለጡት ሰዎች ቅድሚያን መስጠት እንደሚገባ አሳሰቡ

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ማስተባበሪያ ቢሮ፣ ግንቦት 30/2014 ዓ. ም. አዲስ የቪዲዮ ቅንብር ይፋ ማድረጉ ታውቋል። የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ማስተባበሪያ ቢሮ ይፋ ያደረገው የቪዲዮ ቅንብሩ፣ በኢኳዶር ውስጥ ከቤተሰቧ ጋር አዲስ ሕይወት የገነባችውን ሐና የተባለች ቬንዙዌላዊት ስደተኛ የሕይወት ተሞክሮን የሚያጎላ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቪዲዮ ቅንብሩ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑት ቅድሚያን መስጠት ማለት ምን ማለት ነው?” በማለት ያቀረቡት ጥያቄም የተካተተ ሲሆን፣ ማክሰኞ ግንቦት 30/2014 ዓ. ም. ይፋ የሆነው አዲሱ የቪዲዮ ቅንብሩ የበርካታ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች፣ የተፈናቃዮች እና የሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሰለባ የሆኑት ሰዎች የሚገኙበትን ሁኔታ አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑ ታውቋል። በቪዲዮ ቅንብሩ፣ ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማንም ሰው ከማኅበራዊ ሕይወት መገለል እንደሌለበት አጽንኦት ሰጥተው፣ እያንዳንዱ ሰው በአካባቢው ተገቢ ሥፍራ እንዲሰጠው፣ ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰቡ ክፍሎች አስፈላጊው ትኩረት እንዲሰጣቸው በማለት ማሳሰባቸው ተመልክቷል።

ለአደጋ ተጋላጮች ቅድሚያ ይሰጥ!

የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ማስተባበሪያ ቢሮ ያዘጋጀው የቪዲዮ ቅንብሩ፣ በርካታ አስተያየቶችን የያዘ ሲሆን፣ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆነው የማኅበረሰብ ክፍል ቅድሚያን መስጠት እንደሚያስፈልግ ያብራራል። ለአደጋ ለተጋለጡት ቅድሚያን መስጠት ማለት “ቅዱስ ወንጌልን ማስቀደም፣ በማንኛውም ጊዜ  መገለል፣ አቅመ ደካማነት ወይም ለአደጋ የመጋለጥ ክፉ ዕድል  እያንዳንዳችንን በማንኛውም ወቅት ሊያጋጥም እንደምንችል መረዳት” ማለት እንደሆነ የቪዲዮ ቅንብሩ በማስረዳት፣ ለሁሉም ሰው እኩል ዕድሎችን በማመቻቸት ኅብረትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።   

የሐና ታሪክ

ከቤተሰቧ ጋር በኢኳዶር አዲስ ሕይወት የገነባችው ሐና፣ ከቬንዙዌላ የመጣች ስደተኛ መሆኗን የቪዲዮ ቅንብሩ ገልጾ፣ የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ሐና ፋሪያ ከባለቤቷ ጋር በመሆን ለልጆቿ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ፣ በአገሯ ያለውን ችግር ሸሽታ ወደ ኤኳዶር መሰደድን የሚገልጽ መሆኑ ታውቋል። ሐና በኢኳዶር ውስጥ አዲስ ሕይወት ከጀመረች በኋላ በምትኖርበት አካባቢ የምታበረክተው የሕክምና አገልግሎት በማኅበረሰቡ መካከል ለተቸገሩ ሰዎች ግንዛቤን በማስጨበጥ ማበረታቻ እውቀት እንደሚሰጣቸው ታውቋል። ሐና በዚህ የቪዲዮ ቅንብር የቤተሰቦቿን ታሪክ በኤኳዶር ውስጥ እንደገና መገንባቷን፣ ልጆቿም በዚያች አገር ውስጥ ማደጋቸውን፣ አዳዲስ ትዝታዎችንን እና ታሪኮችን በዚያች አገር ውስጥ እያሳደገች መምጣቷን ገልጻለች።

ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን

ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን በየዓመቱ በመስከረም ወር መጨረሻ እሁድ የሚከበር ሲሆን፣ ዘንድሮ የሚከበረው በመስከረም 15/2015 ዓ. ም. እንደሆነ ታውቋል። በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ማስተባበሪያ ቢሮ ዘንድሮ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ በዓል በማስመልከት አጫጭር የቪዲዮ ቅንብሮችን በማዘጋጀት በልዩ ልዩ አገራት የሚታዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለማምለጥ የተገደዱት ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ልምድ ላይ ትኩረት ለመስጠት ዘመቻ መጀመሩ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዘንድሮ መስከረም 15/2015 ዓ. ም. ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን መልዕክታቸው፣ “ከስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጋር መልካም የወደፊት ሕይወትን መገንባት” የሚል መሪ ርዕሥ መምረጣቸው ታውቋል።

07 June 2022, 16:39