ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የኦስዕና በዓል በተከበረበት ወቅት መስዋዕተ ቅዳሴ ባሳረጉበት ወቅት ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የኦስዕና በዓል በተከበረበት ወቅት መስዋዕተ ቅዳሴ ባሳረጉበት ወቅት   (AFP or licensors)

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በእርግጠኝነት በኢየሱስ ዘንድ ሁል ጊዜ ለሁሉም ሰው የሚሆን ቦታ አለ ማለታቸው ተገለጸ!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በሚያዝያ 02/2014 ዓ.ም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱን እና ሕዝቡም በታላቅ ደስታ እና ክብር “በጌታ ስም ሚመጣው ንጉሥ የተባረከ ነው!” “በሰማይ ሰላም፣ በአርያምም ክብር ይሁን!” በማለት የኢየሱስን ክብር መግለጻቸው የምክበርበት የሆሣህና በዓል በታላቅ ድምቀት ተከብሮ መላፉ ይታወቃል። ይህ በዓል በቫቲካን በምገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ተክብሮ ማለፉ የተገለጸ ሲሆን “በእርግጠኝነት በኢየሱስ ዘንድ ሁል ጊዜ ለሁሉም ሰው የሚሆን ቦታ አለ” ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ የሆሳህና በዓል በተከበረበት ወቅት በቫቲካን በምገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ያሰሙትን ስብከት ሙሉ ይዘት እንደ ምከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

በቀራንዮ ላይ ሁለት የአስተሳሰብ መንገዶች ይጋጫሉ። በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተሰቀለው ኢየሱስ ቃል ከሰቀሉት ሰዎች ቃል ጋር በእጅጉ ይቃረናል። የኋለኛው ደግሞ “ራስህን አድን” እያለ ይቀጥላል። የሕዝቡ መሪዎች፡- “የተመረጠው የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ከሆነ ራሱን ያድን” (ሉቃስ 23፡35) አሉ። ወታደሮቹም ተመሳሳይ ነገር አሉ፡- “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ከሆንክ ራስህን አድን” (ሉቃስ 23፡ 37) አሉ። በመጨረሻም ከወንጀለኞቹ አንዱ የእነዚህን ሰዎች ቃላት በማስተጋባት “አንተ ክርስቶስ አይደለህምን? ራስህን አድን” (ሉቃስ 23፡39) አለው፤ እራስህን አድን እራስህን ተንከባከብ፣ ለራስህ አስብ አለው። ለሌሎች አይደለም፣ ነገር ግን ደህንነትህን፣ ስኬትህን፣ ፍላጎትህን፣ ንብረትህን፣ ስልጣንህን፣ የራስህን መልካም ምስል ብቻ አድን እንደ ማለት ነው። እራስህን አድን የሚለው ይህ ቃል ጌታን የሰቀለው የአለም የማያቋርጥ መታቀብ ነው። እስቲ እናስብበት።

በዚህ “ራስ” ላይ ያማከለ አስተሳሰብ የእግዚአብሔር አስተሳሰብ ከዚህ በተቃራኒው የሚገኝ ሐሳብ ነው። "ራስህን አድን" የምለው መፈክር እራሱን መስዋዕት አድርጎ ከምያቀርበው የአዳኙ ቃላት ጋር ይጋጫል። ልክ እንደ ጠላቶቹ ኢየሱስ በዛሬው ወንጌል ውስጥ ሦስት ጊዜ ተናግሯል (ሉቃስ 23፡ 34.43.46)። እርሱ ግን ለራሱ ምንም ነገር አልጠየቀም፤ በእርግጥም ራሱን እንኳን አልተከላከለም ወይም ራሱን አላጸደቀም። ወደ አብ ጸለየ ለደጉ ሌባ ምሕረትን አቀረበ። ከቃላቶቹ አንዱ በተለይም "ራስህን አድን" በምለው መፈክር መካከል ያለውን ልዩነት አመልክቷል። እንዲህ አለ፡- “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” (ሉቃስ 23፡ 34) አለ።

