ፈልግ

የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባኤ የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባኤ   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ዓለምን ባሰጋው በክፉ ጦርነት ወቅት ክርስቲያኖች ሊተባበሩ ይገባል አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት የተዘጋጀውን ጠቅላላ ጉባኤ የተካፈሉ አባላትን ሚያዝያ 26/2014 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባደረጉት ንግግር፣ ዓለም ጭካኔ በተሞላበት ጦርነት ስጋት ውስጥ በሚገኝበት ወቅት ክርስቲያኖች አንድ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበው፣ አረመኔያዊ የጦርነት ድርጊቶች በመጋፈጥ እና ለአንድነት ያለንን ፍላጎት በማደስ የጦር ሠራዊቱን ልብ በቅዱስ ወንጌል መልካም ዜና መቀየር ይኖርብናል ብለዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም፣ እ. አ. አ በ 2025 ዓ. ም. የሚከበረው የኢዮቤልዩ በዓል፣ ከመጀመሪያው የኒቂያ ጉባኤ 1700 ኛ ዓመት በዓል ጋር በመጣመር፣ ጠንካራ የክርስቲያኖች አንድነት ገጽታ እንደሚኖረው ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዩክሬን እየታካሄደ ያለው ጦርነት መላውን ዓለም እንዳሰጋ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ገልጸው፣ የክርስቲያኖች አንድነት ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱን አሳልፎ የሰጠበት መሆኑን የእያንዳንዱ ክርስቲያን እና አብያተ ክርስቲያን ኅሊና ተገንዝቦ፣ በጥፋት ተግባር ላይ የተሰማሩትን ልብ መቀየር የሚችል የቅዱስ ወንጌል መልካም ዜናን መመስከር ያስፈልጋል ብለዋል። ከክርስቲያኖች አንድነት ጳጳሳዊ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች ጋር መገናኘታቸው መልካም ዕድል እንደሆነ ቅዱስነታቸው ገልጸው፣ በልማድም ወይም በሽንፈት ምክንያት በክርስቲያኖች መካከል ያለውን ልዩነት ለመፍታት የሚደረገውን የጋራ ውይይት ችላ ማለት ልበ ደንዳናነት መሆኑን ታሪክ አስመስክሯል ብለዋል።

ወረርሽኙ የክርስቲያኖችን አንድነት ለማጠናከር ጥሩ አጋጣሚ ነው

ከጦርነቱ አስቀድሞ ዓለምን ያናጋውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በማኅበራዊ ሕይወት ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉን እና ባለፉት ሁለት ዓመታት አብያተ ክርስቲያናቱ በኅብረት ሆነው የሚያካሂዷቸው እንቅስቃሴዎች እውን እንዳይሆኑ በማገድ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን አስታውሰዋል። ወረርሽኙ በክርስቲያኖች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እና ለማደስ መልካም አጋጣሚ ሆኖ እንደተገኘ፣

ምክንያቱም ሁላችንም የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናችንን ከማደስ በተጨማሪ አቅመ ደካማነታችንን ተገንዝበን ከእግዚአብሔር ዘንድ በሚመጣልን ዕርዳታ ብቻ መተማመን እንደሚያስፈልግ አሳይቶናል ብለዋል።

“ፈጽሞ በተናጠል መጓዝ የለብንም”

የወንድማማችነትን ስሜት የሚገልጹ እና የሚያሳድጉ ተነሳሽነቶች ሊኖሩ እንደሚገባ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሳስበው፣ አንድ ክርስቲያን ከሚከተለው ቤተ ክርስቲያን ጋር ብቻ መጓዝ የማይቻል መሆኑን ገልጸው፣ አብያተ ክርስቲያናት አንድነታቸውን በተጨባጭ ካልገለጹ ወደፊት መጓዝ እንደማይቻላቸው እና  የክርስቲያኖች አንድነት ግንዛቤም አንድ ክርስቲያን ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ወንድሞች እና እህቶች ጋር የማይተባበር ከሆነ የእምነት ጉዞ ብቻው ማካሄድ እንደማይችል ያሳያል ብለዋል።

