ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለአምባሳደሮች መልካም ምኞታቸውን በገለጹበት ወቅት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለአምባሳደሮች መልካም ምኞታቸውን በገለጹበት ወቅት 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ አምባሳደሮች ዋና ግባቸው አለመግባባቶችን መፍታት መሆን እንዳለበት አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኞ ጥር 2/2014 ዓ. ም. በቅድስት መንበር ውስጥ ተመድበው ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዋቸውን በመፈጸም ላይ ለሚገኙ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ የዓለማችንን ልዩ ልዩ ርዕሠ ጉዳዮች የተመለከተ ሰፋ ያለ ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው ለአምባሳደሮቹ ባቀረቡት ንግግር ዛሬ ላይ ዓለማችን የሚገኝበትን ሰብዓዊ እና ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን አስታውሰዋል። በጋራ መኖሪያ ምድራችን በኅብረት በሚኖር መላው ሰብዓዊ ቤተሰብ ላይ የደረሱ ችግሮችን ለማስወገድ በቅድሚያ የዓለማችንን ሁኔታ ተገንዝቦ ፈጣን የጋራ መፍትሄ ማግኘት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው በቅድስት መንበር ዲፕላማሲያዊ ተልዕኮዋቸውን በመፈጸም ላይ የሚገኙ አምባሳደሮች ዋነኛ ግባቸው አለመግባባቶችን መፍታት እና ስምምነትን መፍጠር መሆን እንዳለበት አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከሁሉም በላይ በሰው ልጅ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማስከተል ላይ የሚገኘውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መግታት የሁሉም ሰው ትኩረት እና ጥረት ሊሆን እንደሚገባ ቅዱስነታቸው አሳስበው፣ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በሚደረጉ ጥረቶች ላይ አንዳንድ ርዕዮተ ዓለማዊ ልዩነቶች እንቅፋት እየፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል። ይህም የሰው የማመዛዘን ትስስር ከነባራዊ እውነታዎች እንዲቋረጥ ማድረጉን አስረድተዋል።

ወረርሽኙን መዋጋት

የአገራት መሪዎች እና ዜጎች ችግሩን ለማስወገድ መተባበር እንደሚገባ ጥሪ አቅርበው ለጋራ ጥቅም ሲባል ወረርሽኙን ለመከላከል እና የክትባት መርሃ ግብርን ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዱ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ማሳየት ያስፈልጋል ብለዋል። አክለውም “መላው የዓለም ህዝብ አስፈላጊውን የሕክምና እንክብካቤ እና ክትባቶችን በእኩልነት ማግኘት እንዲችል በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኩል ሁሉን አቀፍ ቁርጠኝነት አስፈላጊ ነው” ብለዋል ። መንግሥታት እና የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነት እንዲሰማቸው ጠይቀው፣ “በየደረጃው የተቀናጀ አካባቢያዊ፣ ብሔራዊ፣ ክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ ምላሽ መስጠት እንዲቻል አዳዲስ የጋራ ሞዴሎችን እና መሣሪያዎችን በማዳበር የአገሮችን አቅም ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ በሁሉም አገራት ዜጎች በበቂ የሕክምና መስጫ መሣሪያዎች በመታገዝ ክትባቶችን እና መድኃኒቶችን የማግኘት ዋስትና እንዲኖራቸው የመተጋገዝ ፖሊሲን እንደ ቁልፍ መርህ እንዲወስዱ አሳስበዋል ። 

