ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ   (Vatican Media)

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ እያንዳንዱ ጦርነት መላውን የሰው ልጅ የሚጎዳ ውጤት ያመጣል ማለታቸው ተገለጸ!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በሚያዝያ 09/2014 ዓ.ም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበት የትንሳሄ በዓል በታላቅ መንፈሳዊነት እየተከበረ ይገኛል። ይህ በዓል በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በታላቅ መንፈሳዊነት በተከናወነውና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመሩት መስዋዕተ ቅዳሴ ተከብሮ ማለፉ የተገለጸ ሲሆን በመቀጠልም ቅዱስነታቸው በታላላቅ መንፈሳዊ በዓላት በተለይም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት የገና በዓል ቀን እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በተነሳበት የትንሳኤ ቀን ልማዳዊ በሆነ መልኩ አንድ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በላቲን ቋንቋ “Urbi et Orbi” (በአማሪኛው ለከተማው (ሮም) እና ለዓለም) የተሰኘውን መልእክት እንደ ሚያስተላልፉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በእለቱ ባስተላለፉት መልእክት እያንዳንዱ ጦርነት መላውን የሰው ልጅ የሚጎዳ ውጤት ያመጣል ማለታቸው ተገልጿል።   

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ በላቲን ቋንቋ “Urbi et Orbi” (በአማሪኛው ለከተማው (ሮም) እና ለዓለም) የተሰኘውን መልእክታቸውን ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ መልካም የትንሳኤ በዓል!

የተሰቀለው ኢየሱስ ተነስቷል! በተዘጋው በር ውስጥ በፍርሃትና በጭንቀት በተሞሉና ባዘኑት ሰዎች መካከል ይቆማል። በመካከላቸው ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። (ዮሐ. 20:19 ) በእጆቹ እና በእግሮቹ ላይ ቁስሎችን እንዲሁም በጎን በኩል ያለውን ቁስል ያሳያል። እርሱ መንፈስ አይደለም፣ በመስቀል ላይ የሞተው እና በመቃብር ውስጥ የተቀመጠው ያው ኢየሱስ ነው። በደቀ መዛሙርቱ ፊት “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” ሲል በድጋሚ ተናግሯል። (ዮሐንስ 20፡21)

ዓይኖቻችንም በዚህ የጦርነት ፋሲካ ላይ በማይታመን መልኩ እየተመለከቱ ናቸው። ብዙ ደም፣ ብዙ ዓመፅ አይተናል። ብዙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ከቦምብ ጥቃት ለመዳን ራሳቸውን መቆለፍ ስላለባቸው ልባችንም በፍርሃት እና በጭንቀት ተሞልቷል። ኢየሱስ በእውነት እንደተነሳ፣ በእውነት ሞትን ድል እንዳደረገ ለማመን እንታገላለን። ቅዠት ሊሆን ይችላል? የአስተሳሰባችን ምስል ሊሆን ይችላል ወይ?

አይ ቅዠት አይደለም! ዛሬ ከምንጊዜውም በላይ፣ በምሥራቅ በሚገኙ ክርስቲያኖች ዘንድ በጣም የተወደደውን የትንሳኤ አዋጅ ሲያስተጋባ እንሰማለን፣ “ክርስቶስ ተነስቷል! እሱ በእውነት ይነሳል!” ዛሬ ማለቂያ የሌለው በሚመስለው የዐብይ ጾም ወቅት መጨረሻ ላይ ከምንጊዜውም በላይ እርሱን እንፈልጋለን። ከባድ ጉዳት ካደረሰብን የሁለት ዓመታት ወረርሽኝ ወጥተናል። እጅ ለእጅ ተያይዘን ከዋሻው የምንወጣበት ጊዜ ደረሰ... ነገር ግን አቤልን እንደ ወንድም ሳይሆን እንደ ተቀናቃኝ/ባላንጣ ያየው የቃየል መንፈስ አሁንም በውስጣችን እንዳለ እያሳየን ነው። ተቀናቃኝ መስሎ ስለታየው እሱን እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል አሰበ። በፍቅር ድል ማድረግ እንችል ዘንድ እና እርቅን ተስፋ ማድረግ እንችል ዘንድ የተሰቀለውን እና የተነሳውን ጌታ እንፈልጋለን ። ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በላይ በመካከላችን ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” በማለት ይህንን ቃል እንዲደግም እንፈልጋለን።

