ፈልግ

በዮክሬይን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ብዙ ሕጻናት እና ወላጆቻቸው ለስደት ተዳርገዋል በዮክሬይን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ብዙ ሕጻናት እና ወላጆቻቸው ለስደት ተዳርገዋል  (REUTERS)

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ጦርነት መስዋዕትነት ያስከፍላል፣ ጦርነትን መቀለብ እናቁም” ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጣሊያነኛ ቋንቋ “Contro la guerra. Il coraggio di costruire la pace” (ጦርነትን መቃወም። ሰላምን የመገንባት ድፍረት) በሚል አርዕስት በመጋቢት 05/2014 ዓ.ም አንድ መጽሐፍ ለንባብ ማቅረባቸው የተገለጸ ሲሆን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ውይይትን እንደ ፖለቲካዊ ጥበብ በመጠቀም ሰላምን የመገንባት ሂደትን በማፋጠን የጦር መሳሪያ መፍታት እንደ ስትራቴጂካዊ ምርጫ የሚያቀርብ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መጽሐፍ ለንባብ ይፋ ሆኖ መቀረቡ የተገለጸ ሲሆን የዚህን መጽሐፍ መግቢያው በአጭሩ እንደ ሚከተለው እንመለከታለን።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን  

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዚህ መጽሐፍ መግቢያ ላይ የሚከተለውን ሐሳብ አስፍረዋል።

ከአመት በፊት በከፍተኛ ጦርነት ወደ ተደበደበችው ኢራቅ ሄጄ በነበረበት ወቅት በጦርነት ፣በወንድማማቾች መካከል በተነሳው ግጭት እና በአሸባሪዎች ጥቃት ምክንያት የተፈጠረውን አደጋ ማየት ችያለሁ ፣የቤት ፍርስራሾችን እና የልብ ቁስልን ተመልክቻለሁ ፣ነገር ግን እንደገና የመወለድ የሚመኘውን የተስፋ ዘሮችን አይቻለሁ። ያኔ ከአንድ አመት በኋላ በአውሮፓ ግጭት ይነሳል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር። የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆኜ ከተመረጥኩኝ በኋላ ካገለገልኩበት ጊዜ አንስቶ ስለ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ተናግሬአለሁ፣ አሁንም ይህንን ሁኔታ እየኖርን ነው፣ ምንም እንኳን አሁንም እነዚህ ጦርነቶች ቁርጥራጭ መስለው ቢታዩም፣ እነዚያ ቁርጥራጮች አንድ ላይ እየተጣመሩ እና እያደጉና እየበዙ መጥተዋል … በጣም ብዙ ጦርነቶች በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ እየተከሰቱ ነው ፣ ብዙ ሥቃይ ያስከትላሉ ፣ ንጹሐን ተጎጂዎች በተለይም ሕፃናት ተጎጂዎች ይሆናሉ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለስደት የሚዳርጉ ጦርነቶች፣ ህይወታቸውን ለማትረፍ ምድራቸውን፣ ቤታቸውን እና ከተሞቻቸውን ለቀው እንዲወጡ ተገደዋል። እነዚህ ብዙ የተረሱ ጦርነቶች ናቸው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በትኩረት በማያዩ ዓይኖቻችን ፊት እንደገና ይከሰታሉ።