እነዚህን የጌታን ቃላት እናስብ። መቼ ነው የተናገራቸው? በጣም በተወሰነ ቅጽበት፡ በመስቀል ላይ እያለ ምስማሮቹ  አንጓውን እና እግሮቹን ሲወጉ በተሰማው ጊዜ የተናገራቸው ቃላት ናቸው። ምን ያህል ከባድ ሥቃይ እንደደረሰበት ለመገመት እንሞክር። በዚያን ጊዜ በሕማማቱ እጅግ በሚያስጨንቀው አካላዊ ሥቃይ፣ ክርስቶስ ለሚወጉት ሰዎች ይቅርታ ጠየቀ። እኛ ግን እንደዚህ ባሉ ጊዜያት እንጮሃለን እናም ሁሉንም ንዴታችንን እና ስቃያችንን እንዘረግፋለን። ኢየሱስ ግን፡- አባት ሆይ፥ ይቅር በላቸው አለ።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እነሱ ከምናገረው ከሌሎቹ ሰማዕታት በተለየ (2 መቃባዊያን 7፡18-19) ኢየሱስ ወንጀለኞቹን አልገሠጸም ወይም በእግዚአብሔር ስም ቅጣትን በማምጣት አላስፈራራም። ይልቁንም ለክፉ አድራጊዎች ጸለየ። የውርደት መስቀል ላይ ተጣብቆ በነበረበት ወቅት እርሱ ያሳየው ዝንባሌ የይቅር ባይነት መንፈስ ነበር።

ወንድሞች እና እህቶች፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ነገር ያደርጋል። በድርጊታችን ምክንያት ስቃይ ውስጥ ስንገባ እንኳን እግዚአብሔር የእኛን መከራን ይቀበልልናል አሁንም አንድ ፍላጎት ብቻ አለው፣ ይቅር ሊለን ይፈልጋል። ይህንን ለማድነቅ የተሰቀለውን ጌታ እንመልከት። ከሥቃይ ቁስሉ፣ በኃጢአታችን ችንካር ከፈሰሰው ከደም ፈሳሾች ይቅርታ የሚፈልቅ ነው። በመስቀል ላይ ወደ አለው ኢየሱስ እንመልከትና “አባት ሆይ የምያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” የምሉትን ከዚህ የምበልጡ ቃላት መቼም እንዳልተነገሩ እናስተውል። በመስቀል ላይ ያለውን ኢየሱስን እንመልከተው እና መቼም በለዘብታ እና በርኅራኄ እይታ እንደ ምመለከተን እንረዳ። በመስቀል ላይ ወደ ኢየሱስ እንመልከትና ከዚህ የበለጠ የፍቅር እቅፍ ተቀብለን እንደማናውቅ እንረዳ። ወደ የተሰቀለው ጌታ እንመልከት፡- “አመሰግንሃለሁ፣ ኢየሱስ ሆይ፡ ትወደኛለህ እና ሁልጊዜም ይቅር በለኝ፣ ራሴን መውደድ እና ይቅር ማለት በከበደኝ ጊዜም ቢሆን አንተ ይቅር በለኝ ልንለው ይገባል።

በዚያ እርሱ በመስቀል ላይ ሳለ፣ ሥቃዩ ከፍ ባለ ጊዜ፣ ኢየሱስ ራሱ ጠላቶቻችንን እንድንወድ የምጠይቀን ቃላት ተጠቅሞ ትእዛዛቱን  ራሱ ፈጸም። በሕይወታችን ውስጥ፣ የጎዳን፣ ያናደደን፣ ወይም ያሳዘነንን ሰው እናስብ። እንድንናደድ ያደረገን፣ ያልተረዳን ወይም መጥፎ ምሳሌ የሆነን ሰው እናስብ። የበደሉንን ወደ ኋላ በመመልከት ስንት ጊዜ እናጠፋለን! ስንት ጊዜ ወደ ኋላ መለስ ብለን እናስባለን እና ሌሎች ሰዎች በሕይወታችን ውስጥ የፈጸሙብንን በደል እና ያበላሹብንን ታሪኮች እያሰላሰልን እነዚያን ቁስሎች እያከክን የምንኖረው አስከመቼ ነው? ዛሬ ኢየሱስ በዚያ ዓይነት ስሜት ውስጥ ገብተን እንዳንቆይ ያስተምረናል፣ ነገር ግን ምላሽ እንድንሰጥ፣ የክፋትና የሀዘን አዙሪት እንድንሰብር ይመክረናል። በህይወታችን ውስጥ ያሉትን ምስማሮች በፍቅር ምላሽ ለመስጠት፣ በጥላቻ ቡፌ ፊት ይቅርታ ማድረግ እንድንችል እና በይቅርታ እንድንተቃቀፍ ይመክረናል። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን ጌታችንን እንከተላለን ወይስ ሌሎችን ለማጥቃት የምመኘውን ፍላጎቶቻችንን ነው የምንከተለው?