እሱ ብቻ ነው ይህንን ማድረግ የሚችለው። ዛሬ እሱ ብቻ ስለ ሰላም ሊናገረን መብት አለው። የቆሰለው ኢየሱስ ብቻ፣ ቁስላችንን ይሸከማልና ይህንን ማደረግ የሚችለው እርሱ ብቻ ነው። የእርሱ ቁስሎች የእኛ ናቸው፣ በሁለት ምክንያቶች። በኃጢአታችን፣ በልባችን ድንዳኔ፣ ወንድማማችነትን በጥላቻ በመቀየር በእርሱ ላይ ባደረስናቸው ስቃዮች ምክንያት የእኛ ናቸው። ስለ እኛ ሲል ስለ ተሸከማቸው እነርሱ የእኛ ናቸው፣ ከከበረ ሥጋው አልሻራቸውም፣ ለዘላለም ሊሸከማቸው መረጠ። የሰማዩ አባት አይቶ እኛን እና ዓለምን ሁሉ ይምረን ዘንድ የማይሻረው የፍቅሩ ማኅተም፣ የዘላለማዊ የምልጃ ተግባር ናቸው። በትንሳኤው በኢየሱስ አካል ላይ ያሉት ቁስሎች ሰላም እንዲኖረን እና በሰላም እንድንኖር በፍቅር መሳሪያ የተሸነፈው ለእኛ ሲል የተዋጋው እና ያሸነፈበት ጦርነት ምልክት ነው።

እነዚያን የከበሩ ቁስሎችን ስናስብ፣ የማያምኑ ዓይኖቻችን በሰፊው ይከፈታሉ፤ የደነደነ ልባችን ይከፈታል እናም “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” የሚለውን የትንሳኤ መልእክት በደስታ እንቀበላለን።

የክርስቶስ ሰላም ወደ ህይወታችን፣ ቤታችን እና ሀገራችን እንዲገባ እንፍቀድ!

በጦርነት ለተመሰቃቀለችው ዩክሬን ሰላም ይውረድ፣ በደረሰባት ግፍ እና ጭካኔ የተሞላበት ጦርነት እጅግ ተጎድታለች። በዚህ አስከፊ የመከራና የሞት ምሽት አዲስ የተስፋ ጎህ በቅርቡ ይገለጣል! ሰላምን ለማረጋገጥ እንወስን። ሰዎች እየተሰቃዩ እያለ የጡንቻ መለካካት ይብቃ። እባካችሁ ጦርነትን አንልመድ! ሁላችንም ከሰገነቶቻችን እና ከመንገዶቻችን ላይ ሆነን ስለሰላም ለመማጸን እራሳችንን እንስጥ! የአገር መሪዎች የሰዎችን የሰላም ልመና ይስሙ። ሳይንቲስቶች ከሰባ ዓመት ገደማ በፊት ያቀረቡትን “የሰውን ዘር እናስወግድ ወይስ የሰው ልጅ ጦርነትን ይክዳ?” የሚለውን አሳሳቢ ጥያቄ አዳምጡ።

በልቤ ሁሉንም የዩክሬን ተጎጂዎች፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ስደተኞች እና ተፈናቃዮች፣ የተከፋፈሉ ቤተሰቦች፣ ብቻቸውን የተተው አዛውንቶች፣ ሕይወታቸው የተሰበረ እና ከተማዎቻቸው ወደ ምድረበዳነት የተቀየረ ጉዳተኞችን ላስብ እፈልጋለሁ። ከጦርነቱ የሚሸሹ ወላጅ አልባ ህፃናት ፊት አይቻለሁ። እነርሱን ስንመለከት፣ በዓለማችን ሁሉ እየተሰቃዩ ካሉት ሌሎች ሕጻናት ሁሉ ጋር፣ በረሃብ ወይም በሕክምና እጦት የሚሞቱትን፣ የበደል እና የጥቃት ሰለባ የሆኑትን ሕጻናት ሁሉ የእነርሱን የስቃይ ጩኸት ከመስማት በቀር ምንም ማድረግ አልቻልንም። የመወለድ መብት የተነፈጉ በማሕጸን ያሉ ሕጻናትን ጨምሮ ማለት ነው ለእነርሱም ቢሆን የሚገባንን ማድረግ አልቻልንም።

በጦርነቱ ስቃይ ውስጥ በመላው አውሮፓ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን የሚቀበሉ የእነዚያ ቤተሰቦች እና ማህበረሰቦች በሮች ክፍት መሆናቸው አበረታች ምልክቶችም ናቸው። እነዚህ በርካታ የበጎ አድራጎት ተግባራት ለህብረተሰባችን በረከት ይሁኑ፣ አንዳንድ ጊዜ በራስ ወዳድነት እና በግለኝነት የተዋረደ ማንነታችን ለሁሉም ሰው እንግዳ ተቀባይ እንድንሆን ያግዘን።

በአውሮፓ ውስጥ ያለው ግጭት በሌሎች አገራት ውስጥ ያሉ ግጭቶች ፣ የስቃይ እና የሀዘን ሁኔታዎች ፣ ሁሉንም የዓለማችን አካባቢዎችን የሚነኩ ሁኔታዎች ፣ ችላ ልንላቸው የማንችላቸው እና ልንረሳቸው የማንፈልጋቸው ሁኔታዎች የበለጠ እንድንጨነቅ እና መፍትኸ እንድንፈልግ ያነሳሱን።

