ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በዩክሬን ሰላም እንዲሰፍን እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነቶችን እንዲቆሙ እንጸልይ አሉ! ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በዩክሬን ሰላም እንዲሰፍን እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነቶችን እንዲቆሙ እንጸልይ አሉ!  (AFP or licensors)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በዩክሬን ሰላም እንዲሰፍን እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነቶችን እንዲቆሙ እንጸልይ አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቤተ መቅደሶች ሕብረት ጋር በመተባበር በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት እና በዓለም ላይ ባሉ ሌሎች ጦርነቶች ለሚሰቃዩት ሰዎች ሁሉ በሮም ከተማ እምብርት ላይ በሚገኘው የታላቂቷ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ በመጪው ሳምንት በግንቦት 24/2014 ዓ.ም የመቁጠሪያ ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በዚህም የጸሎት ስነ ስረዓት ላይ ምዕመናን ከያሉበት ሥፍራ ሆነው ይሳተፉ ዘንድ ጥሪ ማቅረባቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት እና በዓለም ዙሪያ በሚደረጉ ጦርነቶች ለሚሰቃዩ ሰዎች የተስፋ ምልክት እንዲሆን የመቁጠሪያ ጸሎት እራሳቸው በመምራት እንዲፈጸም የሚያደርጉ ሲሆን በዚህም የጸሎት ዝግጅት ላይ የሰላም ንግሥት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሰላምን በዓለም ዙሪያ ታሰፍን ዘንድ አማላጅነቷን ከምዕመኑ ጋር በጋራ በመሆን እንደ ሚማጸኑም ይጠበቃል።

ይህ አሁን የምንገኝበት ወር የግንቦት ወር እንደ ሆነ ይታወቃል። ይህ የግንቦት ወር በወር ደረጃ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ “የማርያም ወር” በመባል የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ የግንቦት ወር ውስጥ የክርስቶስ፣ የቤተክርስቲያን፣ የእግዚአብሔር እና የምዕመናን እናት ለሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለየት ባለ መልኩ ጸሎት የሚደርግበት፣ አማልጅነቷን የምንማጸንበት፣ በተለይም ደግሞ በልባችን፣ በቤተሰባችን፣ በማኅበረሰባችን፣ በአገራችን እና በአጠቃላይ በዓለም ውስጥ የጥል እና የክርክር ግድግዳ ተደርምሶ በአንጻሩ የሰላም እና የብልጽግና መንፈስ ይወርድ ዘንድ በእርሷ አማላጅነት ወደ ልጇ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመማጸኛ ጸሎት እንድታቀርብልን እርሷን በተለየ ሁኔታ በመቁጠሪያ ጸሎት የምንማጸንበት ወር ነው የግንቦት ወር።

በዚህ የማርያም ወር በመባል በሚታወቀው የግንቦት ወር መጨረሻ ማክሰኞ እ.አ.አ ግንቦት 31/2022 ዓ.ም እንደ ሚጠናቀቅ የሚጠበቅ ሲሆን በዚህን የማርያም ወር በመባል የሚታወቀው የግንቦት ወር ማብቂያ ላይ  ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዩክሬን በተፈጠረው ግጭት እየተሰቃዩ እና አሁንም በመላው ዓለም እየተካሄዱ በሚገኙት ጦርነቶች፣ ዓመጾች ሰለባ እና ተጠቂ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንድትደርሳልቸው እና ለዓለም የተስፋ ምልክት ለመስጠት እንደ ሚፈልጉ ቅዱስነታቸው ካስተላለፉት መልእክት ለመረዳት ተችሏል።

እ.አ.አ በመጪው ማክሰኞ ግንቦት 31/2022 ዓ.ም  በኢትዮጲያ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በሮም ከተማ እንብርት ላይ በምትገኘው ቀዳማዊቷ የቅድስት ማርያም ባሲሊካ በመገኘት ጸሎቱን እንደ ሚመሩ ይጠበቃል።

"በየትኛውም የአለም ክፍል ያሉ ምእመናን ሁሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለሰላም ንግሥት በሚያቀርቡት ጸሎት እንዲሳተፉ ተጋብዘዋል" ሲል መግለጫው አበረታቷል። በስነ ስረዓቱ ላይ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን ጸሎት ለመደገፍ ምእመናንን የሚወክሉ የተለያዩ ሰዎች ይገኛሉ።

በቅርብ ሳምንታት ውስጥ የመጀመሪያ ምስጢረ ቁርባን እና ምስጢረ መሮን የተቀበሉ ወንዶች እና ሴት ልጆች ፣ ስካውቶች ፣ የዩክሬን የሮማ ማህበረሰብ ቤተሰቦች ፣ በማርያም ስም የተቋቋሙ የተለያዩ ማሕበራት አባላት ተወካዮች፣ የቫቲካን ጄንዳርሜሪ ኮርፕስ አባላት እና የጳጳሳዊ የስዊዝ የክቡር ዘበኛ አባላት ከቅዱስነታቸው ጋር በመሆን ጸሎቱን ያሳርጉታል። በሮማ ከተማ ውስጥ በድንግል ማርያም የሰላም ንግሥት ስም የተሰየሙት ሦስቱ ደብሮች ከሮማውያን የተለያዩ የጳጳሳዊ ምክር ቤቶች አባላት ሳይቀሩ እንደ ሚሳተፉ ተገልጿል።

ሌላው አስፈላጊ ምልክት ከመላው ዓለም የተውጣጡ ዓለም አቀፍ ቤተመቅደሶች ተሳትፎ አሁንም በጦርነት በተጎዱ አገሮች ውስጥ ከሚገኙ አንዳንድ ቤተመቅደሶች ጋር ወይም በውስጣቸው ጠንካራ የፖለቲካ አለመረጋጋት ባለባቸው ለብዙ ሁከት ክስተቶች መንስኤዎች ሰላማዊ መፍትሄ ይገኝ ዘንድ ጸሎት ይደረጋል።

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ እና በማርያም ስም የተሰየሙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቤተ መቅደሶች ውስጥ የሚገኙ ምዕመናን ከቅዱስ አባታችን ጋር በተመሳሳይ ጊዜ እና ሰዓት የመቁጠሪያ ጸሎት እንደ ሚሳተፉ እና ከሮም ከተማ በቀጥታ የሚተላለፈውን ዝግጅት በቴለቪዢን በመከታተል ጸሎት ያደርጋሉ።

ከጳጳሱ ጋር የሚገናኙት እነዚህ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቤተ መቅደሶች በዩክሬን ውስጥ የሚገኘውን ማርያም የእግዚአብሔር እናት ቤተ መቅደስን ጨምሮ፣ በኢራቅ ውስጥ የሳይዳይት አል-ናጃት (የድነት እመቤታችን) ካቴድራል፣ በሶርያ የሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል፣ በባህሬን የሚገኘው የአረብ ንግሥት ማርያም ካቴድራል በዚህ ዝግጅት ላይ በቀጥታ መስመር በመሳተፍ ጸሎት እንደ ሚያደርጉ ይጠበቃል።  

27 May 2022, 13:53