በእውነት የክርስቶስ መሆናችንን ለመፈተሽ ከፈለግን ለበደሉን ሰዎች ምን እያደረግን መሆናችንን  እንመልከት። ጌታ የምጠይቀን እንደተሰማን ወይም እንደሌላው ሰው ምላሽ እንድንሰጥ አይደለም፣ ነገር ግን በመንገዱ ላይ እንድንሄድ እና እርሱ በእኛ ላይ በምሰራው መልኩ እንድንሥራ ይፈልጋል። “ከወደዳችሁኝ እወድችኋለው” ከሚለው አስተሳሰብ እንድንወጣ ይጠይቀናል። ጓደኛዬ ከሆንክ ጓደኛህ እሆናለሁ፣ ከረዳችሁኝ እረዳችኋለው" ከምለው የግል እና የራስ ወዳድነት መንፈስ ተላቀን ለእያንዳንዱ ሰው ርኅራኄን እና ምሕረትን ማሳየት አለብን፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ወንድ ወይም ሴት ልጅን ይመለከታልና። በክፉም በደጉም ወዳጅና ጠላት አድርጎ አይለየንም። ይህን የምናደርገው እኛ ነን በዚህ መልኩም እግዚአብሔርንም እንዲሰቃይ እናደርጋለን። ለእርሱ ሁላችንም የሚወደን ልጆቹ ነን፣ አቅፎ ይቅር ሊለን የምፈልጋቸው ልጆች ነን።

አባት ሆይ የምያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው። በወንጌል መሠረት ኢየሱስ ይህን “ይል ነበር” (ሉቃስ 23፡ 34)። በመስቀል ላይ ተቸንክሮ ሳለ እነዚህን ቃላት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ብቻ አይደልም የተናገራቸው፣ ይልቁንም ዘመኑን ሁሉ በመስቀል ላይ በምያሳልፍበት ወቅት ሁልጊዜም ቢሆን በከንፈሩ ላይ የሚገኙ ቃላቶች ናቸው። እግዚአብሔር ይቅር ለማለት አይታክትም። ይህንን ለተወሰነ ጊዜ ፈጽሞ ከእዚያን በኋላ ሐሳቡን የምለውጥ አምላክ አይደለም። ኢየሱስ - የሉቃስ ወንጌል እንደ ምያስተምረን ከሆነ - ወደ ዓለም የመጣው ለኃጢአታችን ስርየትን ሊያመጣልን ነው (ሉቃ. 1፡77)። በመጨረሻ የኃጢአትን ስርየት ለሁሉም በስሙ እንድንሰብክ ግልጽ ትእዛዝ ሰጠን (ሉቃ. 24፡47)። የእግዚአብሔርን ይቅር ባይነት ከመስበክ አንታክት፣ እኛ ካህናት የንስሐ ምስጢር የምናስተዳድር በመሆናችን የተነሳ ሁሉም ክርስቲያኖች ይቅርታን ተቀብለው ለሌሎች ይቅርታን መስበክ ይችሉ ዘንድ ልንረዳቸው ይገባል።

አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው። አንድ ተጨማሪ ነገር እናስተውል። ኢየሱስ ይቅርታ እንዲደረግላቸው መጠየቁ ብቻ ሳይሆን፣ ምክንያቱንም ጠቅሷል ይህም “የሚያደርጉትን አያውቁምና” የምለው ነው። እንዴት ሊሆን ይችላል? የሰቀሉትም እንዴት እንደ ምገሉት ቀደም ብለው ካሰቡበት በኋላ ነበር፣ እስሩንና ችሎቱን አደራጅተው ነበር፣ አሁን ደግሞ ሞቱን ለማየት በቀራንዮ ላይ ቆመው ነበር። ነገር ግን ክርስቶስ እነዚያን ዓመፀኛ ሰዎች አያውቁም በማለት ያጸድቃቸዋል። ኢየሱስ በእኛ ረገድ የምያደርገው እንዲህ ነው፤ ራሱን ለእኛ ጠበቃ አድርጎ ያቆማል። እርሱ ከእኛ በተቃራኒው ጎን ሆኖ አይቆምም፣ እርሱ የምቆመው ለእኛ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ ኃጢአታችንን ይቃወማል፣ ቃሉ እንድናስብ ያደርገናል፤ አያውቁምና ይቅር በላቸው ይላል።

