ፈልግ

የዓለም የቤተሰብ ቀን ስብሰባ ኦፊሴላዊ አርማ የዓለም የቤተሰብ ቀን ስብሰባ ኦፊሴላዊ አርማ 

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ‘የቤተሰብ ፍቅር የቅድስና ጥሪ እና መንገድ ነው’ ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ አሥረኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ በዚህ ሳምንት በሮም ሊካሄድ እንደ ሆነ ገልጸዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሰኔ 12/2014 ዓ.ም ባስተላለፉት ሳምንታዊ ምልእክት በመጪው ረቡዕ በሰኔ 15/2014 ዓ.ም በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ አስረኛው የአለም አቀፍ የቤተሰብ ቀን ስብሰባ በሮም ከተማ እንደሚጀምር ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በእንግሊዘኛው ምህጻረ ቃል (WMOF፤ World Meeting of Families) እ.ኤ.አ. በ1994 ዓ.ም በቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የተመሰረተ የዓለም የቤተሰብ ስብሰባ ቀን ነው።

የምእመናን፣ ቤተሰብ እና ሕይወት ጉዳዮችን የሚመለከተው ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የተዘጋጀው የዘንድሮው የዓለም የቤተሰብ ቀን መሪ ቃል “የቤተሰብ ፍቅር፡ ጥሪ እና የቅድስና መንገድ” ነው የሚለው እንደ ሆነ ተገልጿል።

በዚህ ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ሕዝባዊ ስብሰባ፣ ዝግጅቱ በሁሉም አህጉረ ስብከት ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳት ጋር እንዲከበር፣ አካባቢያዊ የሕነጻ ትምህርቶችን፣ የጸሎት እና የኅብረት ልምድ እርስ በእርስ በመለዋወጥ እንዲከበር መወሰኑ ይታወሳል።

ሆኖም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የካቶሊክ ቤተሰቦችን በመወከል ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ ልዑካን እ.አ.አ ከሰኔ 22 እስከ 26/2022 ዓ.ም በቫቲካን ጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ እንደ ሚካሄድ ተገልጿል።

ከዚህ ቀደም እንደ ሚደርገው ሁሉ በዚህ መሰረት፣ በመርሃ ግብሩ መጀመሪያ እና መጨረሻ ላይ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በተገኙበት፣ በሥርዓተ ቅዳሴ የሚጀምር እና የሚጠናቀቅ ሲሆን የቤተሰብ በዓልን በማስመልከት ዓለም አቀፍ የነገረ መለኮት - መጋቢ ጉባኤን ያካትታል።

የጳጳሱ የምስጋና ቃላት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እሁድ ሰኔ 12/2014 ዓ.ም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ አስተንትኖ ካደረጉ በኋላ ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልእክት እንደተናገሩት ስብሰባው በሮም እና በተመሳሳይ ጊዜ በመላው ዓለም እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

ጳጳሳትን፣ የሰበካ ካህናትን እና ለቤተሰብ ሐዋርያዊ እንክብካቤ የሚያደርጉትን እና በቤተሰብ ዙሪያ የሚሰሩትን በሙሉ አመስግነዋል።

“ከሁሉም በላይ፣ ለቤተሰባዊ ፍቅር እንደ ጥሪ እና የቅድስና መንገድ ለሚመሰክሩት ባለትዳሮች እና ቤተሰቦች አመሰግናለሁ፣ መልካም ስብሰባ ይሁንላችሁ!" ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

20 June 2022, 13:19