ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከአረጋውያን ጋር ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከአረጋውያን ጋር  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የአረጋውያን ጸሎት ዓለምን ሊለውጥ እንደሚችል ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለሁለተኛ ጊዜ የሚከበረውን የአረጋውያን እና የአያቶች ዓለም አቀፍ የጸሎት ቀን መልዕክታቸውን ይፋ አድርገዋል። ቅዱስነታቸው ግንቦት 2/2014 ዓ. ም ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ በተለያዩ ቀውሶች ጦርነቶች መካከል የአረጋውያን ጸሎት ዓለምን ሊለውጥ እንደሚችል አስረድተው፣ አረጋውያን ተስፋን ሳይቆርጡ በጸሎት እንዲተጉ አሳስበው፣ ዓለምን በጸሎት እና በርኅራኄ ለመለወጥ ታላቅ ኃይል ያላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“እርጅና መታደል ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ምንም እንኳን የማኅበረሰቡ ወይም የራሳችሁ ድክመቶች የዕድሜ ባለጠግነትን በሌላ አቅጣጫ እንዲያስቡ ሊፈታትን ቢችልም የዕድሜ ባለጠግነት በዋጋ ሊተመን የማይችል በመሆኑ እግዚአብሔር በተስፋ እንድትጸኑ ይፈልጋል” በማለት ዘንድሮ ሐምሌ 17/2014 ዓ. ም. ለሁለተኛ ጊዜ ለሚከበረው የአረጋውያን እና የአያቶች ዓለም አቀፍ የጸሎት ቀን መልዕክታቸውን ገልጸዋል።

ቤተ ክርስቲያን የአረጋውያን እና የአያቶች ዓለም አቀፍ የጸሎት ቀንን የምታከብረው የኢየሱስ ክርስቶስ አያቶች፣ ቅዱስ ኢያቄም እና ቅድስት ሐና ክብረ በዓል ሲቃረብ መሆኑ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “አረጋዊያን የሕይወት እና የእምነት ልምድን ለወጣቶች በማስተላለፍ በትውልዶች መካከል ትስስርን ይፈጥራሉ” በማለት ቀኑ በቤተ ክርስቲያን እ. አ. አ ከ2021 ዓ. ም. ጀምሮ እንዲከበር መወሰናቸው ይታወሳል።

ማኅበረሰቡ ለአረጋውያን የሚሰጥ ክብር አሳንሷል

በመዝ. 92:14 ላይ “ያን ጊዜ በለመለመ ሽምግልና ያፈራሉ፣ ደስተኞችም ሆነው ይኖራሉ።” ተብሎ የተጻፈውን ቅዱስነታቸው አስታውሰው፣ የዛሬ ዓለም ለአረጋዊያን የሚሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ ቢሆንም እኛ ኝ ለአረጋውያን ሊሰጥ የሚገባውን ክብር እና እንክብካቤን በተግባር መመስከር ያስፈልጋል ብለዋል። የዕድሜ ባለጸግነት በሽታ እየመሰላቸው ብዙ ሰዎች ወደ አረጋውያን መቅረብ እንደሚፈሩ ገልጸው፣ ከዚህም በተጨማሪ አረጋውያን ከቤት እንዳይወጡ በመደረጋቸው የተሰማቸውን በሐዘን ገልጸዋል። የሽምግልናን ዘመን በቀላሉ መገንዘብ እንደማይቻል የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ወጣትነትን በማክበር እርጅናን የምንጸየፍ ከሆነ ውጤት ማምጣት አንችልም ብለዋል።         

በተስፋ መጽናት ያስፈልጋል

ዳዊት በመዝሙሩ በተስፋ መጽናት እንዳለብን የተናገረውን የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፣ እግዚአብሔር በእያንዳንዱ የዕድሜ እርከን ውስጥ እንደሚገኝ በመግለጽ በተስፋ እንድንጸና አሳስበዋል። እግዚአብሔር በእርጅና ወቅትም ቢሆን የሕይወት ስጦታ እየሰጠን በክፉ እንዳንሸነፍ ይጠብቀናል ብለው፣  በእርሱ ከታመንን፣ እርሱን የምናመሰግንበትን ብርታት እናገኛለን ብለዋል። “እርጅና ኩነኔ ሳይሆን በረከት ነው!” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ እርጅና ከተፈጥሮአዊ የሰውነት ድካም የሚበልጥ እና የረጅም ሕይወት ስጦታ መሆኑን እንገነዘባለን ብለዋል።

