ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የቅድስና መንገድ “ቀላል” ነው፣ ኢየሱስን በሌሎች ውስጥ ማየትን ይጠይቃል አሉ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በግንቦት 07/2014 ዓ.ም ዐሥር አዳዲስ ቅዱሳንን ማወጃቸው እና ማዕረገ ቅድስና መስጠታቸው የተገለጸ ሲሆን በወቅቱ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ በተከናወነው ሥርዓተ አምልኮ መጀመሪያ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አሥር አዳዲስ ቅዱሳንን ማወጃቸው ተገልጿል። እነዚህ አዳዲስ ቅዱሳን ቅዱስ ቲቶ ብራንድስ፣ ቅዱስ አላዓዛር ዴቫሻያም፣ ቅዱስ ቼዛር ደ ቡስ፣ ቅዱስ ሉዊጂ ማሪያ ፓላዞሎ፣ ቅዱስ ጁስቲኖ ማሪያ ሩሶሊሎ፣ ቅዱስ ቻርለስ ደ ፎኩውል፣ ቅድስት ማሪያ ሪቪየር፣ ቅድስት የኢየሱስ ሩባቶ ማሪያ ፍራንቼስካ፣ ቅድስት የኢየሱስ ሳንቶካናሌ ማሪያ፣ ቅድስት ማሪያ ዶሜኒካ ማንቶቫኒ መሆናቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በወቅቱ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ በተከናወነው የሥርዓተ አምልኮ ሥነ  ሥረዓት ላይ ከ50 ሺህ በላይ መዕመናን መታደማቸው የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት የቅድስና መንገድ ቀላል ነው፣ ኢየሱስን በሌሎች ውስጥ ማየትን ይጠይቃል ማለታቸው ተገልጿል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደርጉትን ስብከት ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።  

ኢየሱስ በዚህ ዓለም የነበረውን ቆይታ ጨርሶ ወደ አብ ከመመለሱ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸውን ቃላት ሰምተናል። ክርስቲያን መሆን ምን ማለት እንደሆነ ነግሮናል፡- “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” (ዮሐ. 13፡34) በማለት ገልጾልናል። በእውነት ደቀ መዛሙርቱ መሆናችንን ወይም አለመሆናችንን የምንረዳበት የመጨረሻው መመዘኛ ክርስቶስ የሰጠን ውርስ ይህ ነው። የፍቅር ትእዛዝ ነው። የዚህን ትእዛዝ ሁለት አስፈላጊ ነገሮች እንመልከት፡ ኢየሱስ ለእኛ ያለውን ፍቅር - “እኔ እንደወደድኳችሁ” - እና ለሌሎች እንድናሳይ የሚጠይቀን ፍቅር - “እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” የሚሉትን ሁለት ሐረጎች እናገኛለን።

በመጀመሪያ "እኔ እንደወደድኳችሁ" የሚሉትን ቃላት እናገኛለን። ኢየሱስ እኛን የወደደን እንዴት ነው? እስከ መጨረሻው ድረስ እራሱን ስጦታ አድርጎ እስከ መስጠት ድረስ ነው የሚወደን። ራሱን አጠቃላይ ስጦታ አድርጎ በማቅረብ ነው የሚወደን። በላይኛው ክፍል ውስጥ ያለው ድባብ በጥልቅ ስሜት እና ጭንቀት ውስጥ በነበረበት በዚያ ጨለማ ሌሊት እነዚህን ቃላት መናገሩ አስገራሚ ነው፣ መምህሩ ደቀ መዛሙርቱን ሊሰናበታቸው ስለ ነበር ጥልቅ ስሜት ውስጥ ገብቶ ነበር፣ ከመካከላቸው አንዱ አሳልፎ እንደሚሰጠው ተናግሮ ነበርና ተጨነቀ። የኢየሱስን ልብ የሞላውን ሀዘን፣ በሐዋርያት ልብ ውስጥ የተከማቸ ጨለማ ደመና፣ እና ይሁዳ በመምህሩ ወጪቱ ያጠቀሰውን ቁራሽ ከተቀበለ በኋላ ክፍሉን ለቆ ወደ ውስጥ ሲገባ ሲያዩ ምን ያህል እንዳሳዘኑት መገመት እንችላለን። የክህደት ምሽት ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ክህደት በተፈፀመበት ወቅት ለእነርሱ ያለውን ፍቅር በድጋሚ አረጋግጧል። በህይወት ጨለማ እና አውሎ ነፋሶች መካከል፣ ያ ከሁሉም በላይ አስፈላጊው ነገር ነው፣ እግዚአብሔር ይወደናል።

