ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከሠራተኞች ጋር ሲገናኙ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከሠራተኞች ጋር ሲገናኙ   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ሥራ በዓለማችን የሁሉን ሰው ክብር እንዲያስጠብቅ ጠየቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት ጸሎት ካቀረቡ በኋላ ንግግር አድርገዋል። ቅዱስነታቸው ለምዕመናኑ ባቀረቡት ንግግር ቅዳሜ ሚያዝያ 22/2014 ዓ. ም. በሰሜን ጣሊያን፣ ሚላን ከተማ ሁለት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የነበሩ፣ የአባ መርዮ ቺቼሪ እና የእህት አርሚዳ ባሬሊ ብጽዕና የታወጀበት ዕለት መሆኑን አስታውሰዋል። አባ ማርዮ ቺቼሪ በጸሎት እና በንስሐ የሚተጉ፣ ሕሙማንን የሚጎብኙ እና ሕጻናትን በማስተማር እና በመምከር ወደ መልካም መንገድ በመምራት የሚታወቁ ተጠቃሽ ሐዋርያ እንደነበሩ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አርሚዳ ባሬሊ የሴት ወጣቶች ካቶሊካዊ ተግባር ማሕበር መስራች እና አንቀሳቃሽ እንደነበረች ገልጸው፣ በጣሊያን ውስጥ በሚገኙ ክፍለ ሀገራት በመዘዋወር መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችን ታስተባብር  እንደነበር፣ የሴቶች ማኅበርን እና የቅዱስ ልበ ኢየሱስ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲን ለማቋቋም ከአባ ጀሜሊ ጋር መተባበሯንም ገልጸው፣ ሚያዝያ 22 “ከሴቶች ልብ ጋር” በሚል መሪ ቃል ዓመታዊ በዓል የሚከበርበት ዕለት መሆኑንም አስታውሰዋል።

የጎርጎሮሳውያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ ምዕመናን ዘንድ እሑድ 23/2014 ዓ. ም. እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የምትከብርበት እና የምትወደስበት ግንቦት ወር መጀመሪያ መሆኑን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ምዕመናን በሙሉ በግንቦት ወር ዘወትር የመቁጠሪያ ጸሎትን በመድገም ለሰላም እንዲጸልዩ አደራ ብለዋል። በዩክሬን ውስጥ የምትገኝ ማሪዩፖል ከተማን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የከተማዋ ባልደረባ እንደሆነች እና ከተማዋም በስሟ የምትጠራ መሆኗን አስታውሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ እሑድ ሚያዝያ 23/2014 ዓ. ም. የሠራተኞች ቀን መሆኑንም አስታውሰው፣ በሁሉም የዓለማችን አካባቢዎች እና በሁሉም ሰው ዘንድ ሥራ ሰብዓዊ ክብርን የሚያስጠብቅ እንዲሆን ጠይቀዋል። አክለውም ሥራ በኤኮኖሚው ዘርፍ ማኅበራዊ ዕድገትን የሚያስገኝ እና ሰላምንም የሚያረጋግጥ እንዲሆን ተመኝተው፣ ሥራ ላይ እያሉ ሕይወታቸውን ያጡትን በሙሉ በጸሎታቸው አስታውሰዋል። ማክሰኞ ሚያዝያ 25/2014 ዓ. ም. የዩኔስኮ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን መሆኑን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ይህን መብት ለማስከበር ሕይወታቸውን ለሚከፍሉ ጋዜጠኞች ያላቸውን ክብር ገልጸዋል። ባለፈው የፈረንጆቹ 2021 ዓ. ም. በዓለማችን ውስጥ 47 ጋዜጠኞች መሞታቸውን እና 350 የሚደርሱ መታሠራቸውን ገልጸው፣ አሁን በሥራ ገበታቸው ላይ ሆነው በዓለማችን በሰዎች የሚደርሰውን ቁስል በመዘገብ ላይ ለሚገኙት ልዩ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም ከሮም ከተማ እና አካባቢዋ፣ እንዲሁም ከተለያዩ የጣሊያን ሀገረ ስብከቶች ለመጡት ምዕመናን እና ነጋዲያን፣ ከስፔን፣ ከፖርቱጋል እና ከአሜሪካ ለመጡት ምዕመናን፣ ነጋዲያን እና ሀገር ጎብኝዎች በሙሉ ሰላምታቸውን እቅርበውላቸዋል። ከተለያዩ ሀገረ ስብከቶች እና ቁምስናዎች ለመጡ መንፈሳዊ ማኅበራት እና እንቅስቃሴ እባላት በሙሉ ሰላምታቸውን በማቅረብ፣ መልካም ዕለተ ሰንበትን ከተመኙላቸው በኋላ፣ ምዕመናኑ እንዲጸልዩላቸው በመጠየቅ ንግግራቸውን ደምድመዋል።       

02 May 2022, 17:35