ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሰዎች ላይ የሚፈጸም የጭካኔ ተግባር ሊታወስ ይገባል አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥር 18/2014 ዓ. ም. ያቀረቡትን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮአቸውን ከማጠቃለላቸው በፊት ከዚህ በፊት በዓለማችን የተፈጸሙ አሳዛኝ ታሪኮች የሚዘከሩበትን ዕለት ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው በዓለማችን ውስጥ ከዚህ በፊት በተፈጸሙ አሳዛኝ ታሪኮች ላይ አዲሱ ትውልድ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ ወላጆች እና የትምህርት ቤት መምህራን እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ጭካኔያዊ ተግባራት ከእንግዲህ ወዲህ በዓለማችን መፈጸም የለባቸውም” ያሉት ርዕሠ  ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በተለይም የዘረኝነት እና ፀረ-ሴማዊነት ክፋቶች በአዲሱ ትውልድ መካከል በድጋሚ መከሰት የለበትም ብለው፣ በዓለማችን ከዚህ በፊት የተፈጸሙ ጭካኔያዊ ተግባራት አደጋን እና ሞትን በማስከተል ቤተሰብ ለሐዘን መዳረጉን አስታውሰዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጥር 18/2014 ዓ. ም. በጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ያቀረቡትን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮ ለተከታተሉት ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት፣ ጥር 19/2014 ዓ. ም. በፖላንድ ኦሽዊትዝ-ቢርኬናው የተመሠረተው የሰዎች ማጎሪያ፣ የግድያ እና የስቃይ ካምፕ ነጻ የሆነበት 76ኛ ዓመት የሚታሰብበት ዕለት መሆኑን ገልጸው፣ የወቅቱን አስከፊ ታሪክ አዲሱን ትውልድ ግንዛቤ በማስያዝ ቤተሰቦች እና የትምህርት ቤት መምህራን እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበው፣ "በሚሊዮን በሚቆጠሩ አይሁዶች እና የተለያየ ዜግነት እና ሃይማኖታዊ እምነት ባላቸው ሰዎች ላይ የተፈጸመን ጭፍጨፋ ማስታወስ አስፈላጊ ነው ብለው፣ ይህ አሳዛኝ እና ጭካኔያዊ ተግባር ከእንግዲህ መደገም የለበትም" ብለዋል።   

ለመምህራን እና ለወላጆች ጥሪ ቀርቧል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው በዓለማችን ከዚህ በፊት የተፈጸሙ አሳዛኝ ተግባራትን  ሁሉም ሰው ሊያስታውሰው ይገባል ብለው፣ በተለይም "የትምህርት ቤት መምህራን እና ወላጆች በአዲሱ ትውልድ መካከል ግንዛቤን በማሳደግ፣ በታሪክ ውስጥ ስላለው ጥቁር ገጽታ አስፈሪነት እንዲያስረዱ” በማለት ጥሪ አቅርበዋል። አክለውም የዚህ አስፈሪ እና ክፉ ተግባር ምስክርነት ፈጽሞ እንዳይጠፋ እና እንዳይደበዝዝ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለው፣ ይህን በማድረግ የሰው ልጅ ክብር ዳግም የማይረገጥበትን ጊዜ መገንባት ይቻላል" ብለዋል።

በፖላንድ ኦሽዊትዝ-ቢርኬናው የሚገኝ የሰዎች ማጎሪያ
በፖላንድ ኦሽዊትዝ-ቢርኬናው የሚገኝ የሰዎች ማጎሪያ

ከኦሽዊትዝ ጭፍጨፋ የተረፈች እናት

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጥር 18/2014 ዓ. ም. ያቀረቡትን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮ ካጠቃለሉ በኋላ በፖላንድ ኦሽዊትዝ ማጎሪያ ካምፕ ጭፍጨፋ ከተረፉት፣ የቤላሩስ ተወላጅ ፖላንዳዊት ወ/ሮ ሊዲያ ማክሲሞቪች ጋር ሰላምታ ተለዋውጠዋል። በካምፖች የተፈጸሙ ግፎችን ለመመስከር በሕይወት ካሉት ሰዎች መካከል ወ/ሮ ሊዲያ አንዷ ስትሆን፣ በቫቲካን ውስጥ ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር ስትገናኝ ሁለተኛ ጊዜዋ መሆኑ ታውቋል። ቅዱነታቸው እ. አ. አ ግንቦት 26/2021 ዓ. ም. ባቀረቡት የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮ ዕለትም ወ/ሮ ሊዲያን ማግኘታቸው ይታወሳል። ሊዲያ ትናንት ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር በተገናኘችበት ወቅት፣ የሕይወት ታሪኳን የሚገልጽ መጽሐፍ ጨምሮ በአንድ አጋጣሚ ከቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ መገናኘቷን የሚያሳይ ፎቶግራፍም ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በስጦታ ማበርከቷ ታውቋል።

ከኦሽዊትዝ ጭፍጨፋ የተረፈች እናት ወ/ሮ ሊዲያ ማክሲሞቪች
ከኦሽዊትዝ ጭፍጨፋ የተረፈች እናት ወ/ሮ ሊዲያ ማክሲሞቪች

"አስከፊ እና አሳዛኝ ክስተት"

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለፈው ዓመት ታስቦ በዋለው የዓለማችን አሳዛኝ ታሪኮች መታሰቢያ ቀን ባስተላለፉት መልዕክት፣ "በዓለማችን ውስጥ የሚፈጸሙ አስከፊ እና አሳዛኝ ተግባራትን" ማስታወስ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ እነዚህን ክስተቶች መዘንጋት ተቀባይነት እንደሌለው፣ በዓለማችን ውስጥ ጭካኔያዊ ተግራት በድጋሚ እንዳፈጸሙ ምእመናን መጸለይ እንደሚገባ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

በኦሽዊትዝ ገደል ውስጥ ጸጥታ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ በ 2016 ዓ. ም. በፖላንድ ሐዋርያዊ ንግደት ባደረጉበት ወቅት የኦሽዊትዝ-ቢርኬናው ገደል ከጎበኙ በኋላ ያደረጉት እያንዳንዱ ንግግር የበለጠ ጸጥታ የሰፈነበት ቢሆንም፣ የተሰማቸውን ከፍተኛ ሐዘን በገለጹበት መልዕክታቸው፣ አሳዛኝ እና ጭካኔያዊ ተግባር ከእንግዲህ በምድራችን ውስጥ መደገም የለበትም" ማለታቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በዚህ ሐዋርያዊ ንግደታቸው ቅዱስ ማክስሚሊያን ኮልቤ በማጎሪያ ካምፑ የመጨረሻ ሕይወቱን ያሳለፈበትን ቦታ ከተመለከቱ በኋላ ያቀረቡትን ጸሎት የማጎሪያውን ቦታ አስመልክተው በጻፉት መጽሐፋቸው ውስጥ መጥቀሳቸው ይታወሳል።

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የኦሽዊትዝ-ቢርኬናው ጉብኝት
የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የኦሽዊትዝ-ቢርኬናው ጉብኝት

   

27 January 2022, 15:51