ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ዕለታዊ ጭንቀታችን ለመልካም ሥራችን እንቅፋት መሆን የለበትም አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እሑድ ሚያዝያ 23/2014 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በዕለቱ በተነበበው በዮሐ. 21:1-19 ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ከሞት የተነሳው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሦስተኛ ጊዜ መገለጡን በሚያስታውስ በዚህ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ በስብከታቸውም የዘወትር ጭንቀታችን ለመልካም የፍቅር ተግባራችን እንቅፋት እንዳይሆንብን አሳስበዋል። ክቡራት እና ክቡራን፣ ከዚህ ቀጥሎ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፤ እንኳን ለዛሬው እሑድ አደረሳችሁ!

በዛሬው መስዋዕተ ቅዳሴያችን ከዮሐ. 21:1-19 ተወስዶ የተነበበው የወንጌል ክፍል፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሳኤው በኋላ ለሐዋርያቱ ሦስተኛ ጊዜ እንደታያቸው ያስታውሰናል። ይህም የሆነው በገሊላ ሐይቅ ዳርቻ ሲሆን ከሁሉም በላይ ደግሞ ስምዖን ጴጥሮስን ይመለከታል። ስምዖን ጴጥሮስ በዚያን ወቅት ከሌሎች ደቀ መዛሙርት ጋር ነበርና ዓሣን ለማጥመድ እንደሚሄድ ነገራቸው። ይህን ማለቱ የተለመደ በመሆኑ ምንም የሚያስደንቅ ሆኖ አለተገኘም። ምክንያቱም ከዚያን ጊዜ በፊትም ቢሆን ስምዖን ጴጥሮስ ዓሣ አጥማጅ ስለ ነበረ ነው። ነገር ግን የዓሣ አጥማጅነትን ሥራ እና መረቦቹንም በሙሉ በመጣል ኢየሱስ ክርስቶስ መከተል የጀመረው በዚያው በገሊላ ሐይቅ ነበር። ከሞትም የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ይጠብቀው ስለነበር፣ የዓሣ አጥማጅነት ሥራን መተው ትንሽ ቅር ቢያሰኘውም፣ ወደ ቀድሞ ሕይወቱ እንደሚመለስ ከእርሱ ጋር ለነበሩት ነገራቸው። እነርሱም ከተስማሙ በኋላ አብረውት እንደሚሄዱ ነገሩት። ያን ሌሊት ዓሣን ለማጥመድ ቢሞክሩም ምንም አላገኙም ነበር።

ይህ ሁኔታ በእኛም ላይ ሊከሰት ይችላል። በድካም ብዛት፣ በብስጭት ወይም በስንፍና ምክንያት፣ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ይልቅ የግል ፍላጎትን ለመፈጸም ወይም ራስን ለማስደሰት ካለን ፍላጎት የተነሳ፣ ከዚህ በፊት ላደረግነው ልዩ የሕይወታችን ምርጫ ዋጋን አለመስጠት። ለምሳሌ ከቤተሰብ ጋር አንድ ላይ የሚሆኑበትን ጊዜ ከመመደብ ይልቅ ብቻችን መሆንን መምረጥ፣ መጸልይን መርሳት፣ የግል ፍላጎታችንን ብቻ ለማሳካት መሮጥ፣ በሌሎች አስቸኳይ ሥራዎች በማሳበብ በጎ ሥራዎችን መሥራት እንዳለብን መዘንጋት፣ እነዚህን በመሳሰሉ ምክንያቶች፣ መፈጸም የሚገቡንን ሥራዎች ሳናከናውን እንቀራለን። ነገር ግን ይህን በማድረጋችን የምናተርፈው ብስጭትን ብቻ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስንም ያጋጠመው ይህ ነበር። በዚያን ሌሊት ምንም ዓሣ ሳያጠምድ በቀረ ጊዜ፣ መረቡም ከሐይቁ ውስጥ ምንም ዓሣ ሳይዝ ባዶ በወጣ ጊዜ ተበሳጭቶ ነበር። እኛም ብንሆን እንደ እርሱ ነን። ይህም በሕይወታችን ወደ ኋላ የሚመልሰን እንጂ ምንም ዓይነት እርካታን የሚሰጠን አይደለም።                         

በሐዋርያው ጴጥሮስ እና በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል የሆነው ነገር ምን ነበር? ብለን ስንጠይቅ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስን እና ሌሎችን፣ እንድርያስን፣ ያዕቆብን እና ዮሐንስ ወደ መረጣቸው ገሊላ ሐይቅ ዳርቻ መጣ። ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን ሰዎች በሐይቁ ዳርቻ ባገኛቸው ጊዜ አልነቀፋቸውም። ኢየሱስ ሁሌም ቢሆን ልባቸውን ከመማረክ በቀር ማንንም አይነቅፍም። በዮሐ. 21:5 ላይ እንደተጻፈው፣ ደቀ መዛሙርቱን “ልጆቼ ሆይ!” በማለት በርኅራሄ ይጠራቸዋል። ከዚያን ጊዜ በፊት እንደሚያደርገው ሁሉ መረባቸውን በድፍረት ወደ ሐይቁ እንዲወረውሩ ጋበዛቸው። በዚህ ጊዜ መረባቸው ሞልቶ እስኪፈስ ድረስ ዓሣን ያዘላቸው። ወንድሞቼ እና እህቶቼ በሕይወታችን ውስጥ “መረባችን” ባዶ በሚሆንበት ጊዜ ማዘን፣ መጨነቅ እና ወደ ቀድሞ ሕይወት መመለስ የለብንም። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመሆን አዲስ ሕይወት ልንጀምር ይገባል እንጂ ወደ ኋላ መመለስ የለብንም። “መረባችን” ባዶ በሚሆንበት ጊዜ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመሆን “መረባችንን” በድጋሚ ወደ ባሕሩ መጣል ይኖርብናል። ሐዘንን እና ብስጭትን መጋፈጥ፣ ትርጉም የሌለው ሕይወትን ዘወትር ልንዋጋው ይገባል። “ዛሬ በሕይወት ወደ ኋላ እንደተመለስኩ ይሰማኛል” ብሎ ከማዘን እና ከመበሳጨት ይልቅ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አዲስ ሕይወት እንደገና መጀመር ያስፈልጋል። እርሱም ዘወትር ይጠብቀናል። እርሱ ስለ እያንዳንዳችን፣ ስለ እኔ፣ ስለ አንተ እና አንቺ፣ ስለ ሁላችን ይጨነቃል፣ ያስባል።

