ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የዕድሜ ባለጸጋነት ለዘለዓለማዊ ሕይወት የሚያዘጋጀን መሆኑን አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኔ 1/2014 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን በዮሐ. 3:3-6 በተጻፈው ላይ በማስተንተን የረቡዕ ዕለት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን አቅርበዋል። የዛሬው አስተምህሮአቸው ከዚህ ቀደም በአረጋዊያን ዙሪያ ጀምረውት ከነበረው አስተምህሮ የቀጠለ የክፍል 13 አስተምህሮ እንደነበር ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከጣሊያን እና ሌሎች ልዩ ልዩ አገራት ለመጡት በርካታ ምዕመናን ባቀረቡት በዛሬው አስተምህሮአቸው፣ እርጅና ለዘለዓለማዊ ሕይወት የሚያዘጋጀን መሆኑን አስገንዝበው፣ አረጋዊያን የእግዚአብሔርን ርኅራሄን እንድንመለከት የሚያግዙን መሆናቸውንም አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዕለቱ የተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ

“ኢየሱስም መልሶ፣ ‘እውነት እልሃለሁ፤ ማንም ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም’ አለው። ኒቆዲሞስም፣ ‘ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ዳግመኛ እንዲወለድ ተመልሶ ወደ እናቱ ማሕፀንስ ሊገባ ይችላልን?’ አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ ‘እውነት እልሃለሁ፤ ማንም ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፤ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደም መንፈስ ነው።’ (ዮሐ. 3: 3-6)

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በወንጌላት ውስጥ ከተጠቀሱት አረጋውያን ገጸ-ባህሪያት መካከል አንዱ ኒቆዲሞስ ነው። ኒቆድሞስ ከአይሁድ መሪዎች መካከል አንዱ ነው። ኢየሱስን ለማወቅ ካለው ፍላጎት የተነሳ አንድ ቀን በምሽት ተደብቆ ወደ እርሱ ሄደ። (ዮሐ 3:1-21) በዚያን ወቅት በኢየሱስ እና በኒቆዲሞስ መካከል በነበረው ውይይት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ እና የማዳን ተልዕኮው ዋና ጭብጥ ተገለጠ። እንዲህ ተብሎ የተጻፈው ይገለጽ ዘንድ፥ ‘በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና፤’ (ዮሐ. 3:16)

ኢየሱስም ለኒቆዲሞስ እንዲህ አለው፥ ‘እውነት እልሃለሁ፤ ማንም ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም’። (ዮሐ. 3:3) ይህ ማለት አዲስ እና የተሻለ ሕይወት ለመኖር ዕድል እንዳለን ተስፋ በማድረግ፣ ከተወለድንበት ጊዜ ጀምሮ የኖርነውን ሕይወት ለመድገም ወደ ዓለም እንደገና መምጣት ማለት አይደለም። ሕይወትን መደጋገም ትርጉም የለውም። ይልቁን የኖርንውን ሕይወት ትርጉም የሚያሳጣን እና ባዶ የሚያደርግ፣ ያልተሳካ ሙከራ፣ ጊዜያችን በከንቱ ያለፈበት እና የባከነ ያደርገዋል። ኢየሱስም ለኒቆዲሞስ፥ “ማንም ዳግመኛ ካልተወለደ’ ሲል ከዚህ በፊት የኖርነውን ሕይወት ለመድገም አይደለም። ሕይወት በእግዚአብሔር ፊት ትልቅ ዋጋ አለው። በእግዚአብሔር ርኅራኄ የተወደድን ፍጡራን መሆናችንን ያረጋግጥልናል። "ከላይ መወለድ" ፣ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንገባ ዘንድ የሚፈቅድልን፣ ትውልድ በሙሉ በመንፈስ ቅዱስ አንድ መሆንን፣ ውሃዎችን በመሻገር ፍጥረት ከእግዚአብሔር ፍቅር ጋር በመታረቅ ወደ ተስፋይቱ ምድር መሸጋገርን ያመለክታል።

ኒቆዲሞስ በዚህ መልክ እንደገና መወለድን በተሳሳተ መንገድ በመረዳት፣ ማርጀት የማይቻል መሆኑን ማስረጃ እንዲሰጠው ጠይቋል። የሰው ልጅ ማርጀቱ የማይቀር ነው፤ ለዘላለም ወጣት ሆኖ የመቆየት ህልም በቋሚነት ወደ ኋላ ይመልሳል። የሕይወት ፍጻሜ የማንኛውም ልደት እጣ ፈንታ ነው። አንድ ሰው እንዴት የጉዞ መዳረሻን ከመወለድ ጋር አያይዞ መገመት ይችላል?

