ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የ"ፖለቲካዊ ወንድማማችነት" ማሕበር አባላት ጋር በቫቲካን በተገናኙበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የ"ፖለቲካዊ ወንድማማችነት" ማሕበር አባላት ጋር በቫቲካን በተገናኙበት ወቅት   (Vatican Media)

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ 'ከእናንተ ጋር ከማይስማሙት ሰዎች ጋር የመነጋገር ባሕል አዳብሩ’ ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “Chemin Neuf” ከተሰኘው ማሕበር አባላት ጋር በግንቦት 07/2014 በቫቲካን መገናኘታቸው የተገለጸ ሲሆን ይህ ማሕበር የ"ፖለቲካዊ ወንድማማችነት" ማሕበር በመባል ጭምር ይታወቃል፣ ከዚህ ማሕበር አባላት ጋር በተገናኙበት ወቅት የማሕበሩ አባላት ተገናኝቶ የመነጋገር ባሕል እንዲያዳብሩ ይሥሩ ዘንድ ጥሪ ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን የመወያየት ባሕል እና ለሰው ልጅ የሚጠቅም እርምጃ እንዲወስዱ መጋበዛቸው ተያይዞ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሏል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

የ “Chemin-Neuf” የፖለቲካ ወንድማማችነት ማሕበር ከ18 እስከ 35 ዓመት የሞላቸው ወጣቶችን አቅፎ የያዘ ማሕበር ሲሆን እነዚህ ወጣቶች ከተለያዩ አገሮች እና የፖለቲካ ባህሎች የተውጣጡ፣ ለጋራ ጥቅምና ለድሆች በአንድ ዓይነት ፍቅር ተነሳስተው እና እንደ እግዚአብሔር ልብ በፖለቲካ ውስጥ ለመንቀሳቀስ የሚጓጉ ወጣቶችን ያሰባስባል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሰኞ ዕለት ግንቦት 07/2014 ዓ.ም በቫቲካን ለተገኙ የዚህ ማሕበር አባላት ባደረጉት ንግግር ለክርስቲያኖች እውነተኛ የፖለቲካ ትርጉም ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል።

"ፖለቲካ ማለት መገናኘት፣ ማሰላሰል፣ በተግባር መፈጸም ነው" ብለዋል።

በመጀመሪያ ደረጃ ፖለቲካ የመገናኘት ጥበብ ነው።

ይህ ግንኙነት ለሌሎች ክፍት መሆን እና ልዩነቶቻቸውን እንደ የአክብሮት የውይይት አካል አድርጎ መቀበልን የሚያካትት መሆኑን በመጥቀስ ለክርስቲያኖች ደግሞ ተጨማሪ ነገር አለ ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዳስረዱት ቅዱስ ወንጌል ጠላቶቻችንን እንድንወድ የሚጠይቅ ሲሆን ይህም ማለት “ፖለቲካዊ ግንኙነቶችን እንደ ወንድማማችነት እንድንመለከት ተጠርተናል፣ በተለይም ከእኛ ጋር ከሐሳብ ከማይስማሙ ሰዎች ጋር ተገናኝቶ መወያየት” ማለት ነው ብሏል።

በሌሎች ዘንድ ያለንን አመለካከት እንድንለውጥ፣ ተቀባይነትን እና መከባበርን እንድናሳይ የሚጠይቀን አመለካከት ነው ሲል አክለው ገልጸዋል።

“እንዲህ ዓይነት የአመለካከት ለውጥ ከሌለ ፖለቲካ ብዙውን ጊዜ ሰዎች ሃሳባቸውን ለመጫን እና ከጋራ ጥቅም ይልቅ ልዩ ጥቅምን ለማሳደድ የሚሞክሩበት ወደ ጠብ ግጭት የመቀየር አደጋ ያጋልጣል፣ ይህም “ከግጭት ይልቅ አንድነት ያሸንፋል” ከሚለው መርህ በተቃራኒ የሚገኝ ሐሳብ ነው ብለዋል።

ማሰላሰል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እንደተናገሩት ፖለቲካ የጋራ ጥቅምን ማስከበር ያለበት “በተለያዩ እና ብዙ ጊዜ የሚቃወሙ ፍላጎቶችን በማጋጨት ብቻ ሳይሆን የጋራ ጥቅምን ማሳደድ እንዳለበት በመገንዘብ በክርስቲያናዊ እይታም እንዲሁ አስፈላጊ ነው” ብለዋል ።

"በአንድ ቃል ‘ሙላት ከመከፋፈል ይበልጣል’" ብሏል።

“የእኛ አቅጣጫ መጠቆሚያ ኮምፓስ፣ ይህንን የጋራ መርዐ ግብር ለማራመድ የሚረዳን ቅዱስ ወንጌል ነው፣ እሱም ለዓለም በእግዚአብሔር የተወደደ የሰው ልጅ ጥልቅ አወንታዊ እይታን ያመጣል” ብለዋል።

ተግባር

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ እንደ ተናገሩት “ተግባር” በሚለው ቃል ላይ አስተንትኖ ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን የፖለቲካ ወንድማማችነት “የውይይት እና የሐሳብ ልውውጥ መድረኮች ብቻ በመሆናቸው እርካታ የሌላቸው” መሆኑን የገለጹ ሲሆን ነገር ግን ወደ ተጨባጭ የቁርጠኝነት ዓይነቶች መቀየር እንደ ሚገባቸው ተናግረዋል።

"እንደ ክርስቲያኖች ፈጥነን ወይም ዘግይቶ በሚቀየር አሸዋ ላይ እንዳንገነባ ሃሳቦቻችንን ከከባድ እውነታ ጋር በመጋፈጥ ሁል ጊዜ እውነተኛ መሆን አለብን" ያሉ ሲሆን "እውነታዎች ከሀሳቦች የበለጠ አስፈላጊ መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም" በማለት አክለው ገልጸዋል።

ስደተኞች እና ስነ-ምህዳር

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ማህበረሰቡ በስደተኞች እና በስነ-ምህዳር ስም የሚሰራውን ስራ በማስታወስ አንዳንድ አባላቶቹ በፓሪስ ለሚከናወነው የስነ-ምህዳር ስብሰባ ዝግጅት ውስጥ ቦታ ስለተሰጣቸው አድናቆታቸውን ገልጸው “የድሆችን ድምጽ ለማዳመጥ፡- ይህ በፖለቲካ ሕይወት ውስጥ የመሳተፍ ክርስቲያናዊ መንገድ ነው!” ብለዋል።

መገናኘት፣ ማሰላሰል፣ መተግበር ይህ በክርስቲያናዊ መልኩ የፖለቲካ ፕሮግራም ነው ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱም ከግጭት ይልቅ አንድነት ሁል ጊዜ የበላይ መሆን አለበት ሲሉ በድጋሚ ጥሪ አቅርበው በዚህ ከእርሳቸው ጋር በተደረገው ስብሰባ ላይ የተገኙ ሰዎች “ኢየሱስ ክርስቶስን በመምሰል” እና “መንፈስ ቅዱስን በጥሞና እንዲያዳምጡ” በመንገዳቸው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፣ ይህም ፖለቲካ እንደ “ከፍተኛ የበጎ አድራጎት ተግባር ዓይነት” ተደርጎ እንዲቆጠር እና እንዲተገበር ከጋበዙ በኋላ ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን አጠናቀዋል።

16 May 2022, 14:29