የሐዋርያዊ ጉብኝት እና የሊባኖስ መከራ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየዓመቱ እንደሚገለጹት ሁሉ በእርስ በእርስ አመጽ፣ በፖለቲካ ልዩነት፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እና በድህነት የተጎዱ የዓለማችን አካባቢዎች አስታውሰዋል። ከእነዚህ የዓለማችን አካባቢዎች መካከል በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ የሚገኘውን የሊባኖስ ሕዝብ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በአገሪቱ ውስጥ አስፈላጊ ለውጦች እንዲደረጉ አሳስበው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም እርዳታውን እንዲያበረክት፣ ድጋፉ አገሪቱ በተለያዩ ሃይማኖቶች መካከል ሰላምን እንድታሳድግ፣ የአብሮነትና የወንድማማችነት ተምሳሌት እንድትሆን እና በትክክለኛ ማንነቷ እንድትጸና ይረዳታል” ብለዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር ባለፈው የአውሮፓውያኑ 2021 ዓ. ም. በኢራቅ፣ በቡዳፌስት፣ በስሎቫኪያ፣ በቆጵሮስ እና በግሪክ ያከናውኗቸውን ሐዋርያዊ ጉብኝቶች የክርስቲያኖችን አንድነት ለማጠናከር እና በሃይማኖቶች መካከል የጋራ ውይይቶች ለማካሄድ መልካም ዕድል የሰጡ ፍሬያማ ሐዋርያዊ ጉብኝቶች እንደነበሩ ተናግረዋል።

ስደትን በተመለከተ

የግሪክ ደሴት በሆነች ሌስቦስ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከትውልድ አገራቸውና ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ተለይተው እንዲሰደዱ በሚገደዱ ወገኖች ላይ የሚደርሰውን መከራና ስቃይ ለማየት ያስቻለ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸው፣ ስደተኞችን በክብር ተቀብለው ዕርዳታን ለማድረግ የሚጥሩ ስዎች ለጋስነት የታየበት እንደነበርም አስታው፣ "ለእነዚያ በመከራ ውስጥ ለሚገኙ ቤተሰቦች ግድ የለሾች በመሆን፣ ለደህንነታችው ጥበቃን ከማድረግ እና ለሕይወታቸው ከመጨነቅ ይልቅ በየድንበሮች ላይ በሚቆሙት ግድግዳዎች እና አጥሮች መደበቅ አንችልም" ብለዋል።

አንዳንድ አገሮች በርካታ ስደተኞችን ሲያስተናግዱ የሚያጋጥሟቸው ችግሮች እንዳሉ የተገነዘቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ መንግሥታት እና የአውሮፓ ኅብረት አገራት “በስደት እና ጥገኝነት ጥያቄ ዙሪያ ፖሊሲዎችን በመንደፍ ወጥ እና ሁሉን አቀፍ ሥርዓት እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል። ስደተኞችን የመቀበል ኃላፊነት፣ የጥገኝነት ጥያቄዎችን ገምግሞ ተቀባይነት እንዲኖራው ማድረግ እና ከፊታችን ያሉ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን ታሳቢ በማድረግ ትክክለኛ ሞዴሎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ድጋፉ ለደህንነታቸው እና የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ብለው ወደ አውሮፓ ወደቦች ለሚደርሱት ስደተኞች ብቻ ሳይሆን ከሶሪያ፣ ከአፍጋኒስታን እና በሜክሲኮ አድርገው ወደ ሰሜን አሜሪካ ለሚሰደዱት ሊደርስ እንደሚገባ አሳስበው፣ ከስደተኞች መካከል ብዙዎቹ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራቸው ላይ የደረሰውን አሳዛኝ ሁኔታ በመሸሽ ላይ የሚገኙ የሔይቲ ተወላጆች መሆናቸውን ገልጸዋል። የስደት ጉዳይ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቀውስ እና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተዳምሮ ከደረሰብን ቀውስ ብቻችን መዳን እንደማይቻል በግልፅ የታየበት እውነታ መሆኑን ገልጸው፣ የዘመናችን ትላልቅ ፈተናዎች ዓለም አቀፋዊ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

