ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የእግዚአብሔርን ምሕረት ልባችንን ከፍተን መቀበል ይገባል አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ መጋቢት 18/2014 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በዕለቱ ከሉቃ. 15፡1-3 እና 11-32 ተወስዶ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው የአባካኙን ልጅ ታሪክ ባስታወሱበት የዕለቱ ስብከት፣ የአንድ ሰው ልብ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ በሚሆንበት ጊዜ፣ ሰዎች በሠሩት ኃጢአት ንስሃ ሲገቡ የሚያገኙትን ደስታ መመልከት ይችላል ብለው፣ እኛም ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን ስናገኝ የሚሰማን ደስታ ጎረቤቶቻችንን ማየት የምንችልበት ብርሃን እንዲሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሳምንታዊውን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከመድገማቸው በፊት፣ በዕለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበው፣ “ስለ አባካኙ ልጅ የሚናገረው ይህ የቅዱስ ወንጌል ክፍል፣ እግዚአብሔር ርኅራኄ የተሞላበት ምሕረቱን ሁል ጊዜ እንድሚሰጠን ይተርካል” ብለዋል። በከፋ ኃጢአት ውስጥ ብንወድቅም እንኳ እግዚአብሔር ይቅር እንደሚለን፣ ወደ እርሱ ስንመለስም በደታ እንደሚቀበለን፣ እንደሚወደን እና ወደ እርሱ እስክንመለስ ድረስ የሚጠብቀን መሆኑን ያስተምረናል ብለዋል።

ልባችንን መክፈት ያስፈልጋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀጥለውም፣ አባካኙ ልጅ አባቱን ይቅርታ ሊጠይቀው ከመምጣቱ በፊት የተበላሸ ሕይወት ይኖር እንደነበር አስታውሰዋል። በዚህ ምክንያት ከፍተኛ ንዴቱን የገለጸው የታላቅ ወንድሙ አመለካከት በሁላችንም ዘንድ ያለ መሆኑን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጠቁመው፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት፣ ግዴታውን እና ትእዛዛቱን በማክበር ላይ ብቻ እንደተመሠረተ በማመን፣ ወሰን የሌለው ምሕረቱን፣ ርህራሄውን እና አባታዊ ፍቅሩን እንዘነጋለን ብለዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ተመልክተን ግትርነታች ከእርሱ በማራቅ የሚያስከትለውን አደጋ ማየት መቻል አለብን ብለዋል።

ደስተኞች መሆን

በምሳሌው ላይ አባት አባካኙን ልጅ ለመቀበል ልቡን እንደከፈተ ሁሉ ታላቅ ወንድሙም ልቡን እንዲከፍትለት ሲማጸነው፥ “ሞቶ የነበረው ወንድምህ ሕያው ሆኖ ሲመጡ ደስ ሊትሰኝ ይገባ ነበር” ማለቱን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። እኛም ደግሞ ለአፍታ ያህል በዚህ ላይ በማሰላሰል፣ እግዚአብሔር በልባችን ውስጥ ልንይዛቸው የሚፈልጋቸው ሁለት ነገሮች እንዳሉ፣ እነርሱም፥ “ሌሎችን ማስደሰት እና እኛም መደሰት” መሆናቸውን ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

በኃጢአታቸው ወደ ሚጸጸቱ ሰዎች መቅረብ

“ለሌሎችን ማስደሰት” ማለት ንስሐ ለሚገቡ ወይም በሂደት ላይ ለሚገኙ ሰዎች፣ በችግር ውስጥ ለሚገኙት እና ከእኛ ርቀው ላሉትም ሰዎች ቅርብ መሆናችንን ማሳየት እንደሆነ ያስረዱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ይህን በማድረጋችን የራሳችንን ስህተት በማስታወስ የራሳችንን ፍርሃት እና ተስፋ መቁረጥን በተሻለ መንገድ መቋቋም እንችላለን ሲሉም አክለው አስረድተዋል። እንደ አባት በመሆን፣ ከሰዎች መራቅ እና ኩነኔ የማይረዳ መሆኑን ተገንዝበን ሰዎችን መቀበል እና ብርታትን ልንሰጥ ይገባል ብለዋል። ከእኛ ርቀው የሚገኙትን መቅረብ፣ አብረናቸው ልንሆን፣ ልናበረታታቸው እና ከኃጢአታቸው ተመልሰው ወደ መልካምነት ሲለውጡ አብረናቸው ልንደሰት ያስፈልጋል ብለዋል።

የሰዎች ልብ እግዚአብሔርን መምሰል ያስፈልጋል

በተጨማሪም እኛም "መደሰት አለብን" ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ልባችን በእውነት "እግዚአብሔርን የሚመስል" እና የአንድን ሰው የንስሐ ሕይወት የምንመለከት ከሆነ፣ ኃጢአቶቹ የቱንም ያህል ከባድ ቢሆኑ ጣቶቻችንን እየቀሰርን መቆየት እንደማንችል፣ ነገር ግን በተመረጠው በጎ ነገር አብረን ልንደሰት እንደሚገባ እና በዚህም ከሌሎች ጋር እንዴት መደሰት እንደምንችል መማር አለብን ብለዋል። "እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔርን ምሕረት እንዴት መቀበል እንደምንችል እንድታስተምረን፣ ይህም ጎረቤቶቻችንን የምናይበት ብርሃን ይሁንልን” በማለት፣ መጋቢት 18/2014 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች ያቀረቡትን አስተንትኖ ደምድመዋል።   

28 March 2022, 17:05