ወንድሞች እና እህቶች፣ ይህ መልእክት የእምነታችን አስኳል እና እምነታችንን የምንገልጽበት መንገድ ይሁን፡- “...እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም” (1ኛ ዮሐ 4፡10)። ይህንን መቼም አንርሳ። የእኛ ችሎታዎች እና ጥቅሞቻችን ዋናዎቹ ነገሮች አይደሉም፣ ይልቁንም ቅድመ ሁኔታ የሌለው፣ ነጻ እና ያልተገባ የእግዚአብሔር ፍቅር ናቸው። ክርስቲያናዊ ሕይወታችን የሚጀምረው በትምህርትና በመልካም ሥራ ሳይሆን ከእኛ ምንም ዓይነት ምላሽ በፊት መወደዳችንን በመገንዘብ ከመደነቅ ነው። ዓለም ብዙ ጊዜ ዋጋ የምንሰጠው ለማምረት በምንችለው ነገር ብቻ እንደሆነ ሊያሳምነን ቢሞክርም፣ ወንጌሉ የሕይወትን እውነተኛ ገጽታ ያስታውሰናል፡ ተወደናል። በዘመኑ ይኖሩ የነበሩ መንፈሳዊ ጸሐፊዎች “ማንም ሰው ሳያየን ከረጅም ጊዜ በፊት በአምላክ አፍቃሪ ዓይኖች ታይተናል። ማልቀስ ወይም መሳቅን ምንም ከመስማታችን በፊት ሁላችንም ጆሮ የሆነው አምላካችን ሰምተናል። ማንንም ሰው በዚህ ዓለም ከማናገራችን በፊት ከረጅም ጊዜ በፊት፣ በዘላለማዊ ፍቅር ድምጽ ተነጋግረን ነበር። መጀመሪያ ወደደን፣ እሱ ይጠብቀናል፤ ይወደናል። ማንነታችን ይህ ነው፡ እኛ በእግዚአብሔር የተወደድን ነን። ኃይላችን ይህ ነው፤ በእግዚአብሔር የተወደድን ነን።

ይህንን እውነት መቀበል ስለ ቅድስና ብዙ ጊዜ በምናስበው መንገድ መለወጥን ይጠይቃል። አንዳንድ ጊዜ መልካም ስራዎችን ለመስራት የምናደርገውን ጥረት በማጉላት በራሳችን፣ በጀግኖቻችን፣ በደካማ አቅማችን እና ለሽልማት ለመስዋዕትነት ዝግጁ መሆናችንን መሰረት በማድረግ ከመጠን ያለፈ የቅድስና ሃሳብ ፈጠርን። ይህ አንዳንድ ጊዜ ከልክ ያለፈ ሕይወትን እና ቅድስናን የመመልከት መንገድ ሆኖ ሊታይ ይችላል። ቅድስናን ወደ ማይደረስ ግብ ቀይረነዋል። ከዕለት ተዕለት ኑሮው ለይተነዋል፣ በዕለት ተዕለት ተግባራችን፣ በጎዳናዎች አቧራ ውስጥ፣ በእውነተኛ ህይወት ፈተናዎች ውስጥ፣ እና የአቪላዋ ቴሬዛ ለእህቶቿ በተናገረችው ቃል፣ “ከማሰሮ እና ከድስቶቹ መካከል" በማለት ትናገር ነበር ቅድስና እለታዊ ተግባራትን የሚመለከት ነው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መሆን እና ወደ ቅድስና ጎዳና መራመድ ማለት በመጀመሪያ እና ከሁሉም በላይ ራሳችንን በእግዚአብሔር ፍቅር ኃይል መለወጥ ማለት ነው። የእግዚአብሔርን ከራስ በላይ፣ የመንፈስን በሥጋ ላይ፣ ጸጋን፣ ከመጠን ያለፈ ሥራን ፈጽሞ አንርሳ። እኛ አንዳንድ ጊዜ ለራስ፣ ለሥጋ እና ለሥራ የበለጠ ቦታ እንሰጣለንና። አይደለም፣ ቀዳሚው ከራሳችን በፊት ለእግዚአብሔር፣ መንፈስ በሥጋ ላይ፣ ጸጋ ከመጠን ካለፈ ሥራ በላይ ነው።

