ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከሰኔ 28 እስከ ሰኔ 30\2014 ዓ. ም. ድረስ በደቡብ ሱዳን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከሰኔ 28 እስከ ሰኔ 30\2014 ዓ. ም. ድረስ በደቡብ ሱዳን  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በደቡብ ሱዳን የሚያደርጉትን ጉብኝት የሚገልጽ አርማ ይፋ ተደረገ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሰኔ 28 እስከ ሰኔ 30\2014 ዓ. ም. በደቡብ ሱዳን የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚገልጽ አርማ መዘጋጀቱ ታውቋል። በዮሐ. ም. 17፤23 ላይ “እኔ የምለምነው፣ እኔ በእነርሱ፣ አንተም በእኔ እንደሆንክ እነርሱም በፍጹም አንድ እንዲሆኑ ነው” የሚል መሪ ጥቅስን የያዘው አርማ የወይራ ቅርንጫፍ የያዘ የርግብ ምስልንም ያካተተ መሆኑ የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከሰኔ 28 እስከ ሰኔ 30\2014 ዓ. ም. ድረስ በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ ከሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት አስቀድመው ከሐምሌ 25 እስከ ሐምሌ 28/2014 ዓ. ም. ድረስ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ ውስጥ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የቅዱስነታቸው 37ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት መርሃ ግብር በመጥቀስ የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ አስታውቋል። ከዮሐ. 17፤ 23 ላይ የተወሰደው የኢየሱስ ክርስቶስ ክህነታዊ ጸሎት ቅዱስነታቸው በደቡብ ሱዳን ለሚያደርጉት መሪ ጥቅስ እንዲሆን ተመርጧል። በደቡብ ሱዳን ሰንደቅ አላማ ቀለማት የተዘጋጀው አርማ በዙሪያው መስቀልን የወይራ ቅርንጫፍን በመያዝ ለሰላም ያለውን ፍላጎት የሚገልጽ የእርግብ ምስል እና ሁለት የሚጨባበጡ እጆችን የያዘ መሆኑ ተመልክቷል።

በአርማው መሃል የሚታዩ ሁለት የሚጨባበጡ እጆች በደቡብ ሱዳን ውስጥ በሚገኙ ጎሣዎች መካከል እርቅ እንደሚያስፈልግ፣ በቀኝ በኩል የሚታየው የመስቀል ምልክት የአገሪቱን ክርስቲያናዊ ቅርሶች እና የመከራ ታሪኳን የሚያመለክት፣ ከመስቀሉ ቀጥሎ የሚነበበው “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በደቡብ ሱዳን” የሚል ጽሑፍ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሰኔ 28 እስከ ሰኔ 30\2014 ዓ. ም. በደቡብ ሱዳን የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚገልጽ መሆኑን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ አስታውቋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በደቡብ ሱዳን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋና ዓላማ ከሁሉ አስቀድሞ በእርስ በእርስ ጦርነት በርካታ የሰው ሕይወት በጠፋባት እና ንብረት በወደመባት ደቡብ ሱዳን ሰላምን እንዲያወርድ ከመላው የአገሪቱ ሕዝብ ጋር ጸሎታቸውን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ለማቅረብ እና ይህም ለአገሪቱ ሰላም ከፍተኛ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ነጻነቷን እ. አ. አ. በ2011 ዓ. ም. በተቀዳጀች ደቡብ ሱዳን ውስጥ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ታሪካዊ እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን፣ ሚያዝያ 3/2011 ዓ. ም በቫቲካን በተደረገው የደቡብ ሱዳን መሪዎች የሰላም ውይይት መሐል መሪዎቹ እርቅ እና ሰላም እንዲያወርዱ በማለት ቅዱስነታቸው ተንበርክከው መጠየቃቸው ይታወሳል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሁለቱ የአፍሪካ አገራት ማለትም በዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ ኮንጎ እና በደቡብ ሱዳን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለሁለቱም አገራት የሰላም ጥረት ትልቅ እገዛን እና ድጋፍ የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል።

24 March 2022, 16:22