ፈልግ

ቅዱስነታቸው እ. አ. አ በ2018 ዓ. ም. በሮም በተካሄደው በዓል ላይ ከወጣቶች ጋር ሲገናኙ ቅዱስነታቸው እ. አ. አ በ2018 ዓ. ም. በሮም በተካሄደው በዓል ላይ ከወጣቶች ጋር ሲገናኙ  (Vatican Media) ርዕሰ አንቀጽ

"ወንጌልን ማወጅ" የተሰኘው አዲሱ ሐዋርያዊ ሕገ ቀኖና የመድረሻ እና የመነሻ ነጥብ በአጭሩ፤

በላቲን ቋንቋ “Praedicate Evangelium” (ወንጌልን ማወጅ)፣ “የሮማን ኩሪያ” በቅድስት መንበር አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ መሣሪያ ቤቶችን እና ጳጳሳዊ ምክር ቤቶችን ያቀፈ የባለ ሥልጣናት ስብስብ ነው። ለካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትክክለኛ አሠራር እና ዓላማዋን ለማሳካት አስፈላጊውን አደረጃጀት የሚያስተባብር እና የሚያቀርብም ነው። በአጠቃላይ "የቤተክርስቲያን አስተዳደር" ተብሎ ይታሰባል። “ኩሪያ” በመካከለኛው ዘመን፣ በኋላም በላቲን ቋንቋ አገላለጽ "ፍርድ ቤት" የሚለው ትርጉም ሲሰጠው፣ በ"ንጉሣዊ ፍርድ ቤት" ትርጉሙ "የሕግ አውጭው ፍርድ ቤትን" ቢወክልም ከላይ የተገለጸውን አዲሱ ሐዋርያዊ ሕገ ቀኖና ተግባራዊ የሚደርግ፣ ር. ሊ. ጳ. ለመላዋ ቤተክርስቲያን የሚያበረክቱትን አገልግሎት በማገዝ እና የታዩ ለውጦችን ተቋማዊ የሚያደርግ የቅድስት መንበር ዋና ተቋም ነው።

"ወንጌልን ማወጅ" የተሰኘው አዲሱ ሐዋርያዊ ሕገ ቀኖና የራሳችን መነሻ እና መዳረሻ ቦታ ነው፤ ወይም አንድ ሰው 'እንደገና መጀመር' ሊል ይችላል። እ. አ. አ ሰኔ 5/2022 ዓ. ም. የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የጰንጤቆስጤ በዓል ከተከበረ በኋላ በሥራ ላይ የዋለው የአዲሱ ሐዋርያዊ ሕገ ቀኖና፣ “ወንጌልን ማወጅ” የሚል አርዕስት የተሰጠው ሲሆን፣ ለአሥር ዓመታት ያህል የቆየው የተሃድሶ መንገድ ፍጻሜን አግኝቶ በሥራ ላይ መዋል ጀምሯል። ጉዞው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ማዕረግ ከመቀበላቸው በፊት፣ እ. አ. አ ከ2013 ዓ. ም. በፊት በተደረገው የጠቅላላ ጉባኤ ውይይት መጀመሩ ይታወሳል።

አርታዒ አንድሬያ ቶርኒዬሊ፣ ቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ - ቫቲካን  

ተሃድሶ የተጀመረው በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ. አ. አ 1988 ዓ. ም፣ በላቲን ቋንቋ “Pastor Bonus” በአማርኛ (መልካም እረኛ) በሚል አርዕስት በቀረበው ሕገ ቀኖና በኋላ በይፋ የተሃድሶ ሥራ መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፣ ቀጥሎም ር. ሊ. ጳ ጳውሎስ 6ኛ እ. አ. አ በ1967 ዓ. ም. በላቲን ቋንቋ “Universi regimini Ecclesiae” በአማርኛው (የመላው ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር) በሚል አርዕስት ይፋ በሆነው ሕገ ቀኖና ተሻሽሎ የቀረበ ነበር። አዲሱን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮን ሐዋርያዊ ሕገ ቀኖና ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ጋር የሚያገናኝ፣ ለስብከተ ወንጌል ቅድሚያ መስጠት እና የምእመናን ሚና ዋና ዋና ሃሳቦችን በብዛት አቅፎ የያዘ መልእክት ነው።

የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች

በመጀመሪያ ደረጃ እስካሁን የተከናወኑ ጉልህ ስኬቶችን እንመልከት። ማሻሻያዎቹ ሆን ተብሎ ከመመረጥ ይልቅ ከፍርድ ሂደት አስፈላጊነት ጋር በተቆራኘ መልኩ የተጀመረው በቅድስት መንበር የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ተቋማት ነው። እ. አ. አ. በ 2014 ዓ. ም. ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የኢኮኖሚ አስተዳደርን የመቆጣጠር እና የሮማን ኩሪያ የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች እና ምክር ቤቶች አስተዳደራዊ የገንዘብ አወቃቀሮችን እና እንቅስቃሴዎችን የመቆጣጠር ተግባር ያለውን የኢኮኖሚ ምክር ቤት አቋቋሙ። በዚሁ ጊዜ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የቅድስት መንበር እና የቫቲካን ከተማ አስተዳደር ኢኮኖሚያዊ እና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የሚያስተባብር የሮማን ኩሪያ ቁጥጥር እና መመሪያ መሥሪያ ቤት የሆነውን የምጣኔ ሃብት ዋና ጽሕፈት ቤት አቋቁመዋል። እስካሁን በቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊነት የነበረው የሠራተኞች አስተዳደር አሁን ወደ ኢኮኖሚ ጽሕፈት ተዘዋውሯል።

እርስ በእርስ ግንኙነት፣ ቤተሰብ እና ልማት

ሁለተኛው እርምጃ እ. አ. አ በ2015 የተካሄደው የመገናኛ ጽሕፈት ቤት መመሥረት ሲሆን፣ በኋላም እራሱን የቻለ የመገናኛ ዋና መሥሪያ ቤት ሆኖ 9 የተለያዩ አካላትን ያሰባሰበ (ከጳጳሳዊ የማኅበራዊ ግንኙነት ምክር ቤት እስከ የቅድስት መንበር የተለያዩ ጋዜጦች፣ የቫቲካን ማተሚያ ቤትንም ጨምሮ እንዲያስተዳድር ተደርጎ የተዋቀረ ሲሆን፣ ይህ አዲሱ የመገናኛ ዋና መሥሪያ ቤት እ. አ. አ ከ2018 ዓ. ም. ጀምሮ ፍጹም በሚባል መልኩ በምዕመናን አመራር ሰጪነት የሚተዳደር ዋና መሥሪያ ቤት ሆኖ ተዋቅሯል።

እ. አ. አ. በ2016 ዓ. ም. የምእመናን ፣ቤተሰብ እና የሕይወት ጉዳዮችን የሚመለከተው ጳጳሳዊ ዋና መሥሪያ ቤት የተቋቋመ ሲሆን፣ ይህም የምዕመናን ጳጳሳዊ ምክር ቤት እና የቤተሰብ ጳጳሳዊ ምክር ቤት የነበሩትን አንድ የሚያደርግ እንዲሆን ታስቦ የተቋቋመ ነው። የምእመናንን ሕይወት ከማስተዋወቅ እና ከሐዋርያነት አገልግሎት፣ ለወጣቶች ከሚደርገው ሐዋርያዊ እንክብካቤ፣ ቤተሰብ እና ተልእኮው፣ የሰው ሕይወት ጥበቃን እና ድጋፍን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ብቁ በሆነ መልኩ ተግባሩን የሚያከናውን ዋና መሥሪያ ቤት እንዲሆን ታስቦ የተቋቋመ ነው። እንዲሁም እ. አ. አ. በ 2016 ዓ. ም. ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማትን ለማስፋፋት አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት አቋቋሙ። የፍትህና ሰላም ጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ አንድ ሐሳብ በመባል የሚታወቀው የጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የስደተኞችና ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ ለሚኖሩ ሰዎች ሐዋርያዊ እንክብካቤ የሚያደርገው ጳጳሳዊ ምክር ቤት እና የጤና ባለሙያዎች ጳጳሳዊ ምክር ቤት ሥልጣን በሥሩ ያካተተ ዋና መሥርያ ቤት ተቋቋመ። ይህ ዋና መሥሪያ ቤት ተጠሪነቱ ለ “ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ” (ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በጎ አድራጎት ድርጅት ጭምር ነው።