ከጌታ የምንቀበለው ፍቅር ሕይወታችንን የሚቀይር ኃይል ነው። ልባችንን ይከፍታል እና እንድንወድ ያስችለናል። በዚህ ምክንያት ኢየሱስ እንደ ተናገረው ሁለተኛው አካል ይህ ነው - "እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም ደግሞ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ" የሚለው ነው። “እንደ” የሚለው ቃል የኢየሱስን ፍቅር እንድንመስል የቀረበልን ግብዣ ብቻ አይደለም። እርሱ ስለወደደን ብቻ መውደድ እንደምንችል ይነግረናል ምክንያቱም መንፈሱን፣ የቅድስና መንፈስ፣ የሚፈውስና የሚቀይር ፍቅሩን በልባችን ስላፈሰሰ ነው። በውጤቱም በሁሉም ሁኔታ እና ለምናገኛቸው ወንድም እና እህቶች ውሳኔ ማድረግ እና የፍቅር ስራዎችን ማከናወን እንችላለን ምክንያቱም ስለ ተወደደን እና የመውደድ ኃይል ስላለን ነው። እንደተወደድኩ ሌሎችን መውደድ እችላለሁ። የምሰጠው ፍቅር ኢየሱስ ለእኔ ካለው ፍቅር ጋር አንድ ነው። እሱ እንደወደደኝ እኔም ሌሎችን መውደድ እችላለሁ። የክርስትና ሕይወት እንዲሁ ቀላል ነው። በብዙ ነገሮች የበለጠ የተወሳሰበ አናድርገው፣ ነገሩ በጣም ቀላል ነው።

በተግባር ይህን ፍቅር መኖር ማለት ምን ማለት ነው? ኢየሱስ ይህን ትእዛዝ ከመስጠቱ በፊት የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቦ ነበር፣ ከዚያም ከሰጠ በኋላ ራሱን ለመስቀል እንጨት አሳልፎ ሰጠ። መውደድ ማለት ይህ ነው፣ ማገልገል እና ህይወት መስጠት ማለት ነው። ለማገልገል ማለትም ጥቅማችንን ላለማስቀደም፣ ስርዓቶቻችንን ከስግብግብነት እና ከተፎካካሪነት መርዝ ማፅዳት፣ የግዴለሽነት ካንሰር እና ራስን የማመሳከሪያ ትልን በመዋጋት፣ እግዚአብሔር የሰጠንን ጸጋዎች እና ስጦታዎች በመካፈል ይህንን ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን። በተለይ “ለሌሎች ምን አደርጋለሁ?” ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን። መውደድ ማለት ይህ ነው የእለት ተእለት ህይወታችንን በአገልግሎት መንፈስ፣ በማይታመን ፍቅር እና ምንም ዓይነት ዋጋ ሳንፈልግ መመላለስ ማለት ነው።

ከዚያም ሕይወትን አሳልፎ መስጠት። ይህ በቀላሉ የእኛን ነገር ለሌሎች ከማቅረብ የበለጠ ነው፣ ለእነርሱ ራሳችንን ስለመስጠት ነው። ምጽዋት መስጠት አለብን ወይ በማለት ምክሬን ለሚሹ ሰዎች አንድ ነገር ለመጠየቅ እወዳለሁ። እናም ቢያደርጉ የተቀባዩን እጅ በመንካት ነው ወይ ወይም በቀላሉ ምጽዋቱን ጥዬ ነው የምሄደው? እነዚያ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ያፍራሉ እና አይሆንም ይላሉ። እናም ምጽዋት በሚሰጡበት ጊዜ ሰውየውን አይን ያዩታል ወይስ ሌላ ይመለከቱ እንደሆነ እጠይቃለሁ። በወንድሞቻችን እና በእህቶቻችን ላይ የሚሠቃየውን የክርስቶስን ሥጋ በመንካት እና በመመልከት በመዳሰስ እና በመመልከት የምናደርገውን ተግባር ማከናወን ይኖርብናል። ይህ በጣም አስፈላጊ ነው፣ ነፍስን መስጠት ማለት ይህ ነው።

