ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በቻይና ለሚገኙ ሐዋርያዊ አገልጋዮች እና ምዕመናን እንደሚጸልዩላቸው ገለጹ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ግንቦት 14/2014 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት ጸሎት ካቀረቡ በኋላ ለምዕመናኑ ባሰሙት ንግግር፣ በፈረንሳይ ውስጥ ሊዮን ከተማ ከሰኞ ግንቦት 8 - 15/2014 ዓ. ም. ድረስ የተካሄደውን የእምነት ማስፋፊያ አገልግሎት ማኅበር ጉባኤን አስታውሰው፣ የማኅበሩ መሥራች የነበረች የፖሊን ጃሪኮ ብጽዕና እሑድ ግንቦት 14/2014 ዓ. ም. ይፋ መሆኑን ገልጸዋል። ይህች የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ፣ እ. አ. አ በ1800ዎቹ መጀመሪያ አጋማሽ የኖረች መሆኗን ገልጸው፣ በወቅቱ ለሚከሰቱ ለውጦች ትኩረት በመስጠት የቤተ ክርስቲያኗን ተልዕኮ ለማሳካት ሁለንተናዊ ራዕይ የነበራት መሆኑንም አስታውሰዋል። የእርሷ ምሳሌነት በመታገዝ፣ ወንጌልን በዓለም የማዳረስ ፍላጎት እንዲያድግ ተመኝተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ፣ ከእሑድ ግንቦት 14–21/2014 ዓ. ም. ድረስ የሚከበረውን የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” ሳምንት ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ለመጠበቅ እና ለመንከባከብ በኅብረት እንድንጥር የሚያደርገንን የምድራችንን ጩኸት የበለጠ በትኩረት ማዳመጥ እንደሚገባ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ አጋጣሚ የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” ሳምንትን ያስተባበረውን፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እና ዝግጅቱን ለሚሳተፉ በርካታ ድርጅቶች ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ምዕመናን በሙሉ በያሉበት ሳምንቱን እንዲያስቡት እና በሚቀርቡት ዝግጅቶች እንዲሳተፉ አደራ ብለዋል።

ማክሰኞ ግንቦት 16/2014 ዓ. ም. የክርስቲያኖች ረዳት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መታሰቢያ ቀን መሆኑን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ በተለይም በሻንጋይ ውስጥ በሚገኝ ሼሻን የእመቤታችን ቤተ መቅደስ እና በአገሪቱ በሚገኙ በርካታ ቤተ ክርስቲያናት እና በቤተሰብ ደረጃም ዕለቱ የሚከበር መሆኑን ገልጸዋል። ይህ መልካም አጋጣሚ በመንፈስ ከጎናቸው መሆኔን በድጋሚ እንዳረጋግጥላቸው እድል ይሰጠኛል ብለዋል። በመላዋ ቻይና ውስጥ በውስብስብ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ የታማኝ ሐዋርያዊ አገልጋዮች ሕይወትን በትኩረት እና በንቃት እንደሚከታተሉ ገልጸው፣ በየዕለቱ የሚጸልዩላቸው መሆኑን ተናግረዋል። በቻይና የምትገኝ ቤተ ክርስትያን በነጻነት እና በሰላም ከዓለም አቀፉዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር ውጤታማ ግንኙነት እንዲኖራት እና ወንጌልን የማወጅ ተልዕኮዋን ቀጥላ ለኅብረተሰቡ መንፈሳዊ እና ቁሳዊ እድገት ማምጣት እንድትችል ምዕመናን በጸሎት እንዲደግፏት አደራ ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚቀርብ የእኩለ ቀን የጋራ ጸሎት ለተሰበሰቡት ምዕመናን በሙሉ ባደረጉት ንግግር፣ ከሮም ከተማ እና አካባቢዋ፣ በጣሊያን ከሚገኙ ልዩ ልዩ ሀገረ ስብከቶች ለመጡት ምዕመናን እና ከውጭ አገራት በተለይ ከስፔን፣ ከፖርቱጋል፣ ከፈረንሳይ፣ ከቤልጂዬም፣ ከፖላንድ እና ከፖርቶ ሪኮ ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። ከኢኳዶር ለመጡት ካኅናት፣ ካጣሊያን ፍጃ ከተማ ለመጡት የኤማሁስ ማኅበረሰብ እና በጣሊያን ውስጥ ከኦስታ ክፍለ ሀገር ለመጡት የቅዱስ ፒዬር በጎ ፈቃደኞች ማህበር አባላት እና ከሌሎች የጣሊያን ከፍለ ሀገራት ለመጡት ወጣቶች በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በማከልም፣ “ሕይወትን እንምረጥ” በሚል ርዕስ በቀረበ ብሔራዊ ዝግጅት ላይ ለተሳተፉት በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበው፣ ሕይወትን በመምረጥ እና በማስተዋወቅ፣ በሕይወት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ባሳዩት ቁርጠኝነት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

በመጨረሻዎቹ ዓመታት በጋራ አስተሳሰብ ላይ ለውጥ መታየቱን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ዛሬ ሕይወትን ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ የማዋል፣ የመምራት፣ የመውለድ ወይም ያለ መውለድ ውሳኔ የግለሰብ ምርጫ ብቸኛ ውጤት እንደሆነ አስረድተው፣ ሕይወት የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን እንድናስታውስ፣ ሕይወት ዘወትር የተቀደሰ እና የማይጣስ ክብር እንዳለው በመገንዘብ ህሊናን ንጹህ ማድረግ እንደሚገባ በማሳሰብ፣  ምዕመናኑም በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው ከጠየቁ በኋላ መልካም ዕለተ ሰንበትን በመመኘት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

23 May 2022, 16:57