ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ   (ANSA)

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ እውነተኛ ፍቅር መውደድ እንችል ዘንድ ነፃነትን ይሰጠናል እንጂ አያደናቅፈንም ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው አስተንትኖ እንደሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በግንቦት 21/2014 ዓ.ም ያደረጉት አስተንትኖ በእለቱ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የተከበረውን እና ኢየሱስ በዚህ ምድር የነበረውን ቆይታ አጠናቆ ለሐዋርያቱ ሚስዮናዊ አገልግሎቱን ያስቀጥሉ ዘንድ ባርኳቸው እና መንፈስ ቅዱስን እንደ ሚልክላቸው ቃል ከገባላቸው በኋላ ወደ ሰማይ መውጣቱ የሚከበርበት የዕርገት በዓል ላይ ትኩረቱን ያደርገ አስተንትኖ ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን እውነተኛ ፍቅር መውደድ እንችል ዘንድ ነፃነትን ይሰጠናል እንጂ አያደናቅፈንም ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በእለቱ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል

እንዲህም አላቸው፤ “ ‘እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤ ክርስቶስ መከራን ይቀበላል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፤ ከኢየሩሳሌም ጀምሮ ለሕዝቦች ሁሉ ንስሓና የኀጢአት ስርየት በስሙ ይሰበካል፤’ እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። እኔም አባቴ የሰጠውን ተስፋ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኀይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቈዩ።” ከዚህ በኋላ እስከ ቢታንያ ይዞአቸው ወጣ፤ እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። እየባረካቸውም ሳለ፣ ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ሰማይ ዐረገ። እነርሱም ሰገዱለት፤ በታላቅ ደስታም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ዘወትር በቤተ መቅደስ ነበሩ። (ሉቃስ 24:46-53).

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእለቱ ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ዛሬ በጣሊያን እና በብዙ አገሮች የጌታ ዕርገት ማለትም ወደ አብ መመለሱ የሚከርበት በዓል በማክበር ላይ እንገኛለን። በስርዓተ አምልኮ ደንብ መሰረት ከሉቃስ ወንጌል ላይ ተወስዶ የተነበበው ስለ ትንሣኤው ክርስቶስ የመጨረሻ መገለጥ ለደቀ መዛሙርቱ ይተርካል (ሉቃስ 24፡46-53)። የኢየሱስ ምድራዊውን ሕይወት የሚያጠናቅቀው በዕርገት ሲሆን እኛም በጸሎተ ሐይማኖት መግለጫው ውስጥ “ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ተቀመጠ” ብለን እንመሰክራለን። ይህ ክስተት ምን ማለት ነው? እንዴት ነው መተርጎም ያለብን? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ፣ ኢየሱስ ወደ መንግሥተ ሰማይ ከማረጉ በፊት ባደረጋቸው ሁለት ድርጊቶች ላይ እናተኩር፡ በመጀመሪያ የመንፈስን ስጦታ ያውጃል፣ ከዚያም ደቀ መዛሙርቱን ይባርካል።

በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስ ለወዳጆቹ፡- “እኔም አባቴ የሰጠውን ተስፋ እልክላችኋለሁ” (ሉቃስ 24፡49) አላቸው። እሱ የሚናገረው ስለ መንፈስ ቅዱስ፣ አጽናኝ፣ እሱም አብረዋቸው ስለሚሄድ፣ ስለሚመራቸው፣ በተልዕኳቸው እንደሚረዳቸው እና በመንፈሳዊ ውጊያዎች ስለሚሟገትላቸው ነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ብቻቸውን አይተዋቸውም የሚል አንድ አስፈላጊ ነገር እንረዳለን። ወደ መንግሥተ ሰማያት ይወጣል፣ ነገር ግን ብቻቸውን አይተዋቸውም። ይልቁንም በትክክል ወደ አብ በመውጣት፣ የመንፈሱን መፍሰስ ያረጋግጣል። በሌላ ጊዜ “እኔ ብሄድ ይሻላችኋልና፣ እኔ ካልሄድኩ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣም” (ዮሐ 16፡7) ይላቸዋል። በዚህ ውስጥ ደግሞ ኢየሱስ ለእኛ ያለውን ፍቅር እናያለን፣ ነፃነታችንን ሊገድብ የማይፈልግ መገኘት ነው። በተቃራኒው ግን ቦታን ይተወናል ምክንያቱም እውነተኛ ፍቅር ሁል ጊዜ መቀራረብን ይፈጥራል እንጂ ተቃራኒ እንድንሆን አያደርገንም። በዚህ መንገድ ክርስቶስ እንዲህ ሲል አረጋግጧል፣ “ወደ አብ እሄዳለሁ፣ እናንተም ከላይ የሚመጣውን ኃይል ትለብሳላችሁ፣ መንፈሴን እልክላችኋለሁ፣ ከኃይሉም ጋር፣ በዓለም ላይ ሥራዬን ትቀጥላላችሁ!” (ሉቃስ 24፡49)። እናም ወደ መንግሥተ ሰማያት በመውጣት፣ ኢየሱስ ከአካሉ ጋር ከጥቂት ሰዎች ጋር ከመቀመጥ ይልቅ፣ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ከሁሉም ጋር ይቀራረባል። መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን ከጊዜ እና ከቦታ አጥር በላይ በእኛ ውስጥ እንዲገኝ አድርጎ በአለም ላይ ምስክሮቹ እንድንሆን አድርጎናል።

ከዚያ በኋላ - ሁለተኛው ተግባር ነው - ክርስቶስ እጆቹን ወደ ላይ አንስቶ ሐዋርያትን ባረካቸው (ሉቃስ 24፡50) የሚለው ነው። የክህነት ምልክት ነው። እግዚአብሔር፣ ከአሮን ዘመን ጀምሮ፣ ሕዝቡን የመባረክን ሥራ ለካህናቱ አደራ ሰጥቶ ነበር (ዘኁ. 6፡36)። ቅዱስ ወንጌል ኢየሱስ የሕይወታችን ታላቅ ካህን እንደሆነ ሊነግረን ይፈልጋል። ኢየሱስ ስለ እኛ ሊማልድ፣ ሰብዓዊነታችንን ለእርሱ ለማቅረብ ወደ አብ አረገ። ስለዚህ በአብ ፊት፣ ከኢየሱስ ሰብአዊነት ጋር፣ ሕይወታችን፣ ተስፋችን፣ ቁስላችን አለ በእዚያም ይኖራል። ስለዚህ ወደ መንግሥተ ሰማያት “መውጣቱ” ክርስቶስ ለእኛ “መንገድን ያዘጋጃል”፣ ለእኛ ቦታ ሊያዘጋጅልን ሄዶ፣ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ፣ ስለእኛ ይማልዳል፣ ስለዚህም ሁልጊዜ እንድንታጀብ እና በአብ እንድንባርክ ያደርጋል።

ወንድሞች እና እህቶች፣ የወንጌል ምስክሮች እንድንሆን ከኢየሱስ የተቀበልነውን የመንፈስ ስጦታ ዛሬ እናስብ። ምን እንደሆንን እራሳችንን እንጠይቅ፤ እና ደግሞ ሌሎችን መውደድ ከቻልን፣ ነፃነታቸውን ትተን ለእነሱ ቦታ መስጠት እንችላለን ወይ ብለን ራሳችንን እንጠይቅ። እናም ከዚያ በኋላ እራሳችንን ለሌሎች አማላጅ ማድረግ እንደምንችል እናውቃለን፣ ማለትም ለእነሱ እንዴት መጸለይ እና ህይወታቸውን እንደምንባርክ እናውቃለን? ወይስ ሌሎችን የምናገለግለው ለጥቅማችን ነው? ይህንን እንማር፣ የምልጃ ጸሎት፣ ስለ ዓለም ተስፋና መከራ መማለድ፣ ስለ ሰላም መጸለይ ተገቢ ነው። እናም በየቀኑ የምናገኛቸውን በአይኖቻችን እና በቃላችን እንባርካቸው!

እንግዲህ ከሴቶች መካከል የተባረከችው ወደ እመቤታችን በመጸለይ በመንፈስ ቅዱስም ተሞልታ ዘወትር ስለእኛ የምትጸልይና የምትማልድ ስለሆነች እርሷን እንማጸናት ። 

29 May 2022, 11:32