ፈልግ

ለክርስቲያኖች አንድነት የተደረገ የጸሎት ሳምንት መዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ለክርስቲያኖች አንድነት የተደረገ የጸሎት ሳምንት መዝጊያ ሥነ-ሥርዓት   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ምዕመናን ለክርስቲያን አንድነት በሚደረግ ጸሎት ላይ እንዲሳተፉ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዘንድሮ ከጥር 10-17/2014 ዓ. ም. ድረስ ለክርስቲያኖች አንድነት በሚደረግ የጸሎት ሳምንት ምዕመናን እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበው፣ እያንዳንዱ ክርስቲያን ለአንድነት ሲል የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሦስቱን ሰብዓ ሰገሎችን ያሳታወሰው የዘንድሮ የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ከጥር 10-17/2014 ዓ. ም. ድረስ የሚከናወን መሆኑ ታውቋል። መሲሁን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለማመስገን ከምሥራቅ ወደ ቤተልሔም የመጡት ሰብዓ ሰገሎች “ኮከቡን በምስራቅ አይተን ልንሰግድለት መጣን” ማለታቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰው፣ በተመሳሳይ መንገድ የተለያየ አስተዳደግና የአምልኮ ሥርዓት ያለን ክርስቲያኖች ትኩረታችንን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የምናደርግ ከሆነ ግባችን ወደ ሆነው ሙሉ አንድነት መቅረብ እንችላለን ብለው፣ ክርስቲያኖች በሙሉ ጥረታችን በመካከላችን አንድነትን ለማምጣት እንዲሆን በማለት ብርታትን ተመኝተውልናል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመላው ዓለም ዘንድሮ ከጥር 10-17/2014 ዓ. ም. ድረስ የሚከበረውን የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ሮም በሚገኝ ቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ጥር 17/2014 ዓ. ም በሚደረግ የምሽት ጸሎት ላይ ተገኝተው የሚዘጉት መሆኑን የጸሎት መርሃ ግብሩ አስታውቋል። የር. ሊ. ጳጳሳት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት አስተባባሪ እና አዘጋጅ ጽሕፈት ቤት ዓርብ ጥር 6/2014 ዓ. ም. እንዳስታወቀው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሮም ከተማ በሚገኝ ቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ተገኝተው የመዝጊያ ጸሎት ሥነ ሥርዓትን እንደሚመሩ ገልጾ፣ አምና ባጋጠማቸው የጤና ማነስ ምክንያት በመዝጊያው ጸሎት ሥነ ሥርዓት ሊገኙ አለመቻላቸውን አስታውሷል።

በየዓመቱ ከጥር 10-17 የሚከበር የጸሎት ሳምንት በመላው ዓለም የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን እና የክርስቲያን ማኅበረሰብን የሚያሳትፍ መሆኑ ታውቋል። ለዘንድሮ የቀረበውን የጸሎት ሃሳብ በጋራ የመረጡት የመካከለኛው ምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት እና በጳጳስዊ ምክር ቤት የክርስቲያኖችን አንደነት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት መሆናቸው ታውቋል። ሁለቱ ምክር ቤቶች በጋራ ባቀረቡት የጸሎት ሃሳባቸው ከምሥራቅ ተነስተው ወደ ቤተልሔም የመጡ ሦስቱን ሰብዓ ሰገል ልምድ ገልጸው፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ክርስቲያኖች በሙሉ በሳምንቱ የጸሎት ቀናት ለዕለቱ በተመደበው የጸሎት ጭብጥ ላይ በማስተንተን ጸሎታቸውን እንዲያቀርቡ በማለት ግብዣቸውን አቅርበዋል።

“ኮከቡን በምሥራቅ አይተናል" የሚለው አርዕስት የመጀመሪያ ቀን የጸሎት ሃሳብ መሆኑን የገለጸው የር. ሊ. ጳጳሳት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤቱ፣ የሁለተኛው ቀን የጸሎት ርዕሥም “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?” የሚል መሆኑን አስታውቋል። "ንጉሥ ሄሮድስ ይህን በሰማ ጊዜ ታወከ፣ ኢየሩሳሌምም ከንጉሡ ጋር ሆና ታወከች" የሚለው አርዕስት የሦስተኛው ቀን የጸሎት ሃሳብ መሆኑን ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል። “አንቺም ቤተልሔም… ከምንም አታንሺም” የሚለው የአራተኛው ቀን የጸሎት ሃሳብ እንደሆነ የገለጸው ጽሕፈት ቤቱ፣ ለአምስተኛው የጸሎት ቀን የተመረጠው ርዕሥ “ሰብዓ ሰገሎች ሲወጣ ያዩት ኮከብ ከፊታቸው እየሄደ መራቸው” የሚል መሆኑን አስታውቋል።

የስድስተኛው ዕለት የጸሎት ጭብጥ “ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፣ ተንበርክከውም ሰገዱለት” በሚለው ርዕሥ ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ በሰባተኛው ቀን ሰብአ ሰገል ይዘዋቸው በመጡት ስጦታዎች ላይ እንድናስተነትን የሚጋብዝ እና “ከዚያም ሣጥኖቻቸውን ከፍተው የወርቅ፣ የዕጣንና የከርቤ ስጦታ አቀረቡለት” የሚል ርዕሥ መሆኑን የጸሎት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤቱ ገልጾ፣ መጨረሻም ስምንተኛው እና የመጨረሻው ቀን ትኩረት "በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ" በሚለው ላይ መሆኑን የር. ሊ. ጳጳሳት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

17 January 2022, 16:28