ፈልግ

108ኛው የአለም የስደተኞች እና የጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን መሪ ቃል ይፋ መሆኑ ተገለጸ። 108ኛው የአለም የስደተኞች እና የጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን መሪ ቃል ይፋ መሆኑ ተገለጸ። 

108ኛው የአለም የስደተኞች እና የጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን መሪ ቃል ይፋ መሆኑ ተገለጸ።

በቫቲካን የቅድስት መንበር የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማትን በማስተዋወቅ ላይ የሚገኘው ጳጳሳዊ ምክር ቤት የዘንድሮውን የ108ኛውን የዓለም የስደተኞች እና የጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን መሪ ቃል ይፋ አድርጓል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ በመጪው መከረም 25/2022 ዓ.ም የሚከበረውን 108ኛው የዓለም የስደተኞች እና የጥገኝነት ጠያቂዎች አለም አቀፍ ቀን መሪ ቃል "መጻይ ጊዜያችንን ከስደተኞች እና ከጥገኝነት ጠያቂዎች  ጋር መገንባት" የሚለውን መሪ ቃል መምረጣቸው በቫቲካን የቅድስት መንበር የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማትን በማስተዋወቅ ላይ የሚገኘው ጳጳሳዊ ምክር ቤት ገልጿል።

ቀኑ በየአመቱ በመስከረም ወር የመጨረሻ እሁድ የሚከበረው ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ለማደረግ እና እየደረሰባቸው የሚገኘውን አደጋ ለዓለም ይፋ ለማድረግ፣ በአለም ዙሪያ ያሉ ካቶሊኮች በግጭት እና በስደት የተፈናቀሉ ወገኖችን እንዲያስታውሱ እና እንዲጸልዩ ለማበረታታት እና ለስደተኞች የሚያቀርባቸው እድሎች በተመለከተ የተለያዩ ዝግጅቶችን በማደረግ እንደ ሚከበር ተገልጿል። የዓለም የስደተኞች እና የጥገኝነት ጠያቂዎች አለም አቀፍ ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ የተከበረው እ.አ.አ 1914 ዓ.ም ነበር።

107ኛ ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን መስከረም 16/2013 ዓ. ም. በቫቲካን በተከበረበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓለም የበለጠ እንዲተባበር መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለ107ኛ ጊዜ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን ምክንያት በማድረግ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ካቶሊካዊ ምዕመናን ከመኖሪያቸው ለተሰደዱት በሙሉ ልባቸውን እና ቤቶቻቸውን እንዲከፍቱ አደራ ማለታቸው ይታወሳል። በዕለቱ ባቀረቡት ስብከትም ጭፍን ጥላቻንና ፍርሃትን አስወግደው በመቀራረብ በኅብረት እንዲጓዙ፣ በማኅበረሰቡ መካከል ተጋላጭ ወደሆኑት፣ ስደተኞች፣ ጥገኝነት ጠያቂዎች፣ ተፈናቃዮች፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች እና ብቻቸውን ወደቀሩት በመቅረብ ዕርዳታቸውን እንዲያቀርቡላቸው ጠይቀው፣ እያንዳንዱ ሰው ማንንም ወደ ጎን ያማያደርግ ሁሉን አቀፍ ማኅበራዊ ሕይወት ለመኖር መጠራቱን አስረድተዋል። 

ስደተኞችን የማቋቋሚያ ዕቅዶች

በጣሊያን የዕርዳታ ድርጅት አማካይነት በርካታ ካቶሊካዊ የዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ዓለም አቀፍ የስደተኞችንና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀንን ማስታወሳቸው ታውቋል። መስከረም 16/2013 ዓ. ም በተከበረው በዓል ላይ ተካፋይ የሆኑት በርካታ ሰዎች፣ በቅድስት መንበር የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መምሪያ ክፍል ምክትል ዋና ጸሐፊ ከሆኑት ከብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ እና ከክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ ጋር በመሆን በቫቲካን ወደሚገኝ ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የእግር ጉዞ አድርገዋል።

ለስደተኞች ትኩረት መስጠት

ብጹዕ አቡነ ሮበርት ቪቲሎ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ዕለቱን በማስመልከት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለፈው ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ ይፋ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ቤተክርስቲያን እና የሰው ልጅ በሙሉ ከብቸኝነት ይልቅ የአንድነት ጎዳናን መጓዝ እንዳለባቸው ማሳሰባቸው ይታወሳል። በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተለይም በካቶሊካዊያን ምዕመናን ዘንድም መከበሩ አስፈላጊ እንደሆነ ብጹዕ አቡነ ሮበርት ቪቲሎ ገልጸው፣ ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን ስደተኛን በክብር ተቀብሎ የማስተናገድ ሃላፊነት አለብን ብለዋል። 

ድንበሮችን ከመዝጋት ይልቅ ጥያቄአቸውን መመለስ

በወቅቱ “በርካታ ማኅበረሰብ የሌላ አገር  ዜጎችን ተቀብለው ለማስተናገድ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተመልክተናል” ያሉት ብጹዕ አቡነ ሮበርት፣ በዓለም ዙሪያ በርካታ አገሮች ድንበሮቻቸውን በመዝጋት ለአደጋ የተጋለጡ ሰዎች የሚያቀርቡትን የሕይወት አድን ዕርዳታ ጥያቄን ውድቅ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። የሰሜን አሜሪካ ድንበሮች ለስደተኞች ዝግ በመሆናቸው ምክንያት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው፣ በቅርቡ በሜክሲኮ ስደተኞች ላይ የተወሰደው እርምጃ ትክክል አለመሆኑንም ተናግረዋል።