ጴጥሮስም ይህ አስፈልጎት ነበር። በዮሐ. 21:7 ላይ እንደተጻፈው፣ ኢየሱስ የሚወደው ደቀ መዝሙር ዮሐንስ፣ ጴጥሮስን፥ “ጌታ እኮ ነው!” ባለው ጊዜ በፍጥነው ወደ ሐይቁ ዘልሎ በመግባት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መዋኘት ጀመረ። ይህም ትክክለኛ የፍቅር መገለጫ ነበር። ፍቅር ከአስፈላጊነቱ፣ ከምቾትነቱ ወይም ከግዴታነቱ ባሻገር አስደናቂ ነገሮችን፣ አዲስ ነገሮችን እና እራስን በነጻነት አሳልፎ የመስጠት ቅንዓትን ይፈጥራል። በዕድሜ ከሌሎች የሚያንሰው ዮሐንስ ኢየሱስን ሊያውቅ የቻለው፣ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ታላቅ የነበረው ጴጥሮስም ወደ ሐይቁ ዘልሎ በመግባት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የሄደው በዚህ መንገድ ነበር። ስምዖን ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመድረስ ባደረገው ዋና ውስጥ አዲስ ጉጉት እንደነበረው ይታይ ነበር።

ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ከሞት የተነሳው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬ እያንዳንዳችንን ለአዲስ ተነሳሽነት ይጋብዘናል። ምንም ነገር እንደምናጣ ሳንፈራ፣ ግራ እና ቀኝ ሳንመለከት፣ ሌሎች እንዲጀምሩት ሳንጠብቅ መልካም ወደ ሆነው መንገድ ቶሎ ብለን እንድንገባ ይጋብዘናል። ኢየሱስን ክርስቶስን ለማግኘት ስንነሳ ሌሎችን መጠበቅ አያስፈልግም። ምክንያቱም ለሚያጋጥመን ነገር ሁሉ ሃላፊነትን በመውሰድ በድፍረት መነሳት አለብን። ይህን በምናደርግበት ጊዜ ለሌሎች በጎ የሆነውን ለማድረግ ዝግጁዎች ነን? ወይስ ልባችንን ለሌሎች ዝግ በማድረግ በፍርሃት ውስጥ እንገኛለን? ብለን እራሳችንን መጠየቅ ያስፈልጋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በዛሬ ቃሉ የሚነግረን ይህ ነው። 

በዚህ ታሪክ መጨረሻ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ስምዖን ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ መጠየቁን እንመለከታለን፥    “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! እነዚህ ከሚወዱኝ ይበልጥ ትወደኛለህን?” አለው (ዮሐ. 21:15-16)። ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬ እያንዳንዳችንን “ትወደኛለህን? ፣ ትወጂኛለሽን?” በማለት ይጠይቀናል። ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ በብርሃን ትንሳኤው አማካይነት ልባችን እንዲነሳ ይፈልጋል። እምነት የእውቀት ጉዳይ ሳይሆን የፍቅር ጥያቄ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ እናንተን፣ እኔን እና ሁላችንንም “ትወደኛለህን? ፣ ትወጂኛለሽን?” በማለት ይጠይቀናል። “መረባችን” ባዶ በሚሆንበት ጊዜ፣ ምናልባትም ተስፋን ከመቁርጥ የተነሳ በራስ መተማመን ሲጠፋ፣ በድጋሚ “መረባችንን” ወደ ባሕሩ ለመጣል ድፍረት እንዲኖረን ይጠይቀናል። ስምዖን ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ዘንድ ከመጣበት ጊዜ አንስቶ ቀድሞ የነበረውን የዓሣ አጥማጅነት ሥራን ለአንዴ ለመጨረሻ ጊዜ በመተው፣ ራሱን ለእግዚአብሔር፣ ለወንድሞቹ እና እህቶቹ አገልግሎት ሕይወቱን እዚህ በምንገኝበት ሥፍራ ለሞት አሳልፎ እስከ መስጠት ደርሷል። እኛስ ታዲያ ኢየሱስ ክርስቶስን ማፍቀር እንፈልጋለን?

የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም ዘወትር ዝግጁ የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መልካምን ማድረግ የምንችልበት ኃይል እንድናውቅ ትርዳን።”      

02 May 2022, 17:17