ዓመፅ ስናደርግ አባታችን ስለሆነው አምላክ፣ ሌላው ቀርቶ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ስለሆኑት ምንም እንደማናውቅ እናሳያለን ማለት ነው። በአለም ውስጥ ለምን እንደምንኖር አናስተውልም፣ አልፎ ተርፎም ትርጉም የለሽ የጭካኔ ድርጊቶችን እንፈጽማለን። ይህንንም ክርስቶስ በሌላ ጊዜ በተሰቀለበት በጦርነት ሞኝነት እናያለን። በባልና በወንዶች ልጆች ኢፍትሃዊ ሞት በሚያዝኑ እናቶች ክርስቶስ በድጋሚ በመስቀል ላይ ተቸንሯል። ሕፃናትን በእጃቸው ይዘው ከቦምብ የሚሸሹ ስደተኞች ምክንያት ኢየሱስን በድጋሚ እንሰቅለዋለን። እሱ ብቻቸውን ሆነው እንዲሞት በተተው አረጋውያን ውስጥ ተሰቅሏል፣ የወጣቶችን  የወደፊት እጣ ፈንታ በምያጨልም፣ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ለመግደል በተላኩ ወታደሮች ውስጥ እርሱ በድጋሚ ይሰቀላል።

አባት ሆይ የምያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው። ብዙ ሰዎች እነዚህን ያልተለመዱ ቃላት ሰምተዋል፣ ግን አንድ ሰው ብቻ ምላሽ ሰጣቸው። ከኢየሱስ ጎን የተሰቀለ ወንጀለኛ ሰው የሰጠው ምላሽ ነበር። የክርስቶስ ምሕረት በእርሱ ውስጥ አንድ የመጨረሻ ተስፋ እንዳስነሳ እና እነዚህን ቃላት እንዲናገር እንዳደረገው መገመት እንችላለን፡- “ኢየሱስ ሆይ በመንግሥትህ አስበኝ” (ሉቃስ 23፡42) አለው። “ሌሎች ሁሉ እኔን ረስተውኛል፣ እናንተ ግን የሚሰቅሉህን ሰዎች እንኳን ሳይቀር ይቅር እያልካቸው ነው። እባክህን እኔንም አስበኝ፣ በአንተ አማካይነት እኔም ባንተ ስፍራ ቦታ እንዲኖረኝ አድርገኝ” እንደ ማለት ይቆጠራል። መልካሙ ሌባ ህይወቱ እያለቀ ሲሄድ እግዚአብሔርን ተቀበለ እና በዚህ መንገድ ህይወቱ እንደ አዲስ ጀመረች። በዚህ ዓለም ሲኦል ውስጥ፣ መንግስተ ሰማያት ሲከፈት አይቷል፡ “ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” (ሉቃስ 23፡ 43) አለው። ሞት የተፈረደበትን ሰው የመጨረሻውን ጥያቄ ወደ ታሪክ የመጀመሪያ ቀኖና የለወጠው ይህ የእግዚአብሔር ይቅርታ አስደናቂ ነገር ነው።

ወንድሞች እና እህቶች፣ በዚህ ሳምንት እግዚአብሔር እያንዳንዱን ኃጢአት ይቅር እንደሚል፣ ሁሉንም ርቀት እንደሚያስተካክል እና ኀዘንን ሁሉ ወደ ደስታ እንደሚለውጥ እርግጠኞች እንሁን (መዝ. 30፡12)። በእርግጠኝነት ከኢየሱስ ጋር ሁል ጊዜ ለሁሉም ሰው የሚሆን ቦታ አለ። በኢየሱስ ዘንድ ነገሮች መቼም አያልቁም። ከእሱ ጋር ምንም ነገር ቢሆን በጣም ዘግይቶ አያውቅም። ከእግዚአብሔር ጋር ሁል ጊዜ ወደ ሕይወት መመለስ እንችላለን። አይዞህ! በይቅርታው ወደ ፋሲካ እንጓዝ። ክርስቶስ ዘወትር በአብ ፊት ስለ እኛ ይማልዳል (ዕብ. 7፡25)። ዓመፀኛ እና ስቃይ የበዛበትን ዓለማችንን እያየ፣ “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” በማለት ይህንን ደጋግሞ ከመናገር አይታክትም።

Photogallery

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የኦሳዕና በዓል መስዋዕተ ቅዳሴ ባሳረጉበት ወቅት
10 April 2022, 12:21