ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ ዳግማዊ ጋር በቫቲካን ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ ዳግማዊ ጋር በቫቲካን ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበት  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ ከመቼውም በበለጠ አንድ የሚያደርገን መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት፣ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና በግብጽ የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መካከል ወንድማዊ ግንኙነት የተጀመረበትን ዘጠነኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ፣ ግንቦት 2/2014 ዓ. ም. ለብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ ዳግማዊ መልዕክት ልከዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ግንቦት 10፣ የሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች በመካከላቸው የጀመሩትን የወዳጅነት ቃል ኪዳን የሚያድሱበት ብቻ ሳይሆን፣ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ በተከሰተው ወረርሽኝ እና በጦርነት ምክንያት ለሚሰቃይ ሰብዓዊ ቤተሰብ መጽናናትን ከእግዚአብሔር ዘንድ በጋራ የሚለምኑበት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ተወዳጅ ወንድሜ” ላሏቸው ለብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ ዳግማዊ በላኩት መልዕክት በሁለቱ አብያተ ክርስቲያት መካከል ያሉ እውነታዎች በመመልከት "በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን የማያቋርጥ ወዳጅነት" የበለጠ ለማሳደግ የሚያገለግል ዕለት መሆኑን ገልጸዋል። በኅብረት ጉዞ ወቅት በዓይን ተገናኝተው ለመወያየት የበቁባቸውን ሁለት ጠቃሚ ቀናትን ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በሚቀጥለው ዓመት የሚያከብሩትን እና ሁለቱ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በቫቲካን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበትን ቀን አሥረኛ ዓመትን እና ሁለተኛው፣ እ. አ. አ በግንቦት ወር 1973 በቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እና በቀድሞ የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ሺኖዳ ሦስተኛ መካከል የጸደቀ ታሪካዊ የአንድነት ሰነድ 50ኛ ዓመትን አስታውሰዋል።

ሙሉ እና ግልጽ የኅብረት ጉዞ

የሐዋርያት፣ የቅዱስ ማርቆስ እና የቅዱስ ጴጥሮስ ሐዋርያዊ መንበራት “መንፈሳዊ ትስስርን” በመፍጠር አንድ መሆናቸውን በመግልጽ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የወዳጅነትን ትክክለኛ ትርጉም ለማስረዳት በዮሐ. 15:14 ላይ “እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ።” ተብሎ የተጻፈውን በመጥቀስ፣ ይህን መሠረት በማድረግ “ክርስቲያናዊ የወንድማማችነት ጉዟችንን መቀጠል እንችላለን” ብለዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም፣ “ወዳጅነት በክርስቲያኖች መካከል ያለውን አንድነት እውን ለማድረግ ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው” ብለው፣ በዚህም “ከእንግዲህ ወዲህ ወዳጆቼ እንጂ ባሮች አልላችሁም” ያለውን እና ሁሉም አንድ እንዲሆኑ የሚጸልየውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማየት እንችላለን ብለዋል። 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ለፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ታዋድሮስ ዳግማዊ በላኩት መልዕክት፣ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የማያቋርጥ መንፈሳዊ መቀራረብ መኖሩን አረጋግጠውላቸዋል። “በክርስቲያናዊ ሕይወት እና አስተምህሮው” ሁለቱንም አብያተ ክርስቲያናት በማበረታታት ወደ ሙሉ እና ተጨባጭ የኅብረት ጎዳና የሚመራውን የቅዱስ አጥናቴዎስ አማላጅነት በመለመን፣ መጭውን የጰንጠቆስጤ በዓል በመጠባበቅ ጸሎታቸውን ወደ መንፈስ ቅዱስ አቅርበው፣ መንፈስ ቅዱስ "ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አንድ ስለሚያደርግ፣ በመከራ እና ስቃይ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች በሙሉ፣ በተለይም በወረርሽኝ እና በጦርነት ለሚሰቃዩት የመጽናናት ስጦታን ይሰጣቸዋል" ብለዋል።

11 May 2022, 14:14