ፈልግ

የጎዳና ተዳዳሪነት ሕይወት የጎዳና ተዳዳሪነት ሕይወት 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ዕድገት በሰዎች ብልጽግና እንጂ በትርፍ መጠን መለካት የለበትም አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሮም ከተማ በሚገኝ የላቴራን መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ትናንት ጥር 4/2014 ዓ. ም. “መጭውን ማኅበራዊ ሕይወት ማሳመር እና ሁሉን አቀፍ ዘላቂ ኤኮኖሚን መገንባት” በሚል ርዕሥ ለተካሄደው ስብሰባ መልዕክት ማስተላለፋቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው እድገት በሰዎች ብልጽግና እንጂ በትርፍ መጠን መለካት የለበትም ብለዋል። ስብሰባውን በጋራ ያዘጋጁት በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ መምሪያ እና ዴሎይት የተሰኘ ኅብረት መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የዓላማ መግለጫዎችን ማውጣት ሳይሆን ኢኮኖሚ እና ፋይናንስ በሰዎች እና በጋራ ምድራችን አገልግሎት ላይ እንዲሆኑ ተጨባጭ ቁርጠኝነት ሊኖር ይግባል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ እድገት መለካት ያለበት ከድህነት ሕይወት የሚያላቅቅ ተገቢ ሥራ ባላቸው ሰዎች ብዛት እንጂ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚገኝ ትርፍ መጠን መሆን እንደሌለበት አስረድተዋል።

የሞዴል ለውጥ እና የጋራ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “መጭውን ማኅበራዊ ሕይወት ማሳመር እና ሁሉን አቀፍ ዘላቂ ኤኮኖሚን መገንባት” በሚል ርዕሥ የተካሄደውን ስብሰባ ለተካፈሉት አባላት መልዕክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን፣ የስብሰባውን መድረክ ያዘጋጁት በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ መምሪያ እና ዴሎይት የተሰኘ ኅብረት መሆናቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፣ ለወደፊት ሕይወት ለመዘጋጀት አሉ የተባሉትን ሳይንሳዊ የምርምር ውጤቶችን በመጠቀም ከወንጌል እውነታ ጋር በማጣመር ከማኅበረሰቡ መካከል የተገለሉት ማካተት እንደሚገባ አስረድተዋል። ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ ማኅበራዊ ሕይወታችን የተለየ ይሆናል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በርካታ ማኅበራዊ የእድገት ዕቅዶቻችን ተለውጠዋል ብለዋል። ለጋራ መኖሪያ ምድራችን የሚደረገውን እንክብካቤ ጨምሮ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት መርሃ ግብር፣ የረሃብ እና የድህነት መስፋፋት እንዲሁም ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ግብይቶችን እንደ ምሳሌ ጠቅሰዋል። ይህ በመሆኑ በእድገት ሞዴል ላይ ለውጥ በማካሄድ የጋራ ቁርጠኝነት ማሳየት እንደሚያስፈልግ እና ፈጠራ የታከለባቸው አዳዲስ መፍትሄዎችን ማግኘት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። የኤኮኖሚ እና ፋይናንስ ተቋማት ወሳኝ ኃላፊነት እንዳለባቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በእነዚህ ዘርፎች የተሰማሩት ተቋማት ተባብረው ድህነትን መዋጋት እና የሥራ ዕድሎችን በማመቻቸት አገልግሎታቸውን ለሰው ልጅ እድገት እና ለጋራ መኖሪያ ምድራችን ማዋል ይገባል ብለዋል። ይህን ለማረጋገጥ ሁሉም ሰው በመተባበር የበኩሉን አስተዋጽዖ ማበርከት እንዳለበት እና ዓለምን በሥራ መለወጥ እንደሚገባ አሳስበዋል። ይህ ተግባራዊ ከተደረገ እና ሃላፊነት ተወስዶ ከተሠራበት መጭውን ማኅበራዊ ሕይወት ማስተካከል ይቻላል ብለዋል። ሮም ከተማ በሚገኝ የላቴራን ስብሰባ አዳራሽ ጥር 4/2014 ዓ. ም. የተጀመረው የኤኮኖሚ ባለሙያዎች ስብሰባ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየተሠራበት የነበረው የኤኮኖም እና ማኅበራዊ ሥርዓቶች ደካማነት ገሃድ በማድረግ ወረርሽኙ በዓለማችን ያስከተለው ቀውስ የማኅበራዊ ሕይወት አቅጣጫን መቀየሩን ገምግሞ ለተፈጥሮ እና ለሰው ልጅ ማኅበራዊ ሕይወት ልዩ ዋጋ ሊሰጠው እንደሚገባ ተመልክቷል።   