እነዚህ ጦርነቶች "ሩቅ" ይመስሉን ነበር። እስከ አሁን፣ በድንገት ከሞላ ጎደል ጦርነቱ በአቅራቢያችን ተቀሰቀሰ። ዩክሬን ተጠቃች እና ተወረረች። በግጭቱ ውስጥ፣ በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ብዙ ንጹሐን ዜጎች፣ ብዙ ሴቶች፣ ብዙ ሕጻናት፣ ብዙ አዛውንቶች ተጎድተዋል፣ ከቦምብ ለማምለጥ በምድር ማሕፀን ውስጥ በተቆፈሩት መጠለያዎች ውስጥ ለመኖር የተገደዱ፣ ባሎች፣ አባቶች፣ አያቶች የተለያዩ ቤተሰቦች በጭንቀት ውስጥ ይገኛሉ። እነሱ ለመዋጋት በእዚያው ይቆያሉ ፣ ሚስቶች ፣ እናቶች እና አያቶች ከረዥም የተስፋ ጉዞ በኋላ ጥገኝነት ፈልገው ድንበር አቋርጠው በታላቅ ልብ የሚቀበሏቸውን ሌሎች ሀገራት እንግዳ ተቀባይነታቸውን ይፈልጋሉ ።

በየእለቱ በምናያቸው አስጨናቂ ምስሎች ፊት ለፊት፣ በልጆችና በሴቶች ጩኸት ፊት ጦርነት “አቁሙ!” ብለን ብቻ መጮህ እንችላለን። ጦርነት መፍትሔ አይደለም፣ ጦርነት እብደት ነው፣ ጦርነት ጭራቅ ነው፣ ጦርነት ሁሉንም ነገር በማውጣት ራሱን የሚመግበው ነቀርሳ ነው! ከዚህም በላይ ጦርነት በምድራችን ላይ እጅግ ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወትን፣ የትንንሽ ልጆችን ንጽህና፣ የፍጥረትን ውበት የሚያጠፋ እና መስዋዕትነት የምያስከፍል ነው።

አዎን ጦርነት መስዋዕትነትን ይጠይቃል! ዓለምን በኒውክሌር ግጭት ገደል ውስጥ ሊያስገባው የሚችለውን ጦርነት እንዲያቆም እ.አ.አ በ1962 ዓ.ም ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ በጊዜው ለነበሩት ኃይሎች ያቅረቡትን ልመና  ሳላስታውስ አላልፍም። ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እ.ኤ.አ. በ1965 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ሲያደርጉ “ከእንግዲህ ጦርነት የለም! ከእንግዲህ ጦርነት የለም! ” ብለው ነበር። ወይም ደግሞ፣ እ.አ.አ በ1991 ዓ.ም ጦርነትን “መመለሻ የሌለው ጀብዱ” ሲሉ የገለጹት ደግሞ የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ብዙ የሰላም ጥሪዎችን ማቅረባቸው ይታወሳል።

እያየነው ያለነው ሌላ አረመኔነት ነው እናም እኛ በሚያሳዝን ሁኔታ፣ አጭር ትውስታ አለን። አዎን ምክንያቱም ትውስታ ቢኖረን ኖሮ አያቶቻችን እና ወላጆቻችን የነገሩንን እናስታውስ ነበር፣ እናም ሳንባችን ኦክሲጅን እንደሚያስፈልገው ሁሉ ሰላም እንደሚያስፈልገን ይሰማን ነበር። ጦርነት ሁሉንም ነገር ያነዳል፣ ንፁህ እብደት ነው ፣ ዋና አላማው ጥፋት ነው እናም በትክክል በጥፋት ያድጋል እና በጥፋት ይጎረምሳል እናም ትዝታ ቢኖረን ኖሮ አስር እና መቶ ቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ለዳግም የጦር መሣርያ ትጥቅ እያጠፋን እራሳችንን እያሳደግን የተራቀቀ መሳሪያ ለማስታጠቅ እና ለመታጠቅ ባልቸኮልን ነበር፣ በስቶክሆልም ጠቃሚ የጥናት ማዕከል ቆጠራ መሠረት የጦር መሣሪያ ገበያ ሕፃናትን ፣ ሴቶችን ፣ አረጋውያንን የሚገድሉ የጦር መሳሪያዎች ዝውውር እና በዓመት 1981 ቢሊዮን ዶላር ለጦር መሣርያ ግዢ ባላወጣን ነበር። ወረርሽኙ በተከሰተ በሁለተኛው ዓመት ውስጥ አስደናቂ በሚባል መልኩ የጦር መሣርያ ግዢ በ 2.6 በመቶ ያደገ ሲሆን በምትኩ ጥረታችን ሁሉ በአለም አቀፍ ጤና እና ከቫይረሱ ህይወትን ማዳን ላይ ማተኮር ሲኖርበት በተቃራኒው እየሄድን እንገኛለን።

