ፈልግ

ጉዳት የደረሰባቸው የቶንጋ ደሴቶች ጉዳት የደረሰባቸው የቶንጋ ደሴቶች 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የቶንጋ ደሴቶች ሕዝቦችን በጸሎታቸው አስታወሱ።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ረቡዕ ጥር 11/2014 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው ጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተገኝተው ሳምንታዊውን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ባቀረቡበት ወቅት ቅዳሜ ጥር 7/2014 ዓ. ም. በተከሰተው ኃይለኛ እሳተ ገሞራ ፍንዳታ ጉዳት የደረሰበት የቶንጋ ደሴቶች ሕዝብን በጸሎታቸው ያስታወሷቸው ሲሆን፣ ፍንዳታው ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ውስጥ ከተከሰቱት ፍንዳታዎች መካከል ከፍተኛው ነው ተብሏል። የቶንጋ ደሴቶች በፓሲፊክ ውቅያኖስ ከሚገኙት ደሴቶች መካከከል መሆናቸው ይታወቃል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለተገኙት ምዕመናን ባሰሙት ንግግር፣ በቶንጋ ደሴቶች ሕዝብ ላይ የደረሰው የሕይወት መጥፋት እና የንብረት መውደም ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ ከደረሰበት አደጋ ሕዝቡን እንዲያወጣቸው እግዚአብሔርን በመለመን ከመላው የአገሪቱ ሕዝብ ጋር በመንፈስ መተባበራቸውን ገልጸዋል። አክለውም ምዕመናን በሙሉ የደሴቶቹን ነዋሪዎች በጸሎት እንዲረዷቸው አደራ ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ አደጋው ከደረሰባቸው የቶንጋ ደሴቶች የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፣ ባሁኑ ጊዜ ወደ ደሴቲቱ በመድረስ አስፈላጊውን ሰብዓዊ ዕርዳታ ማቅረብ አስቸጋሪ መሆኑን አመልክተው፣ የደሴቶቹ  ማኅበራዊ መገናኛ መስመሮች በፍንዳታው የተጎዱ በመሆናቸው ከተቀረው የዓለማችን ክፍል ጋር ለማገናኘት ሳምንታትን እንደሚፈጅ ገልጸዋል። የአካባቢው ባለስልጣናት እንደገለጹት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝም በደሴቶቹ ውስጥ በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን አስረድተዋል።

ለቶንጋ ደሴቶች የሚቀርባሉ የተባሉ የሁለቱ አገራት ማለትም የአውስትራሊያ እና የኒው ዚላንድ ወታደራዊ መርከቦች የመጀመሪያ ዕርዳታ ቁሳቁሶችን ይዘው ወደ ሥፍራው ማምራታቸው ታውቋል። በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት “ዩኒሴፍ” በበኩሉ እንዳስታወቀው፣ አሁን ካሉት አስቸኳይ ችግሮች መካከል አንዱ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሆኑን አስታውቋል።

በፓስፊክ አገሮች የ “ዩኒሴፍ” ተወካይ የሆኑት አቶ ዮናታን ቬይች እንደገለጹት አስፈላጊ የሆኑ የውሃ እና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በፍጥነት ለማድረስ እና ሌሎችንም ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማቅረብ ድርጅታቸው ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል። አብዛኛው የአገሪቱ ክፍል - የ “ዩኒሴፍ” ተወካዩ አቶ ዮናታን ቬይች እንደገለጹት፣  የእሳተ ገሞራው አመድ ከፍታ ከመሬት አንድ ሴንቲ ሜትር እስከ ሁለት ሴንቲ ሜትር እንደሚደርስ ገልጸው፣ ይህም የምግብ አቅርቦትን እንደሚጎዳ እና በአየር ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው አስረድተዋል። በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ቅድሚያ የሚሰጠው የዕርዳታ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

የ “ካሪታስ” ምላሽ

 

በቶንጋ መንግሥት መግለጫ መሠረት በፍንዳታው ለተጎዱት አካባቢዎች አስቸኳይ ዕርዳታን ማቅረብ እንደሚያስፈልግ የገለጹት የአውስትራሊያ እና የኒው ዚላንድ ካቶሊካዊ ዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶች፣ የቶናጋ ደሴቶች አስቀድሞም ቢሆን ንጹሕ የመጠጥ ውሃ እጥረት እንዳለበት ገልጸው፣ የሁለቱ አገሮች የዕርዳታ ድርጅቶች ንጹሕ የመጠጥ ውሃን ለማቅረብ የሚጥሩ መሆኑን በፓሲፊክ አገሮች የአውስትራሊያ ካቶሊክ ዕርዳታ አቅርቦት አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አቶ ዳማሪስ ፌንዲት ገልጸዋል። ድርጅታቸው "ቶንጋን" ከተባለ አቻ የዕርዳታ አቅራቢ ድርጅት ጋር ግንኙነቶችን ለመመስረት እየሞከረ መሆኑን ገልጸው፣ በደሴቶቹ ላይ የደረሰው ውድመት ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል። በቁጥር በርካታ መንገዶች እና ድልድዮች መፍረሳቸውን ያስታወቁት አቶ ዳማሪስ፣ ካሪታስ ቶንጋ ቀደም ሲል በዋና ከተማዋ ኑኩአሎፋ እና ሃአፓይ ውስጥ የአደጋ ጊዜ አቅርቦቶች እንዳለው ገልጸው፣ በመሆኑም ቢያንስ ለአስቸኳይ ፍላጎቶች ምላሽ መስጠት እንደሚቻል ገልጸዋል። በተመሳሳይ መልኩ ከኒው ዚላንድ ካቶሊካዊ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅት የሚወጡ ዘገባዎች እንደገልጹት፣ የቶንጋ ደሴቶችን ከአደጋ ቶሎ እንዲያገግሙ ማድረግ አስቸጋሪ እንደሚሆን አቶ ዳማሪስ ገልጸው፣ የካሪታስ ቶንጋ ቡድን በደሴቶቹ ውስጥ በሚገኙ በጎ ፈቃደኞች ቡድን ድጋፍ የሚያገኝ መሆኑን አስታውቀዋል። ሃሳባቸው እና ጸሎታቸው ከሕዝቡ ጋር መሆኑን ገልጸው፣ የቶንጋ እና በተለይ ከአጋሮቻቸው እና ከአካባቢው ማኅበረሰቦች ጋር ለብዙ ዓመታት ያህል አብረው መሥራታቸውን ገልጸው በአሁኑ ሰዓት ግንኙነቱ በጣም አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን በፓሲፊክ አገሮች የአውስትራሊያ ካቶሊክ ዕርዳታ አቅርቦት አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አቶ ዳማሪስ ፌንዲት ገልጸዋል።

20 January 2022, 10:55