ፈልግ

መቶኛ ዓመቱን ያከበረው የቅድስት አገር ጋዜጠኞች ቡድን መቶኛ ዓመቱን ያከበረው የቅድስት አገር ጋዜጠኞች ቡድን  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ወንድማማችነት በስፋት እንዲሰበክ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከቅድስት አገር ኢየሩሳሌም የመጡ ጋዜጠኞችን ትናንት ጥር 9/2014 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው መልዕክት አስተላለፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ጋዜጠኞቹ በክርስቲያኖች እና በሁሉም የአብርሃም ልጆች መካከል ያለውን የወንድማማችነት ታሪክ ለዓለም ሁሉ እንዲናገሩ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ወደ ሃምሳ የሚጠጉ የቅድስት አገር ጋዜጠኞችን ወደ ቫቲካን ይዘው የመጡት በኢየሩሳሌም የቅዱስ ፍራንችስኮስ ማኅበር አለቃ የሆኑት ክቡር አባ ፍራንችስኮስ ፓቶን መሆናቸው ታውቋል። ጋዜጠኞቹ ትናንት ጠዋት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር መገናኘታቸው ታውቋል። የቅድስት ሀገር በሚገኙ ፍራንችስካዊ ማኅበር የሚታተም መጽሔት ዘንድሮ 100ኛ አመቱን እያከበረ ሲሆን፣ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደባት ምድር ያለውን ሕይወት በማስመልከት ዜናዎችን እና መረጃዎችን በማካፈል ግንዛቤዎችን ሲያስጨብጥ መቆየቱ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የክርስቲያን ሚዲያ ማዕከል እና የማኅበሩ ድረ-ገጽ ሠራተኞችን ጨምሮ  መላው የብዙኃን መገናኛ ቡድኑ ለቤተክርስቲያኗ ተልዕኮ ላሳዩት ቁርጠኝነት አመስግነዋቸዋል።

ተልዕኳቸው ወይም አገልግሎታቸው፣ ቀዳሚው የመጽሔታቸው አዘጋጅ የነበረው ኩስቶስ ፌርዲናዶ ዲዮታሌቪን ከሚያቀርበው የመግባቢያ ጽሑፍ ጋር የተጣጣመ እና በመጀመሪያ እትሙ ላይ እንደጻፈው፣ ቅድስቲቱ ምድር፣ የእግዚአብሔርን ምድር፣ የክርስትና እምብርት እና የሰው ዘር ቤዛነት የተፈጸመባቸው የተከበሩ መቅደሶች የሚገኙባት ሥፍራ ናት በማለት ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

በሰዎች መካከል ወንድማማችነትን ማሳደግ

የቅድስት ሀገር ታሪክን መናገር ማለት "አምስተኛውን ወንጌል" እንደማካፈል ይቆጠራል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እሱም "የእግዚአብሔር ቃል የተገለጠበት እና እኛን ለማዳን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን የለበሰበት ታሪካዊና መልክአ ምድራዊ አካባቢን ለሌሎች ማሳወቅ ማለት እንደሆነ አስረድተው፣ በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ በዚያ አካባቢ የሚኖሩ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እና ቤተ እምነቶች እንዲሁም የአይሁድ እና የእስልምና እምነቶችን ጨምሮ የሰዎችን ታሪክ መናገር ማለት ነው ብለዋል። አክለውም የጋዜጠኞቹ ዋና ዓላማ አስቸጋሪ እና ውስብስብ በሆነው የመካከለኛው ምሥራቅ ማህበራዊ ሁኔታ ውስጥ ወንድማዊ ማህበረሰብን ለመገንባት መርዳት መሆን አለበት ብለዋል።

“በሚቻለው ሁሉ የወንድማማችነትን ታሪክ እንድትነግሩ አበረታታችኋለሁ” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በአብያተ ክርስቲያናት እና በክርስቲያን ማኅበረሰብ መካከል ያለው ግንኙነት አሁንም የተራራቀ ቢሆንም በቅድስት ሀገር ባሉት አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው ግንኙነት ለአንድነት የተቀራረበ በመሆኑ የአብርሃም ልጆች በሆኑ አይሁዶች፣ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች መካከል ወንድማዊነትን እንዲመሰክሩ አሳስበዋል። ለራሳቸው እና ለልጆቻቸው መልካም ሕይወት ፍለጋ ከትውልድ አገራቸው ለተፈናቀሉት እና ለስተሰደዱት በሙሉ ቤተክርስቲያናዊ ወንድማማችነትን እንዲመሰክሩ አደራ ብለዋል።

ታሪክን በደንብ መናገር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም ከቅድስት አገር ኢየሩሳሌም የመጡ ጋዜጠኞች “ሰዎች ባሉበት እና በሚገኙበት የኑሮ ሁኔታ” የሚያገኟቸው በመሆኑ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ጋዜጠኞቹ እንደ ሶሪያ፣ ሊባኖስ፣ ፍልስጤም እና ጋዛ ባሉ መካከለኛው የምሥራቅ አገራት ያለውን ስቃይ በዜና ለማቅረብ ድፍረት ማሳየታቸውን አስታውሰው፣ መልካም ሥራቸው የጦርነትን ክፋት በንቃት በመቃወም፣ የዕርቅ ታሪኮችን በመናገር፣ ሰብዓዊ ክብርን ለመመለስ የስደተኞችን ተስፋ እና አሳዛኝ ሁኔታዎች አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

የመዳንን መልዕክት ማስተላለፍ

የእግዚአብሔር ቃል የማዳን መልእክቱን በገለጠበት ቦታ የሕይወት ልምዶችን በብቃት ማድረስ አስፈላጊ መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አመልክተው፣ ጋዜጠኞቹ “የድነት ታሪክ እና የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ስለሚገናኙበት ስለ ቅድስት ሀገር የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፣ በተለይም ስለ ቅዱሳት ወንጌላት እንዲናገሩ መጠራታቸውን አስረድተዋል።

በዓለም ዙሪያ የክርስቲያኖችን እምነት ማሳደግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመጨረሻም ጋዜጠኞቹ የብዙ ሰዎችን እምነት ለማበልጸግ፣ ወደ ቅዱሳን ቦታዎች ለመጓዝ ዕድል የሌላቸውንም በሙሉ ልብ ለማገልገል ሁሉንም ዓይነት ማኅበራዊ ሚዲያዎች በመጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል። ይህም አገልግሎት በዓለም ዙሪያ ለሚገኙት አማኞች እጅግ የከበረ መሆኑን ገልጸው በተመሳሳይ መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደባት አገር ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ድጋፍ መሆኑን አስረድተዋል። ለጋዜጠኞቹ ያላቸውን ድጋፍ እና ቅርበት በመግለጽ በጸሎታቸውም የሚያስቧቸው መሆናቸውን በመግለጽ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

18 January 2022, 16:24