ለዓመታት በተፈጠረው ግጭትና መለያየት በተጎዳው በመካከለኛው ምስራቅ ሰላም ይሁን። በዚህ በከበረች ቀን በኢየሩሳሌም ላይ ሰላም፣ ለሚወዷትም ሁሉ ሰላም ይመጣ ዘንድ እንለምን (መዝ. 121 [122])፣ ክርስቲያኖች፣ አይሁዶች እና ሙስሊሞች በሰላም ይኖሩ ዘንድ እንለምን። እስራኤላውያን፣ ፍልስጤማውያን እና በቅድስት ከተማ የሚኖሩ ሁሉ፣ ከምእመናን ጋር በመሆን የሰላምን ውበት ይለማመዱ፣ በወንድማማችነት ለመኖር እና የእያንዳንዳቸውን መብት በጋራ በማክበር ወደ ቅዱሳን ስፍራዎች በነፃ እንዲገቡ ይሁን።

ለሊባኖስ፣ ለሶሪያ እና ለኢራቅ ህዝቦች በተለይም ለመካከለኛው ምስራቅ ክርስትያን ማህበረሰቦች ሁሉ ሰላምና እርቅ ይሁን።

ሰላም ለሊቢያ ይሁን፣ ከአመታት ውጥረት በኋላ መረጋጋት እንድታገኝ እና በተዘነጋ ግጭት ለምትሰቃይ የመን ቀጣይነት ባለው መልኩ ብዙ ሰዎች ተጎጂ ሰለሆኑ በቅርብ ቀናት የተፈረመው የእርቅ ስምምነት የህዝቧን ተስፋ ይመልስ።

ከሙታን የተነሣው ጌታ የማያንማር ሕዝቦችን የማስታረቅ ስጦታ እንዲሰጠን እንጠይቃለን፣ አስደናቂ የጥላቻ እና የአመጽ ሁኔታ ለቀጠለባት አፍጋኒስታን፣ አደገኛ ማኅበራዊ ውጥረቶች እየተካረሩ ባለባት እና አሳዛኝ ሰብዓዊ ቀውስ በሕዝቧ ላይ ከፍተኛ ስቃይ እያመጣ በመሆኑ በአገሪቷ ሰላም ይሁን።

በአሸባሪዎች ጥቃት እና እየተፈፀመ ባለው ብዝበዛ ምክንያት እየፈሰሰ የሚገኘው ደም መፍሰስ እንዲቆም ለመላው አፍሪካ አህጉር ሰላም ይሁን። በተለይም ደግሞ በስህል ቀጠና አከባቢዎች ያሉ ግጭቶች እንዲቆሙና                 ህዝቦች ወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ ተጨባጭ ድጋፍ አፍሪካ እንድታገኝ እንጸልይ። በከባድ ሰብአዊ ቀውስ እየተጎዳች ባለችው ኢትዮጲያ የውይይት እና የእርቅ መንገድ በአዲስ መልክ እንዲካሄድ እንዲሁም  በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እየደረሰ ያለው ግፍ ይቁም። በደቡብ አፍሪካ ምስራቃዊ ክፍል በአውዳሚ ጎርፍ ለተጠቁ ህዝቦች ጸሎት እና ትብብር አይጉደልባቸው።

በአንዳንድ አጋጣሚዎች በነዚህ አስቸጋሪ የወረርሽኝ ወቅቶች ማህበራዊ ሁኔታቸው እየተባባሰ መምጣቱን እንዲሁም በወንጀል፣ በዓመፅ፣ በሙስና እና በአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ተባብሰው በቀጠሉባት የላቲን አሜሪካ ሕዝቦች ከሙታን የተነሳው ክርስቶስ ይርዳቸው።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ እያንዳንዱ ጦርነት መላውን የሰው ልጅ የሚጎዳ ውጤት ያመጣል፡ ከሀዘን እና ለቅሶ እስከ የስደተኞች ድራማ እና እስከ ኢኮኖሚያዊ እና የምግብ ቀውስ፣ አሁን እያየን ያለነው ምልክቶችን በዋቢነት መጥቀስ እንችላለን። ቀጣይነት ያለው የጦርነት ምልክቶች፣ እንዲሁም በሕይወታችን ውስጥ ከሚያጋጥሙን ብዙ የሚያሠቃዩ መሰናክሎች ጋር እየተጋፈጠ፣ ኃጢአትን፣ ፍርሃትንና ሞትን ድል ያደረገው ኢየሱስ ክርስቶስ ለክፋትና ለዓመፅ እጅ እንዳንሰጥ ይመክረናል። በክርስቶስ ሰላም ድል እንንሳ! ሰላምን ማረጋገጥ ይቻላል፣ ሰላም የግድ ያስፈልጋል፣ ሰላም የሁሉም ቀዳሚ ኃላፊነት ነው!

17 April 2022, 12:24