የአጋርነት ጥቅም

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ "የአንድ ቤተሰብ የጋራ ማንነትን" መልሶ ማግኘት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን፣ በአገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ላይ የሚደርስ ቀውስ "የማኅበራዊ እና መንግሥታዊ ስርዓቶች ተዓማኒነት ይቀንሳል" በማለት ተቃውመውታል። ሁሉም አገሮች በጋራ የሚነጋገሩበት ትክክለኛ የድርድር ሂደት ሳይኖር የሚወጡ መግለጫዎች እና ውሳኔዎች እንደሚያሳስባቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገልጸው፣ ይህም በዓለም አቀፍ ኤጀንሲዎች ላይ ቅሬታ የሚፈጥር እና የአገራት የአንድነት ስርዓቱን በማዳከም ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶችን በመፍጠር ውጤታማነትን የሚቀንስ መሆኑን አስረድተዋል።

በታሪክ የተለያዩ ሕዝቦች ያላቸው ልዩነቶችን እና ስሜቶችን የሚሰርዝ ሳይሆን የሚንከባከብ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲፈጠር ቅዱስነታቸው ጠይቀው፣ ከተለያዩ አመለካከቶች ጀምሮ ሁሉንም የሚጠቅም የጋራ መፍትሄዎችን ለማግኘት የሰው ልጅ እንደ አንድ ታላቅ ቤተሰብ መተባበር እንደሚያስፈልግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሳስበዋል። “በተለይ በሕይወት የመኖር መብት፣ ከጽንስ ጀምሮ እስከ ተፈጥሯዊ የነፍስ ፍፃሜው ድረስ ያለውን መብት እና የእምነት ነፃነት መብትን መጥቀስ እፈልጋለሁ” ያሉት ቅዱነታቸው፣ የሰው ልጅ መሠረታዊ እሴቶች በውይይት እና በስምምነት የሚጸድቁ ከሆነ ከመግባባትም በላይ መሆናቸውን እንገነዘባለን ብለዋል። 

የጋራ መኖሪያ ምድራችንን መንከባከብ

የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በእንግሊዝ ግላስጎው ከተማ ከጥቅምት 21 - ኅዳር 3/2014 ዓ. ም. በተካሄደው 26ኛ የተባበሩት መንግሥታት መሪዎች ጉባኤ ላይ የተደረሰውን ስምምነት በመጠቀስ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን አስቸኳይ እንክብካቤ ማድረግ የበለጠ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በጉባኤው ወቅት በርካታ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አስታውሰው “ካጋጠሙት ችግሮች ክብደት አንፃር ደካማ ቢሆኑም” በሚቀጥለው ዓመት ህዳር ወር ላይ በግብፅ ሊካሄድ ከታቀደው 27ኛ የተባበሩት መንግሥታት መሪዎች ጉባኤ መልካም ውሳኔዎች እንደሚደረጉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የአመጾች የሚታዩባቸው የዓለማችን አካባቢዎች

በዓለም ዙሪያ በሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይ መላውን የሰው ልጅ እንደሚያሳስብ በድጋሚ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም አንዳንድ ጊዜ እንደ እውነተኛ የውክልና ጦርነቶች ለሚመስሉ ማለቂያ ለሌላቸው ግጭቶች መፍትሔን እንዲያፈላልግ አሳስበዋል።

ሶርያ ፖለቲካዊ እና የሕገ መንግሥት ማሻሻያዎች ያስፈልጋታል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በሶርያ ላይ የሚጣል የኤኮኖሚ ማዕቀብ በሕዝቡ ዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ችግር እያከተለ መሆኑን ገልጸው፣ በድህነት ውስጥ ለሚገኝ የሶርያ ሕዝብ ብሩህ ተስፋ መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በየመን ውስጥ ለዓመታት የዘለቀው ግጭት ከማኅበራዊ ሚዲያ ትኩረት የራቀ እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግድ የለሽነቱን ያሳየበት፣ በተለይም በሴቶች እና በህጻናት ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳቶችን እያደረሰ የሚገኝ አሳዛኝ ክስተት መሆኑን ገልጸዋል። በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል የሚደረግ የሰላም ሂደቶች መሻሻልን እንዳላሳዩ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ሁለቱ ሕዝቦች በሁለት መንግሥታት ሥር ሆነው፣ ምሕረት እና እርቅን በማድረግ ጎን ለጎን በሰላም ያለ ጥላቻ እና ያለ ቂም በቀል መኖር እንደሚችሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ሌሎች የሥጋት ምንጮች “በሊቢያ ውስጥ ያለው ውጥረት፣ በሳህል አገሮች መካከል የሚታይ ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነት ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን እና በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የእርስ በእርስ ግጭቶች ናቸው” በማለት ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