ስደተኞችን በመርዳት ካቶሊኮች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ

ብጹዕ አቡነ ሮበርት አክለውም፣ ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ ድርጅቶች እና ሌሎች የቤተክርስቲያኒቱ ድርጅቶች በስደት ላይ የሚገኝ የዓለም ሕዝብ በመርዳት በቀዳሚነት መጠቀሳቸውን አስታውሰው፣ ካቶሊካዊ ድርጅታቸው ከግለሰቦች እና ከሌሎች መንግሥታትዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት  የሚያገኘው የሰብዓዊ ዕርዳታ መጠን መመናመኑ ችግር መፍጠሩን ገልጸዋል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ካቶሊካዊ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መርጃ ድርጅቶችን ማገዝ፣ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ያጡትን ሰብዓዊ ክብር መልሰው እንዲያገኙ ያግዛቸዋል ብለዋል።   

የዓለም የስደተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አነሳሽነት የተመሰረተ የመታሰቢያ ቀን ሲሆን በእዚህም ቀን በዓለማችን የሚከሰቱትን ጦርነቶች እና ብጥብጦች ለሚሸሹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦች ላይ የሚደርሰውን መከራ እና ስቃይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ለዓለም ለማሳወቅ በማሰብ የሚከበር በዓል ነው።

ተስፋ፣ መተማመን እና ወንድማማችነት የሚሉት ሦስት ቃላት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡ ቡኃላ ስድተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ጉዳይ በተመለከተ በተደጋጋሚ የተናገሩዋቸው ቃላት እንደ ሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በዓለም ደረጃ 66 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ከገዛ ሀገራቸው በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ተፈናቅለው እንደ ሚኖሩ ይታወቃል። ይህ መፈናቀል የተከሰተው በጦርነት፣ በብጥብጥ፣ በተለያዩ ማኅበራዊ፣ ፖሌቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተነሳ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ካወጣው ዘገባ ለመረዳት ተችሏል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥር ወር 07/2010 ዓ.ም ላይ አለም አቀፍ የስደተኞች ቀን መዘጋጅ ይሆን ዘንድ በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት “የእኛን በር የሚያንኳኳ እያንዳንዱ እንግዳ ኢየሱስን ለመገናኘት እንችል ዘንድ እድሉን ይከፍትልናል” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን “ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን መቀበል፣  መጠበቅ፣ ማብቃት እና ማዋሃድ" ያስፈልጋል በማለት በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው ቀደም ባሉ ጊዜያት  ባደርጉት ስብከት እንደ ገለጹት በሮቻችንን  እያንኳኩ የሚገኙ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ማስታወስ እና ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንደ ሚገባ በማውሳት  “ስደተኞችን ተቀብሎ ማስተናገድ ከኢየሱስ ጋር የመገናኘትን አጋጣሚ እንደ ሚከፍት “ይህም ሁሉም ሊያውቀው እና ሊወጣው የሚገባው የመበዤያ ወይም ድህነት ሊያመጣ የሚችል ተግባር መገለጫ ነው” ማለታቸውም ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው በተደጋጋሚ ብዙ የዓለም ሀገራት ድንበሮቻቸውን ለስደተኞች ዝግ እያደርጉ መምጣታቸውን መገለጻቸው የሚታወስ ሲሆን ብዙዎች ሀገራት ይህንን የሚያደርጉት ስደተኞ አንድ ጊዜ ወደ ሀገራቸው ከገቡ ተቀብሎ የሚያስተናግዳቸውን ሀገር ባሕል እና ማኅበራዊ ሁኔታ እና እሴት ተቀብለው ለመኖር ስለሚቸገሩ መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች ቅዱስነታቸው መገልጻቸው የሚታወስ ሲሆን “ስደተኞችን ተቀብለው የሚያስተናግዱ ሀገራት ሕዝቦች “እነዚህ አዲስ የሚመጡ ሰዎች የነበረውን ማኅበራዊ መዋቅራችንን እና ልምዶቻችንን ያበላሻሉ የሚል ፍርሃት ስላላቸው መሆኑን ገልጸው፣ አንዳንዴም ባስ ሲል ሁሉም ሌቦች፣ እና ቀማኞች ናቸው የሚል እመንት በመያዛቸው የተነሳ፣ ያገሏቸዋል፣ የጸየፏቸዋል፣ ከሀገራቸውም እንዲወጡ የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት ያደርጋሉ” ማለታቸው ይታወሳል።

“እነዚህ  በሰብአዊ አዕምሮ ልንረዳቸው በምንችለው ጥርጣሬዎች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ጥርጣሬ እና ፍራሃት በራሱ ኃጢኣት አይደለም። ይህ ተግባር ኃጢኣት የሚሆነው ግን እነዚህ ጥርጣሬዎች እና ፍርሃቶች ለስደተኞች የምንሰጠው መልስ ላይ ተጽኖ ሲያደርጉ፣ እንዳንለግስ እጆቻችንን የሚይዙ ከሆነ፣ ጥላችን እና ክፋትን እንድናስብ ሲያደርጉን ነው” ማለታቸው  ይታወሳል።

23 February 2022, 12:50