ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የካናዳ ቀደምት ነዋሪዎች በቫቲካን በተቀበሏቸው ወቅት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የካናዳ ቀደምት ነዋሪዎች በቫቲካን በተቀበሏቸው ወቅት  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በካናዳ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከመጭው ሐምሌ 17 – 23/2014 ዓ. ም. ድረስ በካናዳ ውስጥ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ፣ የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ አስታውቀዋል። ቅዱስነታቸው ከአገሩ ባለ ሥልጣናት፣ ከአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች እና ከአገሩ ቀደምት ነዋሪዎች በኩል የቀረበላቸውን ግብዣ በደስታ መቀበላቸውን፣ የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር፣ አቶ ማቴዮ ብሩኒ ግንቦት 5/2014 ዓ. ም. በቫቲካን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫቸው አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በካናዳ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ምኞት እንዳላቸው ደጋግመው መግለጻቸው የጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ ዳይሬክተር ገልጸው፣ በካናዳ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከአገሩ ቀደምት ነዋሪዎች ጋር እርቅን ለመፍጠት ጥረት ስታደርግ መቆየቷንም አስታውሰዋል። ከአገሩ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት፣ ከቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ከአገሩ ቀደምት ነዋሪዎች በኩል በቀረበላቸው ግብዣ እና በእርሳቸው መልካም ፈቃድ ኤድሞንተን፣ ክቤክ እና ኢካሊት በተባሉ ከተሞች ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ አስታውቋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከካናዳ የመጡ ልኡካንን መጋቢት 23/2014 ዓ. ም. በባቲካን ተቀብለው ማነጋገራቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በውይይታቸው ወቅት ሐምሌ 19 በሚከበረው የቅድስት ሐና ዓመታዊ ክብረ በዓልን ካናዳ ከሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን ጋር በኅብረት ለማክበር እንደሚፈልጉ መግለጻቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው እንግዶችን በቫቲካን ተቀብለው ባነጋገሯቸው ወቅት፣ ከአሥራ ስምንተኛ ክፍለ ዘመን መጨረሻ እስከ አሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ፣ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን ጨምሮ በአገሪቱ በሚገኙ የአብያተ ክርስቲያናት አዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በሕጻናት ላይ ይደርሱ የነበሩ እንግልቶችን አስታውሰዋል።         በዘመኑ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሥር በነበሩ ትምህርት ቤቶች ኃላፊነት የተጣለባቸው አንዳንድ ግለሰቦች በማኅበረሰቡ እና በሕጻናቱ ላይ ባደረሱት በደል እና ክብር ማሳጣት የተሰማቸውን ህመም እና ሐዘን ቅዱስነታቸው ገልጸው፣  የተፈጸመው በደል በባሕል እና በመንፈሳዊ እሴቶች ላይ ጭምር እንደነበር ተናግረው፣ የኢየሱስ ክርስቶስንም ወንጌል የሚቃረን እንደነበር አስረድተዋል።

ወደ እውነት መንገድ መጓዝ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በካናዳ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ ተጨባጭ እና ውጤታማ የሆኑ መልሶ የማቋቋም እርምጃዎች እንዲወሰዱ ቅዱስነታቸው ባቀረቡት ግብዣ መሠረት፣ የካናዳ ቤተ ክርስቲያን የጀመረችው የእርቅ ጉዞ አካል መሆኑ ታውቋል። በዚህ ጥረት በመታገዝ እውነት ለማግኘት በሚወሰዱ እርምጃዎች አማካይነት ቁስሎችን በመፈወስ እና እርቅን በማውረድ ከአገሩ ቀደምት ነዋሪዎች ጋር ያለውን የባሕል እና ማኅበራዊ ሕይወት ግንኙነት ለማሳደግ፣ የፍቅር እና እርስ በእርስ የመከባበር ባሕልን ለማሳደግ መሆኑ ታውቋል።  

የካናዳ ብጹዓን ጳጳሳት ደስታ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በካናዳ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት መርሃ ግብር ይፋ በመሆኑ የተደሰቱት የካናዳ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት፣ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ታሪካዊ፣ በአገሩ ቀደምት ነዋሪዎች ላይ የተፈጠረው ቁስል ለመፈወስ እርቅን ለማውረድ ያለመ መሆኑን አስታውቀዋል።  የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ካናዳን ሲጎበኙ ይህ ለአራተኛ ጊዜ እንደሆነ ያስታወሱት የካናዳ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሬይሞንድ ፖይሰን፣ ከዚህ በፊት እ. አ. አ. በ2002 ዓ. ም. የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በካናዳ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስም የቀረበላቸውን ግብዣ በደስታ ተቀብለው በካናዳ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ መመኘታቸው ያስደሰታቸው መሆኑን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸውን እናመሰግናለን ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሬይሞንድ ፖይሰን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ከአገሩ ተወላጆች ጋር የሚገናኙበት ሰፊ ዕድል እንደሚኖራቸው በሮም በገቡት ቃል መሠረት ምኞታቸውን እንደሚያሟሉ ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ ቅዱስነታቸውን ለመቀበል በጀመሩት የዝግጅት ወቅት ለጤናቸውም እንደሚጸልዩላቸው ገልጸዋል።

14 May 2022, 18:14