ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የዩክሬን ሕዝብ ለቅሶን እና ስቃይ እንደሚጋሩ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እሑድ ሚያዝያ 23/2014 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ጋር ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት፣ በምስራቅ አውሮፓ አገር ዩክሬን ውስጥ ሕዝቡ የሚያሰማውን ለቅሶ እና የሚደርስበትንም ስቃይ የሚጋሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዩክሬን ውስጥ ሕጻናት መኖሪያ አካባቢያቸውን ለቅቀው እንዲወጡ ሲገደዱ እና ሲባረሩ የሚገልጽ ዜና እንደደረሳቸው ቅዱስነታቸው ገልጸው፣ ጭንቀት ውስጥ ከሚገኙ በርካታ ሰዎች ጋር ሆነው፣  “በእርግጥ በዩክሬን ውስጥ ሰላምን ለማውረድ ጥረት እየተደረገ ነው ወይ?" በማለት ጠይቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በትናንትናው ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር ሆነው ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት ጸሎት ካቀረቡ በኋላ፣ በጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር መሠረት እሑድ በገባው የግንቦት ወር በሙሉ ምዕመናን በየቀኑ ሰላምን በመማጸን የመቁጠሪያ ጸሎት እንዲደግሙ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ የጸሎት ጥሪያቸው፣ በዩክሬን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተማ ማሪዩፖል በከባድ ጦር መሣሪያ መውደሟንም አስታውሰዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በአደባባዩ ለተገኙት በሙሉ ባሰሙት ንግግር፣ ዛሬም በድጋሚ በጦርነት መከራ ውስጥ ለሚገኝ ማርዩፖል ሕዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚደርስበት መስመር እንዲመቻች ጠይቀዋል። የዩክሬን ሕዝብ ልቅሶ እና ስቃይ እንደሚጋሩ፣ በተለይም የአቅመ ደካሞችን፣ የአረጋውያንን እና የሕጻናትን ለቅሶ እና መከራ የሚጋሩ መሆናቸውን ገለጸዋል። ሕጻናት እየተባረሩ እና እየተሰደዱ መሆናቸውን የሚገልጽ አስከፊ ዜና መኖሩን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ይህን ለበርካታ ሳምንታት የዘለቀውን ጦርነት በማቆም ሰላምን ለማምጣት ፍላጎት ያለ እንደሆን፣ የጦር መሣሪያዎች ድምጽን ጸጥ ለማድረግ የተቻለ ሁሉ እየተደረገ ስለመሆኑ ጠይቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው መጨረሻ፣ ለአመጽ እና ለጦር መሣሪያ ጥቃት ዕድል መስጠት እንደማይገባ በማሳሰብ፣ ለጋራ ውይይት እና ለሰላም ሁኔታዎች እንዲመቻቹ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።   

02 May 2022, 17:29