ግዛት እና እምነት

እ. አ. አ. በኅዳር 2017 ዓ. ም. ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤቶች ላይ ለውጦችን አደረጉ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ጠቅላላ ጉዳዮችን በውክልና ሲመራ የቆየውና ከተለያዩ አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት በበላይነት የሚቆጣጥረው ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ነበር። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የቅድስት መንበር የዲፕሎማሲያዊ ክፍል እየተባለ የሚጠራውን ሦስተኛውን ክፍል አቋቋሙ። በቫቲካን ዋና ጽሕፈት ቤት ውስጥ የተመሠረተው ይህ ክፍል የራሱ ጸሐፊ ያለው እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዲፕሎማሲ ሠራተኞች የቅርብ ትኩረት እንደሚያደርጉ የሚገልጽ ነው። ለቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ አገልግሎት ከሚሠሩ ወይም ከሚዘጋጁ ሰዎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ብቻ የሚመለከት ነው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እ. አ. አ በየካቲት 2022 ዓ. ም. ተጨማሪ የተሃድሶ እርምጃዎችን አካሂደዋል። የቅድስት መንበርን ውስጣዊ መዋቅር፣ በላቲን ቋንቋ “motu propri” ወይም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እና የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ እንደመሆናቸው፣ በተሰጣቸው መንፈሳዊ ስልጣን በራስ ተነሳሽነት፣ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ከግምት ባስገባ መልኩ የሚጽፋቸውን ሰነዶች፣ የሚሰጧቸውን ሹመቶች፣ የሚያደርጓቸውን ውሳኔዎችን አሻሽለው በመለየት ሁለት የተለያዩ ክፍሎች ማለትም የቤተክርስቲያን አስተምህሮ እና የትምህርት ዘርፎች በማቋቋም፣ እያንዳንዱን እራሱን የቻለ ጽሕፈት ቤት እንዲሆን አድርገዋል። ስለዚህ ይህ ዋና መሥሪያ ቤት ሁለት ተወካዮች ያሉት ሲሆን፣ የተሃድሶው ዓላማም ለትምህርተ ሃይማኖት ክፍሉ እና መሠረታዊ ሚናውን በእምነት በማስተዋወቅ ላይ ያለውን የማስተማር ተግባር ወደ ኋላ እንዳይል በርትቶ ወደፊት በመልካም ተግባሩ ይቀጥል ዘንድ በቅርበት ክትትል ለማድረግ ታስቦ የተቋቋመ ነው። በተጨማሪም አላግባብ ይባክን የነበረውን የሰው ኃይል አስተባብሮ በተቀናጀ መልኩ ሐዋርያዊ ተግባራትን ለማከናወን ታስቦ የተቋቋመ ነው። ከሁለቱ አዳዲስ ጸሐፊዎች መካከል አንዳቸውም ኤጲስ ቆጶስ ሆነው አልተሾሙም።

አዲሱ ሕገ ቀኖና

እ. አ. አ መጋቢት 19 ቀን 2022 ዓ. ም. ይፋ የሆነው አዲሱ ሐዋርያዊ ሕገ ቀኖና፣ እስካሁን የተገለጸውን ጠቅላላ መንገድ ያካተተ እና የተሃድሶ ሂደትን በማጠናቀቅ ሌሎች ሃሳቦችንም ያስተዋወቀ ሲሆን፣ ይህም በቤተ ክርስቲያን የተልዕኮ ጥሪ ውስጥ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ እነርሱም፥ በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎች ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት እና አዲስ የወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶችን አንድ የሚያደርግ ሐዋርያዊ ደንብ መሆኑ ታውቋል። ለወንጌል አገልግሎት በሚሰጡት ከፍተኛ ተኩርት ጳጳሳዊ ምክር ቤቱን በቀዳሚነት የሚመሩት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሲሆኑ፣ ሁለት የምክር ቤቱ አስተባባሪ ብጹዓን ጳጳሳት ተመድበው እንዲያግዟቸው የተደረገ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ከዓለም ዙሪያ ለሚቀርብ መሠረታዊ የወንጌል አገልግሎት ጥያቄ መልስ የሚመልስ ሲሆን ሁለተኛው የመጀመሪያው የወንጌል አገልግሎት የሚካሄድባቸውን አዳዲስ ቤተ ክርስቲያናትን የሚከታተል ክፍል መሆኑ ታውቋል።

