ፈልግ

የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የጦርነት መከራ የሚፈታትን ቢሆንም መሻገር እንደሚቻል አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በፖቱጋል ዋና ከተማ ሊዝቦን ከሐምሌ 25 – 30/2015 ዓ. ም. ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ዝግጅት በማድረግ ላይ ለሚገኙ ወጣቶች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው ለወጣቶች ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፣ በዚህ ወቅት ያጋጠሟቸው የተለያዩ ችግሮችን ተቋቁመው እንዲሻገሩ ብርታትን ተመኝተው፣ ጦርነት ቢፈታትነንም ከዚህ ፈተና አብረን እንወጣለን ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሐምሌ ወር 2015 ዓ. ም. በሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ለመገኘት ዝግጅት በማድረግ ላይ ለሚገኙት ወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት “ችግሮች ተፈራርቀውብናል” ብለው፣ ይህ የምንገኝበት ጊዜ አስቸጋሪ የታሪክ ወቅት መሆኑን አስረድተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በሊዝቦን ከተማ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ፋውንዴሽን ፕሬዚደንት እና የሊዝቦን ከተማ ረዳት ጳጳስ ከሆኑትን ከብጹዕ አቡነ አሜሪኮ ማኑኤልን ጋር የካቲት 24/2014 ዓ. ም በቫቲካን መገናኘታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከቅዱስነታቸው መልዕክት ጋር ጳጳሱ ለወጣቶች ያስተላለፉት መልዕክትም መካተቱ ታውቋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቪዲዮ መልዕክታቸው፣ “ከወረርሽኙ ቀውስ ወጥተን በኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ገብተናል፣ አሁን ደግሞ በጦርነት ቀውስ ውስጥ እንገኛለን ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ጦርነት ደግሞ ሊደርሱብን ከሚችሉ ክፋቶች መካከል አንዱ ነው!” በማለት ገልጸውታል። በዓለም አቀፉ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ለመገኘት ወጣቶች ዝግጁዎች በመሆን፣ ከዚህ በፊት ከተከበሩ የወጣቶች ፌስቲቫል በተለየ መልኩ ለማክበር የበለጠ ዝግጁዎች እንዲሆኑ አሳስበው፣ ብፁዕ ካርሎ አኩቲስን በመጥቀስ፣ “የተጠራነው ያለፈውን ለመድገም ሳይሆን ለመታደስ ነው” ብለዋል።

ችግሮችን ማሸነፍ የሚቻለው በጋራ እንጂ ለብቻ እንዳልሆነ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ የተለያዩ ችግሮችን ተቋቁሞ በአሸናፊነት ለመውጣት ፈተናዎችን መጋፈጥ የግድ ይሆናል ብለዋል። በአሸናፊነት የምንወጣ ከሆነ ከችግሮች በኋላ የሚኖረን ጊዜ የተለየ እንደሚሆን፣ ወይም የተሻለ አለበለዚያም የከፋ ሊሆን ስለሚችል ፈተናዎችን በተሻለ ውጤት ማለፍ ያስፈልጋል በማለት አሳስበዋል።

“እናንተ ወጣቶች የፈጠራ ሰዎች ናቸሁ!”

“እናንተ ወጣቶች የፈጠራ ሰዎች ናቸሁ!” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ሐምሌ ወር 2015 ዓ. ም. የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል እየተመለከቱ በተለያዩ ውጤታማ ሥራዎች የታገዘ  መልካም ዝግጅት እንዲያደርጉ በማለት አደራ ብለዋል። ቅዱስነታቸው በመጨረሻም ፌስቲቫሉን የሚካፈሉ ወጣቶች ከበዓሉ ውስጥ ፍሬያማ የሆኑ ገጠመኞችን እንዲያገኙ፣ ከነበሩበት አስቸጋሪ ወቅት ወጥተው ወደ ተሻለ ጊዜ እንዲደርሱ በጸሎታቸው እንደሚያግዟቸው አረጋግጠውላቸዋል።

700,000 ወጣቶች የተካፈሉበት የመጨረሻው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል በመካከለኛዋ የላቲን አሜሪካ አገር ፓናማ፣ ከጥር 14 – 19/2011 ዓ. ም. መከበሩ ሲታወስ፣ የፌስቲቫሉ መሪ ቃልም ከሉቃ. 1:28 ላይ የተወሰደ እና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለመልአኩ ገብርኤል “እነሆ እኔ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነኝ፤ አንተ እንዳልክ ይሁንልኝ” ባለችው መልስ ላይ ያስተነተነ እንደነበር ይታወሳል። 

08 March 2022, 17:01