ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከቤተሰብ አባላት ጋር በተገናኙበት ወቅት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከቤተሰብ አባላት ጋር በተገናኙበት ወቅት  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የቤተሰብ ሕይወት ክብርን እንደገና መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ከሚያዝያ 19 - 21/2014 ዓ. ም. በተካሄደው ጳጳሳዊ የማኅበራዊ ሳይንስ አካዳሚ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለተገኙት አባላት መልዕክት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸው፣ የቤተሰብ ሕይወት ለረጅም ጊዜ ያህል ችግሮች ቢያጋጥሙትም፣ ክብሩን እና ውበቱን እንደገና መልሶ መንከባከብ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የፍቅር ፈተና እና ቤተሰብ የመልካም ግንኙነት መንገድ” በሚል መሪ ቃል ለሦስት ቀናት በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ዓርብ ሚያዝያ 21/2014 ዓ. ም. ቅዱስነታቸው ተገኝተው ሰላምታቸውን ለተሳታፊዎቹ ካቀረቡላቸው በኋላ፣ ለጋብቻ ሕይወት ትኩረትን በመስጠት በቤተሰብ ሕይወት የሚታዩ ተግዳሮቶችን አስታውሰዋል።

የቤተሰብ ሕይወትን የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች

በዓለማችን ውስጥ የታዩት ማኅበራዊ ለውጦች የጋብቻን ሁኔታ እና የቤተሰብ ሕይወትን እንደለወጡ ገልጸው፣ ረዥም ጊዜን ያስቆጠሩ በርካታ ማኅበራዊ ቀውሶች በቤተሰብ ሕይወት ላይ ጫና መፍጠሩን አስረድተዋል። ለዚህ መድኃኒቱ፣ “ቤተሰብ የማኅበራዊ ሥርዓት መሠረት መሆኑን በመገንዘብ፣ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን መንከባከብ የሚችል ወንድማዊ ኅብረተሰብን ለመገንባት ወሳኝ ክፍል መሆኑን በድጋሚ መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል።

በዓለማችን ውስጥ ለዘመናት ያህል ለውጦች ቢከሰቱም፣ የጋብቻን እና የቤተሰብ ሕይወት ታላቅነት የሚገልጹ ቋሚ ባህሪያት እና እሴቶች መኖራቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውሰው፣ ነገር ግን በምዕራቡ ዓለም በከፊል እንደሚታየው፣ የቤተሰብ እሴትን በግለሰብ ደረጃ የሚኖሩት ከሆነ፣ ቤተሰብ ከኅብረተሰብ አውድ ሊነጠል እና ሊበታተን ይችላል በማለት አስጠንቅቀዋል። ቤተሰብ ለኅብረተሰብ ጠቃሚ መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው ቀጥለውም፣ ይህ ሊገለጽ የሚችለው የግለሰቦች ስብስብ ሳይሆን ግንኙነቱ በጋራ ትስስር ላይ የተመሠረተ ሲሆን ብቻ ነው ብለዋል። የቤተሰብ መልካምነት ታማኝ ፍቅር፣ የመተማመን፣ የመተባበር እና የመረዳዳት ግንኙነቶችን እንደሚያካትት እና ይህም ደስታን እንደሚያስገኝ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል። ቤተሰብ፣ “እኛ” የሚል የጋራ ግንኙነት ካለው፣ ሰብዓዊነትን እንደሚያሳድግ እና በተመሳሳይ መንገድ የእያንዳንዱን ሰው ሕጋዊ ልዩነት ያረጋግጣል ብለዋል።

ቤተ ክርስቲያን እና ቤተሰብ

የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ፣ ከፍቅር የሚገኝ የቤተሰብ ሕይወት ደስታን እንደሚመለክት ገልጸው፣ “ከፍቅር የሚገኝ ደስታ” የሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ታላቁን የቤተ ክርስቲያን የጋብቻ ባሕልን ከመከተል በተጨማሪ በተግባር ለመግለጽ ጥረት እንደሚያደርግም አስረድተዋል። ቤተሰብ የመልካም አቀባበል ባሕሪይ የሚገለጥበት ቦታ መሆኑን ያስረዱት ቅዱስነታቸው፣ በተለይ አቅመ ደካማ ወይም የአካል ጉዳተኛ አባላት ባሉባቸው ቤተሰቦች ውስጥ በግልጽ እንደሚታይ ተናግረው፣ እነዚህ ቤተሰቦች በጎነትን እና ፍቅርን በማዳበር ችግሮች ውስጥ በትዕግስት የመጽናት ችሎታን ያሳድጋሉ ብለዋል። ቤተሰቦች የማደጎ አገልግሎትን ጨምሮ ለህብረተሰቡ ልዩ ልዩ ጥቅማጥቅሞችን እንደሚሰጡ ጠቁመው፣ “ቤተሰብ የድህነት ዋነኛ መድሐኒት ነው" ብለዋል። ቤተሰባዊ ወዳጅነትን የሚያሳድጉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ ፖሊሲዎችን በሁሉም ሀገራት ከሚገኝ የቤተሰብ ሕይወት ጋር በሚስማማ መልኩ ማርቀቅ እና ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የቤተሰብ ሕይወት ውበትን እንደገና መገንዘብ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የቤተሰብ ሕይወት ውበትን "እንደገና መገንዘብ" ወደሚለው ጭብጥ በመመለስ፣ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዙ አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎች እንዳሉ ተናግረዋል። የመጀመርያው፥ እውነታውን እንዳናይ የሚያደርጉ አስተሳሰቦችን ከአእምሮ ማስወገድ፣ ሁለተኛው፥ በተፈጥሮ እና በክርስቲያናዊ ጋብቻ መካከል ያለውን ግንኙነት እንደገና መገንዘብ፣ ሦስተኛው እና የመጨረሻው ቅድመ ሁኔታ፥ በሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ውስጥ የገለጹት እና በምስጢረ ተክሊል ጸጋ በኩል የሚገኝ ክርስቲያናዊ ጋብቻ፣ መላውን ሰብዓዊ ማኅበረሰብ የሚፈውስ እና ወንድማማችነትን የሚያሳድግ መሆኑን አስታውሰዋል።

30 April 2022, 16:55