ፈልግ

በቅድስት መንበር የእምነት አስተምህሮ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምልአተ ጉባኤ በቅድስት መንበር የእምነት አስተምህሮ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምልአተ ጉባኤ  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ሕጻናትን ከጥቃት ለማትረፍ የፍርድ እርምጃ ብቻውን በቂ አለመሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ጥር 13/2014 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ ምልአተ ጉባኤያቸውን ለማካሄድ የተሰበሰቡ የእምነት አስተምህሮ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ተወካዮችን ተቀብለው አነጋግረዋል። ቅዱስነታቸው ለጳጳሳዊ ምክር ቤቱ አባላት ባስተላለፉት መልዕክት፣ በውይይታቸው ወቅት በሦስት አበይት ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ማትኮር አስፈላጊ እንደሆነ፣ እነርሱም ሰብዓዊ ክብር፣ ማስተዋል እና እምነት መሆናቸውን ተናግረዋል። አክለውም ቤተክርስቲያን ሕጻናትን ከጥቃት ለማትረፍ የፍርድ እርምጃ መውሰድ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ጳጳሳዊ ምክር ቤቱ የካቶሊክ እምነትን እና ሥነ ምግባርን፣ የቤተክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ትክክለኛነት በማስተዋወቅ እና በመጠበቅ ረገድ ለዓለም አቀፉ ቤተክርስቲያን ጠቃሚ አገልግሎት በማበርከቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ተወካዮች በምልአተ ጉባኤያቸው ወቅት በሦስት ርዕሠ ጉዳዮች፣ ሰብዓዊ ክብር፣ ማስተዋል እና እምነት በሚሉ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ እንዲያስተነትኑባቸው አሳስበዋል።

ሰብዓዊ ክብር

“ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው መግቢያ ላይ፥ "ለመኖር በተሰጠን በዚህ ጊዜ የእያንዳንዱን ሰው ክብር ተገንዝቦ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወንድማማችነትን ማሳደግ ያስፈልጋል” ያሉትን መልዕክት አስታውሰዋል። በዚህ ረገድም፣ ወንድማማችነት ፈጣሪ ለሰው ልጆች የሕይወት ጉዞ መዳረሻ እንዲሆን ከነደፋቸው መንገዶች መካከል አንዱ እና ዋናው “የእያንዳንዱን ሰው ክብር ማወቅ ነው" ሲሉ አስረድተዋል። “በብዙ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ከጤና ጋር በተያያዙ ውጥረቶች” ውስጥ በምንገኝበት ዘመናችን፣ ሌላውን ሰው እንደ “ባዕድ ወይም ጠላት” የመቁጠር ፈተና እየጨመረ መምጣቱን ቅዱስነታቸው ገልጸዋል። ቤተክርስቲያን ተልእኮዋን ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ የሰውን ልጅ የማይገረሰስ ሰብዓዊ ክብር ስታውጅ መኖሯን ገልጸው፣ “በእርግጥም የሰው ልጅ የፍጥረታት ሁሉ ዋና ነው” በማለት ተናግረዋል። ይህን መነሻ በማድረግ፣ አሁኑ ባለው እውነታ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በሰው ልጅ ክብር ላይ ለማስተንተን የጀመሩትን በቅድስት መንበር የእምነት አስተምህሮ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ተወካዮችን ቅዱስነታቸው አመስግነዋል።

ማስተዋል

የጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ተወካዮች በምልአተ ጉባኤያቸው መወያየት ያለባቸው ሁለተኛው ርዕሠ ጉዳይ ማስተዋል እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በአሁኑ ጊዜ የምእመናንን የማስተዋል ጥበብ ማየት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። የአስተዋይነት ልምድ ሁሉንም ዓይነት ጥቃቶች ለመከላከል አስፈላጊ እንደሆነ ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በእግዚአብሔር ዕርዳታ ቤተ ክርስቲያን በአባላቶቿ በደል ለደረሰባቸው ሰዎች ፍትህ ለመስጠት ያላትን ቁርጠኝነት እየተከታተለች መሆኗን ገልጸዋል። በዚህ አንፃር፣ የፍትህ እርምጃዎችን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ በሚል ዓላማ፣ በእምነት አስተምህሮ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የተያዙ ወንጀሎችን በሚመለከቱ ሕጎች ላይ በቅርብ ጊዜ ማድሻሻያ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ክስተቱን ለመግታት የፍትህ እርምጃ ብቻውን በቂ ሊሆን እንደማይችል፣ ነገር ግን ፍትህን መልሶ ለማስፈን፣ ስህተቶችን በመጠገን ጥፋተኛውን ከጥፋቱ ለመመለስ የሚወሰድ እርምጃ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። በመቀጠልም በጋብቻ ትስስር መፍረስ ላይም ተመሳሳይ ቁርጠኝነት እንዲገለጽ በማለት በአፅንኦት ተናግረዋል።

ቤተክርስቲያን ያላትን ሐዋርያዊ ስልጣን በመጠቀም ያለ ምስጢረ ተክሊል የተፈጸመ የጋብቻ ትስስር እንዲፈርስ ማድረጓ በጋብቻ ላይ ቀኖናዊ ውሳኔ መስጠት ብቻ ባይሆንም፣ እስካሁን የተወሰደው እርምጃ ያልተሳካ መሆኑን ገልጸው፣ በካቶሊክ እምነት ውስጥ የአዲሱን ማኅበረሰብ የቤተሰብ ሕይወት ለማሳደግ ዘወትር የሚጥሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።  

እምነት

የጳጳሳዊ ምክር ቤቱ ተወካዮች በምልአተ ጉባኤያቸው ሊወያዩባቸው ከያዟቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል ሦስተኛው እና የመጨረሻው እምነት ሲሆን፣ ጳጳሳዊ ምክር ቤቱ የተጠራው እምነትን ለመከላከል ብቻ ሳይሆን ለማስፋፋትም ጭምር መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለአባላቱ አስረድተዋል። ያለ እምነት በዓለም ላይ ያሉ ምዕመናን ሕልውና ወደ ድርጅትነት ሊወርድ እንደሚችል ተናግረው፣ እምነት በእያንዳንዱ የተጠመቀ ሰው ሕይወት እና ተግባር ውስጥ በጉልህ መታየት ይኖርበታል ብለው፣ እምነት በማያሻማ መንገድ ግልጽ እና ቀጥተኛ ሊሆን ይገባል ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም ያመጣው የእምነት እሳት በሁሉ ሰው ልብ ውስጥ እንዲነድ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እና እርስ በርሳችንም መተባበር ያስፈልጋል ብለዋል።

22 January 2022, 15:08