የእያንዳንዱን ክርስቲያን እና ቤተ ክርስቲያን ህሊና መጠየቅ

ወረርሽኙ ያስከተለው መዘዝ አሁንም እንዳለ ሆኖ ዓለም በሌላ አዲስ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኝ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት አስታውሰው፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በዓለማችን ውስጥ በልዩ ልዩ ክፍሎች ጦርነቶች ሳያቋርጡ መቀጠላቸውን ገልጸው፣ ለምሳሌ ከ25 ዓመታት በፊት በሩዋንዳ ውስጥ የእርስ በእርስ ጦርነት እንደነበር፣ በሚያንማርም እንደዚሁ ጦርነት መኖሩን ጠቅሰው፣ እነዚህ ጦርነቶች በቅርብ ማየት በማንችላቸው አካባቢዎች ቢካሄዱም ምላሽ ልንሰጣቸው ይገባል ብለዋል። ክልላዊ ጦርነቶች በየቦታው እንደሚካሄዱ በመገንዘብ ከዚህ በፊት ስለ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት መናገራቸውንም አስታውሰዋል።

የወንጌልን የሰላም ዜና ማወጅ

ባለፈው ምዕተ-ዓመት በክርስቲያኖች መካከል የተፈጠረው መለያየት ሐዘን እና የፍትሕ መጓደልን በማስከተል በዓለማችን ውስጥ ታሪካዊ ጫናን መፍጠሩ፣ ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱን አሳልፎ የሰጠበትን አንድነት እንዲመኙ ማድረጉን አስታውሰዋል። አክለውም፣ በዘመናችን እየታካሄደ ያለው አረመኔያዊ ጦርነት፣ የክርስቲያኖችን አንድነት እንደገና ማቀጣጠል እንዳለበት አሳስበዋል። ዓለም ጭካኔ በተሞላበት ክፉ ጦርነት ውስጥ በሚገኝበት ወቅት ክርስቲያኖች አንድ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበው፣ አረመኔያዊ የጦርነት ድርጊቶች በመጋፈጥ እና ለአንድነት ያለንን ፍላጎት በማደስ በጦርነት ላይ የሚገኙትን ወታደሮች ልብ በቅዱስ ወንጌል መልካም ዜና መቀየር ይኖርብናል ብለዋል።

የኒቂያ ጉባኤ ለክርስቲያኖች የጋራ ጉዞ ብርሃን ይሁን!

ሊከበር ዝግጅት እየተደረገለት የሚገኘው የኒቂያው ጉባኤ 1700 ኛ ዓመት በዓል ለክርስቲያኖች አንድነት ከፍተኛ አስተዋጽኦን እንደሚያበረክት ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፣ የኒቂያው ጉባኤ ቤተ ክርስቲያን በሲኖዶሳዊ ጉዞ በራሷ እምነት አንድነቷን ያረጋገጠችበት የእርቅ ጉባኤ እንደ ነበር፣ ለዛሬው የክርስቲያኖች የጋራ ጉዞ ብርሃን እንደሆነ አስረድተዋል። የኒቂያው ጉባኤ 1700 ኛ ዓመት በዓል፣ እ. አ. አ በ 2025 ዓ. ም. ከሚከበረው የኢዮቤልዩ በዓል ጋር መገጣጠሙ ለክርስቲያኖች አንድነት ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን አክለው አስረድተዋል።

ሲኖዶሳዊነት

የመጀመሪያው የክርስቲያኖች አንድነት ጉባኤ፣ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ሕይወት እና አደረጃጀት እንደሚገልጽ የተናገሩት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ለመላው ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ባቀረቡላቸው ግብዣ፣በመካሄድ ላይ የሚገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ ጉዞ የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ወንድሞች እና እህቶች ድምጽ ለማዳመጥ የተዘጋጁ እንዲሆኑ አሳስበው፣ በኅብረት ወደ ፊት መጓዝ እንደሚያስፈልግ፣ በሥነ-መለኮታዊ ርዕሠ ጉዳዮችን ማሰላሰል አስፈላጊ ቢሆንም፣ በአንድነት ጉዞ ወቅት የሥነ-መለኮት ጠበብት ስምምነቶችን መጠበቅ አንችልም ብለዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፣ እንደ ወንድማማቾች በአንድነት መጸለይ፣ በበጎ አድራጎት ሥራዎች እና በእውነትን ፍለጋ መተባበር እንደሚያፈልግ ገልጸው፣ ወንድማማችነት በጋራ የተሰጠን የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን፣ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት የተዘጋጀውን ጠቅላላ ጉባኤ ለተካፈሉት አባላት አስረድተዋል። 

07 May 2022, 16:44