ትዝታ ቢኖረን ኖሮ ጦርነቱ ወደ ግንባር ከመድረሱ በፊት በልቦቻችን ውስጥ መቆም እንዳለበት እናውቅ ነበር። ጥላቻ፣ ጊዜው ከማለፉ በፊት፣ ከልብ መጥፋት አለበት። ይህንን ለማድረግ ደግሞ መነጋገር፣ መደራደር፣ መደማመጥ፣ ዲፕሎማሲያዊ ክህሎትና ፈጠራ፣ አርቆ አሳቢ ፖለቲካ በጦር መሳሪያ ላይ ያልተመሰረተ አዲስ የአብሮ መኖር ስርዓት መገንባት የሚችል፣ በመሳሪያ ሃይል ላይ ያልተጠለጠለ ፖለቲካ ባካሄድን ነበር።

እያንዳንዱ ጦርነት የፖለቲካ ሽንፈትን ብቻ ሳይሆን አሳፋሪ የሆነውን የክፉ ኃይሎችን ፊት ለፊት መሰጠትን ይወክላል። እ.ኤ.አ. ህዳር 2019 ዓ.ም ጃፓንን በጎበኘውበት ወቅት የሁለተኛው የአለም ጦርነት ምልክት በሆነችው ሂሮሺማ ከተማ ነዋሪዎቿ በተገደሉበት ከናጋሳኪ በሁለት ኑክሌር ቦምቦች መደብደቧ የሚታወስ ሲሆን  የአቶሚክ ሃይልን ለጦርነት ዓላማ መጠቀም ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መልኩ በሰው እና በክብሩ ላይ ብቻ ሳይሆን በጋራ ቤታችን ውስጥ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ወንጀል መፈጸም ነው ብዬ ተናግሬ ነበር። የአቶሚክ ኃይልን ለጦርነት ዓላማ መጠቀም ሥነ ምግባር የጎደለው ነው፤ የአቶሚክ የጦር መሣሪያ መያዝ ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት ነው በማለት ተናግሬ ነበር።

ከሦስት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የኒውክሌር ጦርነት በአውሮፓ ውስጥ ይታያል ብሎ ማን ሊገምት ይችላል? ስለዚህ ደረጃ በደረጃ ወደ ጥፋት እየተጓዝን ነው። ቀስ በቀስ ዓለም የሦስተኛው የዓለም ጦርነት ትእይንት የመሆን ስጋት አለባት። የማይቀር መስሎ ይታየናል። ይልቁንስ በኃይል መድገም አለብን፣ አይሆንም አይቀሬ አይደለም! አይ ጦርነት የማይቀር ነገር አይደለም! በዚህ በጦርነት የተመሰለውን ጭራቅ እንድንበላ ስንፈቅድ ይህ ጭራቅ አንገቱን ቀና አድርጎ ተግባራችንን እንዲመራ ስንፈቅድ ሁላችንም ተሸንፈን የእግዚአብሔርን ፍጥረታት እናጠፋለን፣ መስዋዕትነትን እያስከፈልን ልጆች እና የልጅ ልጆቻችን የወደፊት ጊዜ ሞትን እናዘጋጃለን። ስግብግብነት፣ አለመቻቻል፣ የሥልጣን ጥማት፣ ዓመፅ፣ የጦርነቱን ውሳኔ ወደፊት የሚገፋፉ ምክንያቶች ናቸው፣ እነዚህም ምክንያቶች ብዙውን ጊዜ የሚጸድቁት የሰው ልጅ ሕይወት፣ የእያንዳንዱን ሰው ሕይወት፣ የማይለካ ክብር በሚረሳ የጦርነት አስተሳሰብ ነው።