ሁለተኛው የማሻሻያ ለውጥ የተደረገው በቀድሞ የካቶሊክ ትምህርት ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት እና በቀድሞ ጳጳሳዊ የባሕል ጽሕፈት ቤት መካከል የተደረገውን ውህደት የሚመለከት ሲሆን፣ እነዚህ የቀድሞ ጽሕፈት ቤቶች በአንድ ጽሕፈት ቤት ሥር እንዲሆኑ ተደረገዋል። አዲሱ ሐዋርያዊ ደንቡ ያቀረበው ሦስተኛው ለውጥ የር. ሊ. ጳ ሐዋርያዊ የምጽዋት ማስተባበሪያ መምሪያ በሦስተኛው የቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ምክር ቤት ውስጥ “የበጎ አድራጎት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት” ተብሎ እንዲጠራ መደረጉ ታውቋል። አራተኛው የቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች አካል ያልሆነው እና እስከ ዛሬ ድረስ “የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት” ተብሎ ይጠራ የነበረው አሁን “የሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት” ተብሎ እንዲጠራ ተውስኗል።

ሌላው አዲሱ ሐዋርያዊ ሕገ ቀኖና ያጸደቀው እውቅና፣ የጳጳሳዊ ምክር ቤቶች ተጠሪዎችን ወይም ሃላፊዎችን የሚመለከት ሲሆን፣ ከዚህ በፊት የተሰየሙት እንዳሉ ሆነው፣ አዲስ የሚመረጡት የጳጳሳዊ ምክር ቤት ሃላፊዎች የግድ ካርዲናሎች መሆን እንደሌለባቸው ይደነግጋል። "ወንጌልን ስበኩ" በሚለው አዲሱ ሐዋርያዊ ሕገ ቀኖና ውስጥ የተጠቀሱት ሁለቱ ካርዲናሎች የሐዋርያዊ ልዩ ፍርድ ቤት አስተዳዳሪ እና የኢኮኖሚ ምክር ቤት አስተባባሪ መሆናቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተጨማሪም በጳጳሳዊ ምክር ቤቶች ውስጥ የሚያገለግሉ ካህናት በሮም እና በየአገራቱ በሚገኙ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተዘዋውረው እንዲያገለጉ ለማድረግ በየአምስት ዓመት የሚታደስ ውል ኣዘጋጅተዋል።  

ለምእመናን ግልጽነት

አዲሱ ሐዋርያዊ ሕገ ቀኖናው በመጨረሻም በወደፊት እድገቶች እና በየአገራቱ የሚገኙ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያናት አወቃቀር ተጨባጭነትን ለማረጋገጥ የታሰበ መሆኑ ታውቋል። በዚህ አዲሱ ሐዋርያዊ ደንብ መግቢያ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ "እያንዳንዱ ክርስቲያን በጥምቀት በሚቀበለው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርን ፍቅር እስከሚያገኝ ድረስ የወንጌል ደቀ መዝሙር ነው" በማለት አስታውሰው፣ በዚህም መሠረት የምእመናን ተሳትፎ በመንግሥት የኃላፊነት ሚና ውስጥም የሚገለጽ መሆኑን አስረድተዋል። ማንኛውም ምዕመን በልዩ ብቃት እና ታማኝነት ጳጳሳዊ ምክር ቤትን በአደራ መምራት ከቻለ የሃላፊነት ሚና ሊሰጠው እንደሚችል እና እያንዳንዱ የቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ምክር ቤት የሚመራው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በሚሰጥ ትዕዛዝ መሆኑን አዲሱ ሐዋርያዊ ሕገ ቀኖና ያመለክታል።

06 June 2022, 18:10