እንዴት ንቁ መሆን እንደሚቻል

አረጋዊያን ቢሆኑም ዘወትር ንቁ ሆነው መኖር እንደሚቻል የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አንዳንድ ምክሮች አካፍለዋል። “ውስጣዊ ሕይወታችንን በትጋት የእግዚአብሔርን ቃል በማንበብ፣ በየቀኑ በመጸለይ፣ ምስጢረ ቁርባንን በመቀበል እና መስዋዕተ ቅዳሴን የመሳተፍ ልምድን ማሳደግ እንደሚገባ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ካለን ዝምድና በተጨማሪ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት ማዳበር፣ በመጀመሪያ ደረጃ ለቤተሰቦቻችን፣ ለልጆቻችን እና ለልጅ ልጆቻችን እንዲሁም ለድሆች እና ስቃይ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ከልብ በመቅረብ በፍቅር ስሜት ልንጨነቅላቸው እንደሚገባ እና በጸሎት መርዳት ይገባል” በማለት አሳስበዋል።

የአረጋዊያን ጸሎት ዓለምን ሊለውጠው ይችላል!

ዓለማችን በሐዘን፣ በአመጽ እና ስጋን በሚያሰቃይ በሽታ እና ወረርሽኝ ውስጥ እንደሚገኝ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ በተለይ ጦርነት የሰላም እና የዕድገት እንቅፋት እየሆነ ይገኛል ብለዋል። ባለፈው ክፍለ ዘመን የጦርነትን አስከፊነት የተለማመደው ትውልድ እያለቀ ባለበት በዚህ ወቅት ጦርነት ወደ አውሮፓ ተመልሶ መምጣቱ በአጋጣሚ አይደለም ብለው፣ በዓለማችን የሚከሰቱ ትላልቅ ቀውሶች ሰብዓዊ ቤተሰብን እና የጋራ መኖሪያ ምድራችንን አደጋ ላይ የሚጥሉት ለወረርሽኞች እና ሌሎች በምድራችን የተንሰራፋ የአመጽ ዓይነቶችን እውነታ እንዳንገነዘብ ሊያደርጉን ነው ብለዋል። ይህ ሁሉ የሚያመለክተው ጥልቅ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው ብለው፣ በመሆኑም አያቶች እና አረጋውያን የዘመናችንን ሰዎች፣ የራሳቸውን የልጅ ልጆቻቸውን በፍቅር እይታ የማስተማር ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል። አረጋውያን ሌሎችን በመንከባከብ በሰብአዊነት ያሳደጉ በመሆናቸው፣ እኛም በጣም የተቸገሩትን በትኩረት በመከታተል የሕይወት ጎዳናን የማስተማር ሃላፊነት አለብን ብለዋል። “አያቶቻችን በደረታቸው አቅፈውን፣ በጀርባቸው አዝለውን በጸሎት እና ሌሎች እንክብካቤዎችን በማድረግ  እንዳላሳደጉን ሁሉ፣ ዛሬ ሕጻናትን ጨምሮ በርካታ አረጋውያን ከጦርነት ስቃይ ለማምለጥ ስደት ላይ እንደሚገኙ አስታውሰው፣ በልባችን እንያዝ - ልክ እንደ ቅዱስ ዮሴፍ አፍቃሪ እና አሳቢ አባት፣ በዩክሬን ፣ በአፍጋኒስታን ፣ በደቡብ ሱዳን እና በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች የሚሰቃዩ አረጋውያንን እና ሕጻናትን በልባችን ማስታወስ ይገባል” ብለዋል።

10 May 2022, 18:18