ፈልግ

የምዕመናን ጸሎት፤ የምዕመናን ጸሎት፤ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ምዕመናን እንደ ቅድስት ሄድዊግ ለአውሮፓ ሰላም እንዲጸልዩ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሰኔ 1/2014 ዓ. ም. ካቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ቀጥለው በአደባባዩ ለተገኙት ምዕመናን ንግግር አድርገውላቸዋል። በፖላንድ ውስጥ የጃጊሎኒያን ዩኒቨርሲቲ መሥራች የሆነችውን ፖላንዳዊቷን ንግሥት ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ የፖላንድ ምዕመናን በአውሮፓ ውስጥ ጦርነት እንዲቆም የቅድስት ሄድዊግ አማላጅነት በጸሎት እንዲጠይቁ አደራ ብለዋል። የቀድሞ ር. ሊ ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ. አ. አ ሰኔ 8/1997 ዓ. ም. በፖላንድ ክራኮቭ ከተማ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ የንግሥት ሄድዊግ ቅድስናን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት ሄድዊግ ሕይወት ከፖላንድ አገር ሕዝብ ሕይወት ጋር የተገናኘ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ በፖላንድ እ. አ. አ በ1174 ዓ. ም. የተወለደችው ቅድስት ሄድዊግ ከባቫሪያን ቤተሰብ የተወለደች ሲትሆን፣ የፖላንድ ንግሥት ሆና በኖረችባቸው ዓመታት ውስጥ ከገቢዎቿ መካከል ከፍተኛውን ድርሻ ለድሆች መስጠቷ ይታወሳል። በፖላንድ ውስጥ በሚገኝ የዋዌል ካቴድራል ውስጥ በሚገኝ ቅዱስ መስቀል ፊት ለፊት ረጅም ሰዓታትን በጸሎት ማሳለፏ ይታወሳል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን የቅድስት ሄድዊኝ ሕይወት በማስታወስ ባደረጉት ንግግር፣ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የንግሥት ሄድዊግ ቅድስናን ይፋ ማድረጋቸው አስታውሰው፣ ምዕመናን በአማላጅነቷ ተደግፈው፣ እንደ እርሷ በቅዱስ መስቀሉ ፊት ቀርበው ለአውሮፓ ሰላም ጸሎት እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል።

የእርቅ ንግሥት

ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ. አ. አ. ሰኔ 8/1997 ዓ. ም. በፖላንድ ክራኮቭ ከተማ የንግሥት ሄድዊግን ቅድስና ያፋ ያደረጉበትን እና በርካታ ምዕመናን የተካፈሉነት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት መምራታቸው ይታወሳል። ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በጸሎት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባሰሙት ንግግር፣ የቅዱስት ሄድዊግ ክብር የመጣው ከንጉሣዊ ቤተሰብነት ምልክት ሳይሆን ከመንፈስ ጥንካሬ፣ ከአእምሮ ጥልቀት እና ከልበ ርኅሩኅነት የመነጨ እንደነበር መናገራቸው ይታወሳል።

ቅድስት ሄድዊግ
ቅድስት ሄድዊግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለምዕመናኑ ባሰሙት ንግግር፣ “የአገራት መሪዎች፣ ሃያላን በኃይል እና በጉልበት እንደሚገዙ፣ በእናንተ ዘንድ ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ ፣ በመካከላችሁ ታላቅ ሊሆን የሚወድ ግን ራሱን የእናንተ አገልጋይ ያደርግ" የሚለውን የማቴ 20፡25-26 ጥቅስ በማስታወስ፣ እነዚህ የኢየሱስ ክርስቶስ ቃላት በወጣቷ አንጄቪን የዘር ሐረግ ሕሊና ውስጥ ዘልቀው መግባታቸውን አስረድተዋል። ማኅበራዊ አቋሟ እና ተሰጥኦዋ፣ የግል ሕይወቷን ሙሉ በሙሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት ያቀረበች እና መንገሥ ሲገባት ደግሞ ሕይወቷን በአደራ ለተሰጣት ሕዝብ አገልግሎት ማዋሏን ገልጸዋል።

08 June 2022, 16:49