ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ እግዚአብሔር የሚያቀርብልንን አስቸኳይ የንስሐ ጥሪ እንቀበል አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ እለት በቫቲካን ከሚገኘው ከቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ሆነው በእለቱ በሚነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው አስተንትኖ እንደሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በመጋቢት 11/2014 ዓ.ም “ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ” (ሉቃስ 1-9) በሚለው ኢየሱስ ለንስኅ ባቀረብው ጥሪ ላይ መሰረቱን ያደረገ አስተንትኖ እንደነበረ የተገለጸ ሲሆን እግዚአብሔር አስቸኳይ የንስሐ ጥሪ እያቀረበልን ስለሆነ ልንቀበለው ይገባል ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮችን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ!

የዐብይ ጾም ጉዟችን እምብርት ላይ እንገኛለን፣ እናም የዛሬው ቅዱስ ወንጌል የሚጀምረው ኢየሱስን በማቅረብ ሲሆን ይህም በዕለቱ በተከናወኑ አንዳንድ ክስተቶች ላይ ያተኮረ ነበር። ግንብ በላያቸው ላይ በተደረመሰ ጊዜ የሞቱትን አሥራ ስምንቱን ሰዎች አሁንም እያስታወሱ፣ ጲላጦስ ስለ ገደላቸው አንዳንድ የገሊላ ሰዎች ነገሩት (ሉቃስ 13፡1)። እናም ከእነዚህ አሳዛኝ ጉዳዮች ጋር አብሮ የሚሄድ ጥያቄ አለ፣ ለእነዚህ አስከፊ ክስተቶች ተጠያቂው ማን ነው? ምናልባት እነዚያ ሰዎች ከሌሎች ይልቅ ጥፋተኞች ነበሩ እና እግዚአብሔር ቀጥቷቸዋል? ዛሬም የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸው። መጥፎ ዜና ሲከብደን እና በክፉ መንፈስ ፊት ስንቆም አቅም እንደሌለን ሲሰማን ራሳችንን ብዙ ጊዜ እንጠይቃለን፡- ምናልባት ከእግዚአብሔር የመጣ ቅጣት ነው? በማለት እንጠይቃለን። በኃጢአታችን ምክንያት እኛን ለመቅጣት ጦርነትን ወይም ወረርሽኝ አመጣ? እና ጌታ ለምን ጣልቃ አይገባም? እንላለን።

መጠንቀቅ አለብን: ክፉ መንፈስ ሲያስጨንቀን ግልጽነታችንን እናጣለን፣ ለማብራራት ለማንችለው ነገር ቀላል መልስ ለማግኘት መጨረሻ ላይ ጥፋቱን በእግዚአብሔር ላይ እናደርጋለን። እናም ብዙ ጊዜ በጣም መጥፎው ጸያፍ ቃላትን የመጠቀም ልማድ የሚመጣው ከዚህ ነው። በአለም ላይ ያሉብንን መከራዎቻችንን እና እድሎቻችንን ለእርሱ የምንሰጠው ለምን ያህል ጊዜ ነው፣ በእሱ ፈንታ ሁል ጊዜ ነፃ እንድንሆን ለሚተወን እና ስለዚህ ምንም ጣልቃ የማይገባ ፣ ግን ሀሳብ ብቻ የሚሰጠን፣ ሁከትን ​​ፈጽሞ የማይጠቀም ይልቁንም ለእኛ እና ከእኛ ጋር የሚሰቃይ እርሱ ሁሌም ከእኛ ጋር ነው! በእርግጥም ኢየሱስ ለክፋታችን አምላክን ተጠያቂ ማድረግ የሚለውን ሐሳብ እምቢ በማለት አጥብቆ ይሟገታል፡ በጲላጦስ የተገደሉት እና ግንቡ በላያቸው ላይ በወደቀ ጊዜ የሞቱት ሰዎች ከሌሎች ይልቅ ጥፋተኞች አልነበሩም፣ ጨካኝ የሆነ አምልክ ሰላባ አልነበሩም። አምላክ የበቀል አምላክ አይደለም። ክፉ ከቶ ከእግዚአብሔር ሊመጣ አይችልም ምክንያቱም "እንደ ኃጢአታችን አያደርግብንም" (መዝ 103፡10) እንደ ምሕረቱ እንጂ እንደ ሐጢአታችን አይቀጣንም። ይህ የእግዚአብሔር ዘይቤ ነው። በሌላ መንገድ ሊሆን አይችልም። ሁልጊዜም በምሕረት ይይዘናል።

አምላክን ከመውቀስ ይልቅ፣ ኢየሱስ ወደ ራሳችን መመልከት እንደሚያስፈልገን ተናግሯል፡ ሞትን የሚያመጣው ኃጢአት ነው፤ የእኛ ራስ ወዳድነት ግንኙነቶችን ሊያፈርስ ይችላል፣ የእኛ የተሳሳተ እና የጥቃት ምርጫ ክፋትን ሊያመጣ ይችላል። በዚህ ጊዜ ጌታ እውነተኛውን መፍትሔ አቅርቧል፣ እርሱም መለወጥ ነው፡- “ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ” (ሉቃስ 13፡5) ይላል። በተለይ በዚህ የዐብይ ጾም ወቅት አስቸኳይ ጥሪ ነው። ከልባችን እንቀበለው። ከክፉ እንመለስ፣ የሚያታልሉንን ኃጢያት እንተወው፣ ለወንጌል አመክንዮ ክፍት እንሁን ምክንያቱም ፍቅር እና ወንድማማችነት በሚነግስበት ጊዜ ክፋት ከእንግዲህ ስልጣን የለውም!

