ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኮንጎ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት አርማ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኮንጎ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት አርማ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኮንጎ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት አርማ ይፋ ሆነ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአፍሪካዊቷ አገር ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ ከሐምሌ 25-28/2014 ዓ. ም. ድረስ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚገልጽ አርማ እና መሪ ጥቅስ ይፋ መሆኑ ተነገረ። የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት መሪ ቃል “ሁሉም በኢየሱስ ክርስቶስ ታረቁ” የሚል ሲሆን በተዘጋጀው አርማ ውስጥ የዴሞክራሲያዊት ኮንጎ መልክዓ ምድርን እና ቅዱስነታቸው ለአገሩ ሕዝብ የሚያቀርቡትን ቡራኬ የሚያሳይ ምስል በአርማው መካከተቱ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሐምሌ 25-28/2014 ዓ. ም. ድረስ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ ውስጥ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ዋና ከተማዋ ኪንሻሳን እና ጎማ ከተማን እንደሚጎበኟቸው ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደዚያች አገር የሚያደርጉት ጉብኝት 37ኛው ዓለመ አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚሆን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ የቅዱስነታቸውን ሐዋሪያዊ ጉብኝት አርማ ትናንት ይፋ ባደረገበት ወቅት አስታውቋል። የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት አስተባባሪ ኮሚቴ እንዳብራራው አርማው የአገሪቱን ካርታ የሚያሳይ ሲሆን በውስጡ የሚገኙት ማብራሪያዎችም በአገሪቱ የባንዲራ ቀለማት የተገለጹ መሆናቸን አስታውቋል።

ካርታው በአገሪቱ የሚገኙ አንዳንድ የብዝሃ ሕይወት አካላትን የሚያመለክት ሲሆን፣  ለዚህ ታላቅ ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያስገኘውን ፍሬ ለማሳየት በምዕራቡ የአገሪቱ ክፍል ክፍት ሆኖ የተሳለ መሆኑ ታውቋል። በተጨማሪም የባንዲራው ቀለሞች በጥበብ የተከፋፈሉ እና ገላጭ መሆናቸው ታውቋል። በአርማው ውስጥ የታየው ቢጫ ቀለም በሁሉም መልኩ የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ አንጡራ ሃብትን፥ እንስሳትን፣ ዕፅዋትን እና መልክዓ ምድራዊ ገጽታን የሚወክል መሆኑ ታውቋል። ቀይ ቀለም አሁንም በምስራቁ የአገሪቱ ክፍል እንደሚታየው የሰማዕታቱን ደም ለመግለጽ የታሰበ መሆኑ ታውቋል። በአርማው ላይኛው ክፍል የታየው ሰማያዊው ቀለም እያንዳንዱ የኮንጎ ዜጋ ለሰላም ያለውን ጥብቅ ፍላጎት ለመግለጽ የተቀመጠ መሆኑ ታውቋል።

በግራ በኩል በሰማያዊ ቀለም የተገለጸው መስቀል የኮንጎ ህዝብ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያለውን አክብሮት ለመግለጽ የታሰበ፣ የኮንጎ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የመላውን ህዝብ ፀሎት ወደ ክርስቶስ እንደምታቀርብ የሚያሳይ መሆኑ ታውቋል። በአርማው ላይ የሚታዩ ሦስቱ ሰዎች የወንድማማችነት ምልክት፣ ወንዶች እና ሴቶች፣ ጎልማሶች እና ልጆች በኅብረት ተዋደው እንዲኖሩ የሚያሳስብ ሲሆን በመስቀሉ ስር የሚታየው ይህ ምስል ወንድማማችነትን ለመግለጽ እና ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ብቻ እንደሆነ የሚገልጽ መሆኑ ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ የኮንጐ ሕዝብ የኢየሱስ ክርስቶስ ተወካይ እና የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በኅብረት ለመቀበል መዘጋጀታቸውን የሚያሳይ መሆኑ ታውቋል።

በተጨማሪም በኮንጎ ታሪክ ውስጥ ሥር የሰደደ የሰማዕትነት ጽንሰ-ሀሳብን የሚያመለክት የዘንባባ ዛፍ ድልን፣ ዳግም መወለድን እና አለመሞትን የሚገልጽ፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳስት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት የቀረበውን የተስፋ መልእክት ያመለክት መሆኑ ታውቋል። በመጨረሻም በኮንጎ ካርታ እና በቅዱስ መስቀል መካከል የሚታየው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ምስል ቅዱስነታቸው ለኮንጎ አገር ያበረከቱትን ተግባር እና ታላቅ ደስታ ምልክት የሚገልጽ መሆኑ ታውቋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት አስተባባሪ ኮሚቴው በተጨማሪም በአገሪቱ ግዛት ውስጥ የሚገኙትን የብዝሀ ሕይወት አካላትን በመዘርዘር፣ ተራራዎችን በተለይም እሳተ ጎመራ የሚገኝበት ምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍልን እና የጎማ ግዛት ሕዝብን በአርማው አስታውሷል። ከዚያም የሀገሪቱን የውሃ ሀብት፣ የኮንጎ ወንዝን እና በልዩ ልዩ ቦታዎች የሚገኙ ሐይቆችም ተመልክተዋል።  አጠቃላይ እፅዋት እና የምድራችንን ልዩ ባህሪ የሚገልጹ፣ ኦካፒ የተባለ ግማሽ የሜዳ አህያ እና ግማሽ ቀጭኔን የሚመስል፣ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ ብቻ የሚገኝ ልዩ አውሬ የተመለከተ መሆኑ ታውቋል። 

15 March 2022, 16:46