ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የጣሊያን ብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት በጎ ፈቃደኞችን በቫቲካን ተቀብለዋቸዋል ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የጣሊያን ብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት በጎ ፈቃደኞችን በቫቲካን ተቀብለዋቸዋል   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የሰዎች መልካም ተግባር ዓለምን የመገንባት ኃይል እንዳለው አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሰኞ ግንቦት 15/2014 ዓ. ም. ከጣሊያን ብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት በጎ ፈቃደኞች ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል። በጎ ፈቃደኞቹ ትርጉም የሌለውን ጦርነት ሸሽተው ወደ ጣሊያን ለሚመጡት የዩክሬን ስደተኞች በተለይም ሴቶችን እና ሕጻናትን ተቀብለው ለሚያደርጉላቸው ዕርዳታ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። “በስውር የሚደረግ መልካም ተግባር ዓለምን ይገነባል” ያሉት ር. ሊ. ፍራንችስኮስ፣ “በጭንቅ ውስጥ የሚገኝ ምድራችን ዋይታ የማናዳምጥ ከሆነ ተፈጥሮ በበኩሉ የጭካኔ ፊቱን ያሳየናል” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሰዎችን የሰላም ህልም የያናጋውን የዩክሬን ጦርነት የጠቀሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እ. አ. አ ጥቅምት 4/1965 ዓ. ም. በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ “ጦርነት መደገም የለበትም” ማለታቸውን ለጣሊያን ብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት በጎ ፈቃደኞች አስታውሰው፣ ትርፉ የሰው ሕይወት መጥፋት እና የንብረት መውደም ብቻ የሆነውን የዩክሬን ጦርነት ሸሽተው የሚሰደዱ ሰዎች ሁኔታን በመመልከት፣ “እያንዳንዱ ጦርነት የሰው ልጅ እራሱን የመከላከል አቅሙ መዳከሙን እና የተባበሩት መንግሥታት ውሎች ተቀባይነትን አለማግኘታቸውን ያመለክታል” ብለዋል።

“በስውር የሚደረግ መልካም ተግባር”


ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጋቢት 28/2014 ዓ. ም. ባቀረቡት የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን በድጋሚ ጥያቄ ውስጥ ያስገባ እና “ሕዝቦች ሰላምን የማግኘት ቅዱስ መብት” አስታውሰው፣ የጣሊያን ብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት በጎ ፈቃደኞች፣ በአገራቸው እየተካሄደ ያለውን ዋጋ ቢስ ጦርነት ሸሽተው የሚመጡ የዩክሬን ዜጎችን በተለይም አቅመ ደካሞችን፣ ሴቶችን እና ሕጻናትን ለመቀበል ላሳዩት ቁርጠኝነት፣ እስካሁን ላደረጉት እና በማድረግ ላይ ለሚገኙት መልካም ሰብዓዊ ዕርዳታ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸው፣ በስውር የተከናወነ መልካም ተግባር ዓለምን ሊገነባ እንደሚችል አስረድተዋል።

በወረርሽኙ ወቅት የተደረገ ዕርዳታ

የጣሊያን ብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ማኅበር በጎ ፈቃደኞች ተግባር፣ በጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉትን ተቀብሎ ማስተናገድ ብቻ ሳይሆን፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ችግር ውስጥ የወደቁትንም ጭምር መርዳት እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በዚህ መጠነ ሰፊ አገልግሎት፣ ችግር ውስጥ ለወደቀ የዕርዳታ እጁን የሚዘረጋ፣ ፈገግታን የሚያሳይ፣ ነጻ አገልግሎቱን የሚያበረክት እና በተፈናቃዩ ልብ የቤተኛነት ስሜት እንዲፈጠር የሚያደርግ ሰው ማግኘት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል። በወረርሽኙ ወቅት የተከናወኑ መልካም ተግባራትን ያወደሱት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ አቅመ ደካማ ቤተሰቦችን ከመርዳት ጀምሮ አረጋውያንን፣ ድሆችን እና የታመሙ ሰዎችን በመርዳት፣ በብቃት የተካሄደውን የክትባት መርሃ ግብርን ለመደገፍ የተደረጉ ጥረቶችን አድንቀዋል።

ከበጎ ፈቃደኞች ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የቀረበ ስጦታ
ከበጎ ፈቃደኞች ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የቀረበ ስጦታ

የአደጋ መከላከል ሶስት እርምጃዎች

የአደጋ መከላከል መርሃ ግብር ውጤታማ እንዲሆን የሚያግዙ ሦስት እርምጃዎች እንዳሉ በጎ ፈቃደኞችን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ በጎ ፈቃደኞቹ ለአደጋ የተጋለጡ ሰዎችን ከጉዳት ለመጠበቅ እና ለመንከባከብ መሰማራታቸውን ገልጸው፣ ይህን አገልግሎታቸውን በብቃት ለመወጣት ጊዜን መመደብ፣ እራስን መንከባከብ እና ክህሎታቸውን ማበርከት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ሌሎችን ከአደጋ “መጠበቅ” ማለት ወንድሙን ወይም እህቱን መንከባከብ፣ ተጨባጭ የሆነ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ስሜት መግለጽ እንደሆነም አስረድተዋል።  