የኒቆዲሞስ ተቃውሞ ለእኛ ትምህርት ይሆነናል። በኢየሱስ ክርስቶስ ቃል መሠረት እርጅና ተገቢ ተልእኮ ያለው መሆኑን መረዳት እንችላለን። በእርግጥም፣ እርጅና ኢየሱስ ክርስቶስ ለተናገረው እና ከላይ የመወለድን ምስጢር ለማብራራት የሚያስችለን ትክክለኛ ጊዜ እንጂ እንቅፋት ሊሆን አይችልም። እርጅና ከተስፋ ቢስነት ነጻ ያደርገናል። ዘመናችን እና ባሕላችን ልጅ መወለድን እንደ ቀላል የሰው ልጅ ወደዚህች ምድር የመምጣትን እና ሥነ ሕይወታዊ መራባት አድርጎ በመቁጠር አሳሳቢ ዝንባሌዎችን ያሳየበት፣ ዕድሜአችንን በሙሉ በወጣትነን ቁመና መኖር የሚለው ሕልም እንዲያድግ ያደርጋል። በብዙ መልኩ ለእርጅና ክብር እና አድናቆት የማይቸርለት ለምንድነው? እርጅና የማይደነቀው ወይም የማይወደደው ‘ከእናታችን ማሕጸን እንደገና መወለድ’ የሚለውን ሕልም ወይም ተረት ስለሚቃረን ነው።

የዘመናችን ቴክኖሎጂዎች በሁሉም መንገድ በዚህ ተረት ወይም ሕልም ተማርከዋል። ላለመሞት ከሚደረገው ትግል ጋር ሰውነታችንን በመድኃኒት እና በመዋቢያዎች እገዛ ሕይወትን ለማቆየት፤ እርጅናን ለመቀነስ፣ ለመደበቅ እና ከተቻለ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ለመሻር ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛል። በተፈጥሮ እንድ ሰው ደህንነቱን ለመጠበቅ የሚያደርገው እንክብካቤ አንድ ነገር ነው። ነገር ግን ይህን እንክብካቤ ለማስረዳት የምንጠቀምበት ሕልም ወይም አፈ ታሪክ ሌላ ነው። ይሁን እንጂ በሁለቱ መካከል ያለው ውዥንብር በውስጣችን የተወሰነ፣ በአእምሮአችን ግራ የማጋባት ሁኔታን እየፈጠረ መሆኑን መካድ አይቻልም።

በሚሞት ሥጋችን ውስጥ ያለው ሕይወት ገና ፍጻሜውን ያላገኘ እውነታ በመሆኑ ውብ እና መልካም ነው። ምክንያቱም ሥራው እንዳላለቀለት የሥነ ጥበብ ሥራ ልዩ ትኩረት ስለሚሰጠው ነው። እርጅና የሕይወት መጀመሪያ እንጂ መጨረሻው አይደለም። የሰው ልጅም ወደዚህ ዓለም የመጣው በዚህ መልክ ነው፤ በዓለም ውስጥ እንደ ሰው ለዘላለም ይኖራል። ነገር ግን በሚሞተው ሥጋችን ውስጥ ያለው ሕይወት በቦታ እና በጊዜ ገደብ ሳይበላሽ ለማቆየት እና በዓለም ውስጥ እጅግ ውድ የሆነው የሕይወታችን ክፍልን ለማሟላት ያለን ጊዜ በጣም አጭር ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ስለተፈጠርንለት ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የሚናገረውን የቅዱስ ወንጌል መልካም ዜናን የሚቀበል እምነት እጅግ አስደናቂ እና ቀዳሚ እንደሆነ ተናግሯል። ምክንያቱም እምነት የእግዚአብሔርን መንግሥት እንድናይ ያስችለናል። በእምነት አማካይነት፣ ሕይወታችን በእግዚአብሔር በኩል የዘላለማዊነት ተስፋ ምልክቶች እንዳሉት በእውነት ማየት እንችላለን።

ምልክቶቹም በኢየሱስ ክርስቶስ በብዙ መንገድ የተገለጡ የቅዱስ ወንጌል ፍቅር ምልክቶች ናቸው። እነዚህን ምልክቶች ማየት ከቻልን፣ እንደገና በሚታደሰው ውሃ ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ በኩል ወደ እግዚ አብሔር መንግሥት መግባት እንችላለን።

እርጅና ብዙዎቻችን ከላይ በሚገኝ እንደገና የመወለድ ተአምር ውስጥ እንድንገባ የተሰጠን መንገድ ነው።ለሰብዓዊ ማኅበረሰብም ተዓማኒነት ያለው ነው። እርጅና ለመዳረሻችን ያለውን ፍቅር የሚገልጽ እንጂ የጊዜ ገደብ ተሰጥቶት መጨረሻችንን እያሰብን ዘወትር እንድንጨነቅ የሚያደርገን መሆን የለበትም። በዚህ መሠረት እርጅና ልዩ ውበት ያለው፣ ወደ ዘላለማዊነት የምንጓዝበት መንገድ ነው። የዘመኑን ቴክኖሎጂ ይሁን የተለያዩ ምግቦችን በመመገብ ማንም ሰው ወደ እናቱ ማሕጸን ውስጥ እንደገና መግባት አይችልም። የሚቻልስ እንኳ ቢሆን ያ የሚያሳዝን እንጂ የሚያስደስት አይደለም። እርጅና መዳረሻው ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ሰማያዊው መንግስት የሚጓዙበት መንገድ ነው። ስለዚህ እርጅና ከወደፊት የሥነ ሕይወት እና ቴክኖሎጂያዊ ቅዠት የምንለይበት ልዩ ጊዜ ነው። እርጅና በተለይም የእግዚአብሔርን ርኅራኄ እና የፍጥረት ሥራውን መረዳት እንድንችል ያግዘናል። መንፈስ ቅዱስ ከላይ መወለድ ጋር አንድ የሚያደርገን የእርጅና መንፈሳዊ እና ባሕላዊ ተልእኮን የምናውቅበት ልብ ይስጠን።”

08 June 2022, 16:35