ቅድስና ጥቂት የጀግንነት ምልክቶችን ሳይሆን ብዙ ትናንሽ የዕለት ተዕለት የፍቅር ተግባራትን ያቀፈ ነው። ወደ ተቀደሰው ሕይወት ተጠርተሃል? ዛሬ ብዙዎቻችሁ እዚህ ናችሁ! እንግዲያውስ ቃል ኪዳናችሁን  በደስታ በመኖር ቅዱሳን ሁኑ። አግብተሃል? ክርስቶስ ለቤተክርስቲያን እንዳደረገው ባልህን ወይም ሚስትህን በመውደድ እና በመንከባከብ ቅዱሳን ሁኑ። ለኑሮ ትሰራለህ? ለወንድሞቻችሁና ለእህቶቻችሁ በታማኝነት በማገልገል፣ ለጓደኞቻችሁ ለፍትህ በመታገል ሁል ጊዜ ትክክለኛ ደመወዝ እንዲቀበሉ ከስራ ውጭ እንዳይቀሩ በመሥራት ቅዱሳን ሁኑ። እርስዎ ወላጅ ወይም አያት ነዎት? ኢየሱስን እንዲከተሉ ትንንሽ ልጆችን በትዕግሥት በማስተማር ቅዱሳን ሁኑ። ንገረኝ፣ በስልጣን ላይ ነህ? በሥልጣን ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች ዛሬ እዚህ አሉ! ከዚያም ለጋራ ጥቅም በመስራትና የግል ጥቅምን በመካድ ቅዱሳን ሁኑ። ይህ የቅድስና መንገድ ነው፣ እና በጣም ቀላል ነው! ኢየሱስን ሁልጊዜ በሌሎች ውስጥ ለማየት ሞክሩ።

ወንጌልን፣ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ለማገልገል፣ በምላሹ ምንም ዓይነት ነገር ሳንጠብቅ ምንም ዓይነት ዓለማዊ ክብር ሳንጠብቅ ህይወታችንን ለሌሎች ለማቅረብ ዝግጁ ነን ወይ? ይህ ሚስጥር ነው ጥሪያችንም ነው። ዛሬ ወገኖቻችን ቅድስናቸውን የኖሩት በዚህ መልኩ ነበር። ጥሪአቸውን በጉጉት ተቀብለው - እንደ ካህን፣ የተቀደሰች ሴት፣ ምእመን - ሕይወታቸውን ለወንጌል አሳልፈው ሰጥተዋል። ወደር የማይገኝለት ደስታን አግኝተዋል እናም የታሪክ ጌታ ብሩህ ነጸብራቅ ሆኑ። ቅዱሳን ማለት ያ ነው፡ የታሪክ ጌታ ብሩህ ነጸብራቅ መሆን ማለት ነው። እኛም እንዲሁ ለማድረግ እንትጋ። የቅድስና መንገድ አልተከለከለም፣ ዓለም አቀፋዊ ነው እና በጥምቀት ይጀምራል። እሱን ለመከተል እንትጋ፣ እያንዳንዳችን ወደ ቅድስና፣ የሁላችንም የቅድስና መልክ ተጠርተናልና። ቅድስና ሁል ጊዜ “ኦሪጂናል” ነው፣ ብፁዕ ካርሎ ኩቲስ እንደሚሉት፡ ፎቶ ኮፒ አይደለም፣ ግን “ኦሪጅናል”፣ የእኔ፣ የእናንተ፣ የሁላችንም ነው። በልዩ ሁኔታ የራሳችን ነው። በእውነት ጌታ ለሁሉም ሰው የፍቅር እቅድ አለው። ለህይወትህ፣ ለኔ ህይወት፣ ለእያንዳንዳችን ህይወት ህልም አለው። ሌላ ምን ማለት እችላለሁ? ያንን ህልም በደስታ ተከታተል።

15 May 2022, 12:15