አዲስ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት

ዛሬ በዓለማችን ውስውጥ የታየው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ የማኅበራዊ ሕይወት መዛባት መኖሩን የሚገልጽ የረጅም ጊዜ ምልክት ነው ያሉት፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት  ጊዜያዊ ሃላፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ፣ በስብሰባው ማክፈቻ ላይ ባሰሙት ንግግር፣ ወረርሽኙ ትርፍን የመሰብሰብ ዓላማን በማስወገድ አዲስ የአመለካከት ለውጥ እንድናደርግ የሚያሳስብ ጥሪ እና ኤኮኖሚያዊ እድገትን ብቻ የሚያስቀድም የአንድ አቅጣጫ ልኬት በማለት ገልጸዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት በማስታወስ ንግግር ያደረጉት ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል፣ ከዚህ ድንገተኛ አደጋ በጽናት ለመውጣት ከፈለግን አማራጭ የአስተሳሰብ መንገዶችን መከተል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ለወደፊት ማኅበራዊ ሕይወት የመዘጋጀት እሳቤ፣ ፈጠራዎቻችንን ከዚህ በፊት ተጠቅመን በማናውቃቸው መንገዶች እንድንጠቀም እና ከዚህ የችግር ጊዜ በኋላ አዲስ ዜዴን እንድንፈልግ የሚያሳስበን ሲሆን ይህም የሚጀምረው ከስር ነቀል፣ ሁሉን አቀፍ የሥርዓት ለውጥ ጋር መሆኑን ገልጸው፣ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን ልዩ ትኩረት በመስጠት ሁላችሁንም በሰላም የምንኖርበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ በመግለጽ አስተያየታቸውን አጠቃልለዋል።

የሃብቶችን ለተሻለ ጥቅም ማዋል

የስብሰባው ተካፋዮች በአስተያየታቸው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ለረጅም ጊዜ የቆየውን ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ አለመመጣጠንን ጉልህ እንዳደረገው ተናግረው፣ ኤኮኖሚያዊ ተቋማት የተሻለ የወደፊት ሕይወት ለማምጣት ከሚያደርጉት ሚና ጋር ሊከተሏቸው የሚገቡትን መፍትሔዎች በመፈለግ፣ ሁሉን የሚያካትቱ አዳዲስ የመፍትሄ ሃሳቦችን ማግኘት ያስፈልጋል በማለት አስተያየታቸውን ገልጸዋል።    

የጋራ መኖሪያ ምድራችን እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች

ስብሰባው በዓለማች ውስጥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን ሊደረግ የሚገባው እንክብካቤ እና ጥበቃ ከፍተኛ እንደሆነ በሚገባ ያመላከተ ሲሆን፣ የጋራ እሴቶችን የመከላከል አቅማችን ለእያንዳንዱ ሰው ደህንነት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝቧል። ከዚህም ጋር በማዛመድ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመልካም የወደፊት ሕይወት እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል እና ቴክኖሎጂዎቹ የጋራ ሀብቶችን ለሁሉ ሰው በማመቻቸት እኩልነትን ለማምጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦን ማበርከት እንደሚችሉ ተበራርቷል። በጳጳሳዊ አካዳሚ የማኅበራዊ ሳይንስ ፕሬዚደንት የሆኑት ፕሮፌሰር ስቴፋኖ ዛማኚ ለስብሰባው ተካፋዮች ባቀረቡት ጽሑፋቸው፣ ኢኮኖሚው ከማኅበራዊ እና አካባቢያዊ እይታ ጋር ወንድማማችነት ከማሳደግ አንጻር ዘላቂ መሆን አለበት ብለዋል። በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ መምሪያ አስተባባሪ የሆኑት እህት አሌሳንድራ ስሜሪሊ በበኩላቸው ሰላም እና ተግባር የሚሉ ቃላት የኢኮኖሚ ስርዓቶችን ለማሻሻል በሚደረግ ሂደት ውስጥ አንድ አካል ሊሆኑ ይገባል ብለዋል። 

13 January 2022, 15:38