ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በአይርላንድ የቤልፋስት ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በቫቲካን ተቀብለው ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በአይርላንድ የቤልፋስት ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በቫቲካን ተቀብለው  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ዩኒቨርሲቲዎች የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚዳብርበት ቦታ እንዲሆኑ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሰኞ ሚያዝያ 17/2014 ዓ. ም. በአይርላንድ፣ ቤልፋስት ኩዊንስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚማሩ ካቶሊካዊ ወጣት ማኅበር አባላትን በቫቲካን ተቀብለው አነጋግረዋል። ቅዱስነታቸው ለእንግዶቹ ባቀረቡት መልዕክት፣ ዩኒቨርሲቲዎች እውነተኛ የእርስ በእርስ ግንኙነት ባሕል የሚዳብርበት ቦታ ሊሆን ይገባል ብለዋል። እምነት እና ክርስቲያናዊ ግንኙነት በእውነት ፍለጋ ውስጥ እራሳቸውን ለሌሎች የመስጠት ልባዊ ስጦታን የሚያካትት መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ማየት ብቻ ሳይሆን መመልከት፣ መስማት ብቻ ሳይሆን ማድመጥ፣ ነገሮችን አይቶ ማለፍ ብቻ  ሳይሆን ቆም ብሎ ማጤን ያስፈልጋል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የእርስ በእርስ ግንኙነት ባሕል ሊያድግ የሚችለው በዚህ መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል። ሰኞ ሚያዝያ 17/2014 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር የተገናኙት የዩኒቨርሲቲው ወጣቶች ሃያ አምስት ሲሆን፣ ወደ ቫቲካን የተጓዙበት ዋና ዓላማ በዩኒቨርስቲያቸው ውስጥ የወጣት ካቶሊካዊያን ሐዋርያዊ አገልግሎት የተመሠረተበት 50ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ መሆኑ ታውቋል።

በዙሪያው ያሉትን ማግኘት

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከአይርላንድ ለመጡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ ወጣቶቹ በመካከላቸው እና በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ መካከል እርስ በእርስ የመገናኘት ባህልን ለማዳበር እና እውነተኛ የወንጌል መንፈስን ለማስረጽ፣ በጥበብ ለተሞላ ምሁራዊ እና መንፈሳዊ ዕድገት አድናቆትን መስጠት፣ እንዲሁም ካቶሊካዊ ባሕልን መረዳት እንደሚጠይቅ ገልጸው፣ ሁሉም ነገር የሚጀምረው እርስ በእርስ ከመገናኘት እንደሆነ እና የክርስትና እምነት መሠረቱ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መገናኘት” መሆኑን አስረድተዋል።

“በእውነት በኢየሱስ ክርስቶስ የምናምን ከሆነ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመምሰል መሞከር አለብን” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ድነት የሚገኝበትን የወንጌል እውነትን ለሌሎች ማካፈል እንችል ዘንድ በዙሪያችን ካሉ ሰዎች ጋር መገናኘት ያስፈልጋል ብለው፣ እንደ ሰዎች፣ በተለይም እንደ ክርስቲያኖች፣ እውነትን ለሌሎች በመስጠት ልባዊ ስጦታን ካላቀረብን በስተቀር በግላችን መኖር እና ማደግ አንችልም ብለዋል።

ተጋግዞ በኅብረት መጓዝ

ወጣቶቹ የግል ጥረታቸውን እንዲያደርጉ የጠየቁት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የግል ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜም ነገሮችን ማየት ብቻ ሳይሆን መመልከት፣ ሌሎችን መስማት ብቻ ሳይሆን ማድመጥ፣ የምናገኛቸውን ሰዎች ሰላም ብሎ ማለፍ በቂ እንዳልሆነ፣ ነገር ግን አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መወያየት እና መሳተፍ ያስፈልጋል ብለዋል። ከግል ጥረት ባሻገርም፣ የሕይወት ጉዞን ለሌሎች በማካፈል ደስታን ማግኘት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ በእውነት ፍለጋ ወቅት እርስ በእርስ በመደጋገፍ፣ ሕይወታችን የእውነተኛ ወንድማማችነት ልምድ እንዲኖረው፣ የተቀደሰ የአንድነት ጉዞ ለማድረግ የሚያስችለንን የግንኙነት መረብ ለመዘርጋት መጣር ያስፈልጋል ብለዋል።

ይህን እርስ በእርስ የመገናኘት ባሕል በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ መካከል ለማዳበር እያንዳንዱ ተማሪ በሚመቸው እና በሚችለው አካሄድ ማከናወን እንደሚገባ፣ በዚህ መንገድ የተከበረውን የአየርላንድ ሕዝብ የእንግዳ አቀባበል፣ የእርቅ፣ የወንጌል ታማኝነት እና ቅድስናን የመፈለግ ባሕልን በጽናት ለማስቀጠል አስተዋጽኦን ማበርከት እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል።  ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመጨረሻም ወጣቶቹ በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ መካከል የእምነት እና የወዳጅነት ምሳሌ በመሆን ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ በማሳሰብ፣ መልካምን ተመኝተውላቸውዋል።

26 April 2022, 15:27