ከዩክሬን ወደ እኛ የሚመጡትን የሞት ምስሎች እየተመለከትን ተስፋ ማድረግ አስቸጋሪ ነው። ሆኖም የተስፋ ምልክቶች አሉ። ጦርነት የማይመኙ፣ ጦርነትን የማያጸድቁ፣ ግን ሰላም የሚጠይቁ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ጦርነቱን ለማስቆም፣ ጦርነቶችን ለማቆም የሚቻለውን እና የማይቻለውን ሁሉ እንድናደርግ የሚጠይቁን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች አሉ። በመጀመሪያ ከሁሉም ወጣቶች እና ልጆች ጋር አንድ ላይ መደጋገፍ እንዳለብን እያሰብን ዳግም ጦርነት እንዳይከሰት መጣር አለብን። እናም በተመሳሳይ ጊዜ የበለጠ ሰላም የሰፈነበት ዓለም ለመገንባት እራሳችንን መስዋዕት አድርገን ማቅረብ የሚገባን ሲሆን ምክንያቱም የበለጠ ፍትሃዊ የሆነ  ሰላም የሚያሸንፍበት እንጂ የጦርነት እብደት የሌለበት ዓለም መገንባት እንችል ዘንድ ነው።  የፍትህ እና የጦርነት ኢፍትሃዊነት፣ እርስ በርሳችን ይቅር መባባል እንጂ እርስ በርስ የሚከፋፈሉ እና በሌላው ላይ ከእኛ የተለየ ጠላት እንድናይ የሚያደርገን ጥላቻን ማስወገድ ይገባል።

እዚህ ላይ እኔ አንድ ጣሊያናዊ መንፈሳዊ አባት አባ ቶኒኖ ቤሎ ፑሊያ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሰላም ነቢይ የሆኑ አባት ያሉትን መድገም እወዳለሁ፣ ግጭቶች እና ጦርነቶች ሁሉ " ሥር መሰረቶቻቸውን ያደረጉት ከደበዘዘ ፊት ላይ ነው” ይሉ ነበር። የሌላውን ፊት ስናጠፋ የጦር መሳሪያ ድምጽ እንዲሰነጠቅ ማድረግ እንችላለን። ሌላውን በዓይኖቻችን ፊት ፊቱ ሕመሙን የሚገልጽ ሲሆን ያኔ ክብሩን በአመጽ እንድንጎዳ አይፈቅድልንም።

በጣሊያነኛ ቋንቋ “ፍራቴሊ ቱቲ” (ሁላችንም ወንድማማቾች ነን) በተሰኘው ጳጳሳዊ መልእክት ውስጥ ለጦር መሳሪያዎች እና ለሌሎች ወታደራዊ ወጪዎች የሚውለውን ገንዘብ ረሃብን ለማስወገድ እና የድሃ ሀገራትን ልማት ለማስፋፋት ነዋሪዎች የገዛ አገሮቻቸውን ጥለው እንዳይሰደዱ ለማድረግ የታሰበ ዓለም አቀፍ ፈንድ ለማቋቋም ሀሳብ አቅርቤ ነበር። ይህ እውን ቢሆን ኖሮ አታላይ እና የበለጠ ክብር ያለው ሕይወት ለመፈለግ አገራቸውን ለቀው እንዲወጡ አይገደዱም ነበር። ይህንን ሃሳብ ዛሬ በተለይም ዛሬ አድሳለሁ። ጦርነቱ መቆም ስላለበት ነው፣ ጦርነቱ መቆም ስላለበትና የሚቆመው ደግሞ ጦርነቱን “መመገብን” ካቆምን ብቻ ነው።

13 April 2022, 11:21