ከማኅበራዊ ሕይወት መገለል

የመጀመሪያው ከጉዳት የመጠበቅ ወይም የመከላከል አገልግሎት፣ ሰዎች ከማኅበራዊ ሕይወት እንዳይገለሉ ማድረግ እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በዚህ መንገድ በተግባር የሚገለጽ ከአደጋ የመጠበቅ አገልግሎት ፣ የተስፋ ድምጽ የሚሰጥበት አስፈላጊ የአደጋ መከላከያ መንገድ መሆኑን አስረድተዋል። ይህም አቅመ ደካማነታችን እና ማንም ሰው ከሚደርስበት አደጋ ብቻውን መዳን እንደማይችል በግልጽ የታየበት የወረርሽኙ ወቅት አገልግሎት መሆኑን ገልጸዋል። ሕይወታችን ከሌሎች ሰዎች ሕይወት ጋር የተቆራኘ መሆኑን መረዳት እና ማየት ይኖርብናል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ይህም በወንድማማችነት እና በእህትማማችነት ስሜት የበለጠ እንድንገናኝ እና እንድንተሳሰር፣ ማኅበረሰባችንም በኅብረት ለመኖር የበለጠ ምቹ እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል።

ምድራችን ብሶቷን በመግለጽ ላይ ትገኛለች!

ከጉዳት የመጠበቅ እና የመከላከል ሁለተኛ መንገድ እንዳለ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ይህም አካባቢያዊ አደጋዎችን ለመከላከል የሚደረግ ጥረት መሆኑን አስረድተው፣ "እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ይቅር ይላል፣ ሰዎች አልፎ አልፎ ይቅር ይላሉ፣ ተፈጥሮ ግን ፈጽሞ ይቅር አይልም" የሚለውን የስፔን ጥንታዊ አባባልን አስታውሰዋል። "የዘመናችን የአየር ንብረት ለውጥ አስከፊ ክስተቶችን በማሳደግ በሕዝቦች ላይ አስደንጋጭ አደጋዎችን እያስከተለ እንደሚገኝ ገልጸው፣ በኃይለኛ የጎርፍ እና የአውሎ ነፋስ አደጋዎች እንዲሁም የባሕር መናወጥ የተነሳ ሰዎች ሕይወታቸውን እና ቤት ንብረታቸውን እያጡ መሆኑን አስታውሰዋል። “ምድራችን ብሶቷን በጩሄት እየገለጸች ትገኛለች!” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በጭንቅ ውስጥ የምትገኝ ምድራችን የምታሰማውን ዋይታ የማናዳምጥ ከሆነ፣ ተፈጥሮ በበኩሉ የጭካኔ ፊቱን እንደሚያሳየን እና የሰው ልጅም የፍርሃት ድምጹን እንደሚያስተጋባ ገልጸዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከበጎ ፈቃደኛ ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከበጎ ፈቃደኛ ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ

ከአደጋ ራስን የመከላከል ግንዛቤን መፍጠር

የሰው ልጅ ራሱን ከጉዳት የሚጠብቅበት ሦስተኛው መንገድ፣ በአስተዳደር ኃላፊነት ላይ የሚገኙ ልዩ ልዩ ግለሰቦችን ማሳተፍ እንደሆነ የተገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ ለሰው ልጅ በሙሉ ከፈጣሪው የተሰጠው የተፈጥሮ ጸጋዎች በጥቂት ሰዎች እጅ ብቻ እንዳይወድቁ በቂ ግንዛቤን ማስጨበጥ እንደሚያስፈልግ እና አሉታዊ ክስተቶች በሕዝቡ ላይ የማይጠገኑ አደጋዎችን እንዳያስከትሉ ጥንቃቄን ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በጎ ፈቃደኝነት እንክብካቤ የሚገባው ውድ እሴት ነው!

“በጎ ፈቃደኝነት” የሚለውን በማስረዳት ንግግራቸውን ያጠናቀቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሌሎች አካባቢዎች ያላዩአቸውን ሦስት እሴቶችን በጣሊያን ማኅበረሰብ ዘንድ ማግኘታቸውን ገልጸው፣ ከነዚህ ሶስት እሴቶች መካከል አንዱ የጣሊያን ሕዝብ ጠንካራ የበጎ ፍቃደኝነት አገልግሎት ጥሪ እና ጠንካራ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ፍላጎት መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ጥሪ ለአገሪቱ ውድ የባሕል ሃብት በመሆኑ በደንብ እንክብካቤ ሊደረግለት እና ሊጠበቅ እንደሚያስፈልግ፣ በሐዋርያዊ ሕንጻ ውስጥ ለተቀበሏቸው የጣሊያን ብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት በጎ ፈቃደኞች አሳስበዋል።   

24 May 2022, 17:05