ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለስነ-ሕይወት ስነ-ምግባር ክርስቲያናዊ ምላሽ ለመስጠት መጸለይ ያስፈልጋል አሉ!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየወሩ ለወሩ የሚሆን የጸሎት ሐሳብ ይፋ በማድረግ ምዕመኑ እና በጎ ፍቃድ ያላቸው ሰዎች ሁሉ ከእርሳቸው ጋር በመንፈስ በመተባበር ጸሎት እንዲያደርጉ ጥሪ እንደ ሚያቀርቡ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው ለመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም ይሆን ዘንድ ያቀረቡት የጸሎት ሐሰብ በአሁን ወቅት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ውስጥ በስነ-ሕይወት ዙሪያ ላይ እየተከናወኑ የሚገኙ ጥናቶች መሰረታዊውን የሰው ልጅ ስነ-ምግባር የሚጻረር እንዳይሆን እና ክርስቲያኖች ለዚህ አሁናዊ ለሆነ ሁኔታ እና ተግዳሮት ተገቢውን ምላሽ ይሰጡ ዘንድ ጸሎት እዲደረግ ቅዱስነታቸው ጥሪ ማቅረባቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን 

“ለሥነ-ሕይወት ተግዳሮቶች ክርስቲያናዊ ምላሽ እንድንሰጥ እንጸልይ” በማለት በቪዲዮ ያስተላለፉትን መልእክት የጀመሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለመጋቢት ወር ባደረጉት የጸሎት ሐሳብ ለካቶሊክ ምዕመናን ይህንን ግብዣ አቅርበዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሳይንስ በባዮኤቲክስ (የስነ-ሕይወት ስነ-ምግባር) ዘርፍ ከፍተኛ መሻሻሎችን በማሳየቱ በርካታ ችግሮችን እያስመዘገበ መሆኑንም ጠቁመዋል። ጳጳሱ እንዳሉት ክርስቲያኖች ለእነዚህ ተግዳሮቶች ምላሽ መስጠት አለባቸው እንጂ “ጭንቅላታችንን እንደ ሰጎን” መቅበር የለብንም ብለዋል።

ባዮቴክኖሎጂ “በሰው ልጅ ክብር ላይ በተመሰረተ መልኩ ሁልጊዜ ጥቅም ላይ እንዲውል” ቅዱስነታቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ለሕይወት ያለን የግድየለሽነት አመለካከት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የሰው ልጅ ፅንስ በግዴለሽነት መንፈስ የማስወገድን አሁናዊ አሰራር በምሳሌነት ጠቅሰዋል። “የእኛ የመጣል ባህላችን [በሰው ልጅ ሽሎች ] ላይም እየሠራ ይገኛል። በፍጹም እንዲህ ማድረግ ተገቢ አይደለም። ይህን ባህል በዚህ መንገድ ማራዘም ብዙ ጉዳት ያመጣል” በማለት ቅዱስነታቸው በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚታየውን ጽንስ የማስወረድ ተግባር በዋቢነት በመጥቀስ ሰዎች ይህንን አሰቃቂ ጉዳይ እንደ ሰብዓዊ መብት እየቆጠሩ መምጣታቸው አሳዛኝ እንደ ሆነ አክለው ገለጿል። ጥልቅ ለውጦች እየተከሰቱ መሆናቸውን ልንገነዘብ እና በደንብ ማስተዋል ይገባናል ሲሉ የተናገሩት ቅዱስነታቸው ትርፍ ለማጋበስ ብቻ በማሰብ የሚካሄዱትን እና እየተካሄዱ የሚገኙትን የባዮሜዲካል ጥናት እንዴት የተከናወነ እንደ ሚገኝ በማንሳት ተችተዋል።

የባዮቴክኖሎጂ እድገትን በአግባቡ መምራት እንጂ መገታት አይገባም

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ቤተክርስቲያኗ የቴክኖሎጂ እድገቶችን ለመገደብ በፍጹም እንደማትፈልግ፣ ይልቁንም እነዚያን እድገቶች ለመከተል እንደምትሞክር የገለጹ ሲሆን "ይህም ማለት እድገትን ለማምጣት የሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብርን አደጋ ላይ መጣል የለብንም” ማለት ነው ብለዋል። ማንኛው ማሕበራዊ እና ቴክኖሎጃዊ አድገት የሰው ልጆችን ሰብዓዊ ክብር መጣረዝ እንደ ሌለበት ሁላችንም ማወቅ ይኖርብናል ሲሉ የተናገሩት ቅዱስነታቸው “ይህ ማለት ዕድገትን ለማረጋገጥ የሰውን ክብር ዋጋ ማሳጣት አንችልም። ሁለቱም አብረው ይሄዳሉ፣ ተስማምተው መሄድ ይችላሉ፣ የሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብርን አደጋ ላይ በማይጥል ሁኔታ እድገትን ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል።

በመጨረሻም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዓለም የቴክኖሎጂ እድገቶችን ለማረጋገጥ በሚጥርበት በአሁኑ ወቅት የሰውን ክብር እንዲያከብር በዚህ በያዝነው የመጋቢት ወር ጸሎት እናድርግ ሲሉ ምዕመኑን ከጋበዙ በኋላ ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

“አዲስ የሥነ-ሕይወት ተግዳሮቶች ለሚገጥሟቸው ክርስቲያኖች እንጸልያለን” ሲሉ ቅዱስነታቸው ማሳሰባቸውን የቅድስት መንበር የሕትመት እና የዜና አገልግሎት የገለጸ ሲሆን "የሰው ልጆችን ሁሉ ክብር በጸሎት እና በተግባር ማስጠበቅን እንቀጥላለን" ብለዋል።

ጥልቅ እና ስውር ማስተዋል

በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዓለም አቀፍ የጸሎት ኔትወርክ የተዘጋጀው ከጳጳሱ ቪዲዮ ጋር የተያያዘ ጋዜጣዊ መግለጫ የዚህ ወር የጸሎት ዓላማ ይፋ የሆነው በጳጳሳዊ የሕይወት አካዳሚ እገዛ እንደ ሆነ ገልጿል።

የእሱ ዓላማ መግለጫውን አመልክቷል፣ ባዮኤቲክስን በተመለከተ “ይበልጥ ጥልቅ እና ረቂቅ ማስተዋልን” ይጠይቃል። አባ ፍሬድሪክ ፎርኖስ የጳጳሱ ዓለም አቀፍ የጸሎት መረብ ዓለም አቀፍ ዳይሬክተር  እንደገለጹት ከሆነ “እነዚህ መጥፎ የሆኑ ባህሎችን እንድንተው የሚረዱንና ለሰው ልጅ ሕይወት ማለትም ከልደት እስከ ሞት ድረስ ያለውን የሰው ልጅ ሕይወት ሙሉ በሙሉ እንድንከባከብ የሚረዱን የማስተዋል አስፈላጊ መስፈርቶች ናቸው” ብለዋል ። አባ ፎርኖስ አክለው እንደተናገሩት "በባዮኤቲክስ አዳዲስ ተግዳሮቶች ፊት ለፊት ሁል ጊዜ በጸሎት እና በማህበራዊ ተግባር የህይወት ጥበቃን በማድረግ እንድንበረታ እንጸልይ" ካሉ በኋላ መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

09 March 2022, 11:37