ኢየሱስ ግን መለወጥ ቀላል እንዳልሆነ ያውቃል፣ እናም ብዙ ጊዜ ተመሳሳይ ስህተቶችን እና ተመሳሳይ ኃጢአቶችን የምንደግም በመሆኑ እዚህ ሊረዳን ይፈልጋል። ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን፣ እናም አንዳንድ ጊዜ መልካም ለማድረግ ያለን ቁርጠኝነት ክፋት የሚገዛ በሚመስልበት ዓለም ውስጥ ከንቱ ሊመስል ይችላል። ስለዚህ ከይግባኙ በኋላ፣ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ትዕግስት በሚገልጽ ምሳሌ ያበረታታናል። እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ትዕግስት ማስታወስ አለብን። በተፈቀደው ወቅት ፍሬ የማታፈራ፣ ግን ያልተቆረጠችውን የበለስን አጽናኝ ምስል ያቀርባል። እሱ ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠዋል፣ ሌላ ዕድል ይሰጠናል። ለእግዚአብሔር መልካም ስም ያለው “የሌላ እድል አምላክ” ሊሆን እንደሚችል ማሰብ እወዳለሁ፡ እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ሌላ እድል ይሰጠናል፣ ሁልጊዜም፣ ሁል ጊዜ። ምህረቱም እንደዛ ነው። ጌታ ከእኛ ጋር የሚሠራው በዚህ መንገድ ነው። ከፍቅሩ አይለየንም። በደግነት አደራውን በድጋሚ ሊሰጠን አይታክትም። ወንድሞች እና እህቶች፣ እግዚአብሔር በእኛ ያምናል! እግዚአብሔር አምኖ በትዕግስት ይሸኘናል፣ የእግዚአብሔር ትዕግስት ከእኛ ጋር ነው። ተስፋ አይቆርጥም፣ ነገር ግን ሁልጊዜ ተስፋን በውስጣችን ያሳድራል። እግዚአብሔር አባት ነው እና እንደ አባት ይጠብቅሃል። ምርጥ አባቶች ያልደረስክበትን ስኬት ብቻ ሳይሆን የሚመለከቱት ነገር ግን ልታፈራ የምትችለውን ፍሬ ነው የሚመለከቱት። ድክመቶችህን አይከታተልም ነገር ግን አቅምህን ያበረታታል። እሱ ባልፈው ነገር ላይ አያተኩርም፣ ነገር ግን በልበ ሙሉነት ስለወደፊትህ ይወራል። ምክንያቱም እግዚኣብሔር ለእኛ እጅግ በጣም ቅርብ ነው።  የእግዚአብሔር ዘይቤ መቀራረብ መሆኑን አንዘንጋ፣ እርሱ በምሕረትና በርኅራኄ የቀረበ ነው። በዚህ መንገድ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው፣ በቅርበት፣ በምሕረት እና በርኅራኄ።

ስለዚህ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በተስፋና በድፍረት እንድትሞላልን፣ የመለወጥንም ፍላጎት እንድታሳድርን እንለምን።

20 March 2022, 11:06

የገብርኤል ብሥራት ጥንታዊ መሠርት የያዘና የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን በማስታወስ በቀን ሦስት ጊዜ ማለትም በንጋት (በአስራሁለት ሰዓት) በቀትር (በስድስት ሰዓት) እንዲሁም በማታ (በአስራሁለት ሰዓት) የሚደገም የጸሎት ዓይነት ሲሆን ጸሎቱ በሚደገምበት ሰዓት ቤተ ክርስቲያንም የመልኣከ እግዚኣብሔርን ደወል በዚሁ ሰዓት ትደውላለች። ይህ ጸሎት መልኣከ እግዚኣብሔር የሚለውን ስያሜ ያገኝው ከጸሎቱ ከመጀመሪያ ስንኝ የእግዚኣብሔር መልኣከ ማርያምን አበሠራት ከሚለው የተወሰደ ሲሆን ጸሎቱ ስለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ይናገራል። ጸሎቱ በሦስት የተከፈሉ አጫጭር ስንኞች ሲኖሩት በእነኚህ በሦስት አጫጭር ስንኞች መሓል ጸጋን የተሞላሽ የሚለው የማርያም ጸሎት ይደገማል። ይህ ጸሎት በሰንበትና በበዓላት ዕለት ልክ በእኩለ ቀን ላይ በዕለቱ ወንጌል ላይ ትንሽ አስተምሮና ገለፃ ከሰጡ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ ላይ ይህንን ጸሎት ይመራሉ። በመቀጠልም በአደባባዩ ላይ የተገኝው ከተለያየ ቦታ ለንግደት የመጣውን ሕዝብ ሰላምታ ይሰጣሉ።በየትኛውም ጊዜ ከበዓለ ፋሲካ እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ በመልኣከ እግዚኣብሔር ጸሎት ፈንታ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ የሚዘክረውን “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ” የሚለው ጸሎት የሚደገም ሲሆን በመሓል በመሓሉ ጸጋን የተሞላሽ ማርያም ሆይ የሚለው ጸሎት ይታከልበታል።

መልኣኩ ገብርኤል ማሪያምን አበሰራት የሚለው የቀርብ ጊዜ ጸሎት

ሁሉንም ያንብቡ >