ትኩረታቸውን በእኩልነት ማጣት እና ኢፍትሃዊነት ላይ ያደረጉት ቅዱስነታቸው፣ ሥር የሰደደ ሙስና እና የሰዎችን ክብር የሚነኩ የተለያዩ የድህነት ዓይነቶች በአሜሪካ አህጉር እያደጉ መምጣታቸው ማኅበራዊ ግጭቶችን እያባባሱ መሆናቸውን ገልጸው፣ በተለይም ድሆች እና ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ክፍሎችን ለችግር መዳረጋቸውን አስረድተዋል። በአውሮፓ ውስጥም ለዩክሬን፣ ለደቡብ ካውካሰስ እና ለባልካን አገሮች ዘላቂ መፍትሄ እንዲገኝላቸው ጠይቀዋል።

አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በመዝለቅ ሚያንማርን ለከፍተኛ ጉዳት የዳረገውን ቀውስ በጥበብ ለመፍታት የጋራ ውይይት እና ወንድማማችነት በጣም አስፈላጊ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተው፣ በአገሪቱ ውስጥ የተቀሰቀሰው ግጭት በአምልኮ ሥፍራዎችም ከፍተኛ ጥፋት እያስከተለ መሆኑን አስታውሰዋል።

የጦር መሣሪያ ትጥቅ የማስፈታት ሂደት

እነዚህን ግጭቶች የሚያባብሱ ብዛት ያላቸው የጦር መሣሪያዎች ምርት መኖሩን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ “የጦር መሣሪያን ለማቅረብ የሚጥሩ ሰዎች ጨዋነት የጎደላቸው ናቸው” ብለው፣ በኒውዮርክ ሊሰበሰብ የነበረው የኑክሌር የጦር መሣሪያ ቅነሳ ስምምነት ጉባኤ፣ ተዋናይ ወገኖች አዲስ ቃል ኪዳን እንዲገቡ የሚያደርግ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸው የጦር መሣሪያ ትጥቅ ማስፈታት ሂደት እንዲኖርም ጠይቀዋል። “ከኒውክሌር ጦር መሥሪያ ነፃ የሆነ ዓለም መገንባት የሚቻል እና አስፈላጊ ነው” በማለት የቅድስት መንበርን አቋም በድጋሚ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የኑክሌር ጦር መሣሪያዎች ለደህንነት ሥጋቶች ምላሽ የማይሰጥ ሥነ ምግባር የጎደለው እና የሰውን ልጅ ህልውና አደጋ ላይ የጣለ መሆኑንም አስረድተዋል።

የትምህርት እና የሥራ ዕድሎች

በመጨረሻም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአውሮፓዊያኑ አዲስ ዓመት መግቢያ ዕለት በተከበረው ዓለም የሰላም ቀን ያስተላለፉትን መልዕክት በማስታወስ፣ የጋራ ውይይቶችን እና የወንድማማችነት ባህልን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ትምህርት ልዩ ቦታ እንዳለው የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ግለሰቦችን ነፃ እና ተጠያቂ ስለሚያደርጋቸው የሰው ልጅ ዋና ተግባር መሆን እንዳለበት አስረድተዋል። በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሚመሩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚፈጸሙ ጾታዊ የጥቃት ወንጀሎችን ከመጥቀስና ከማውገዝ ባለፈ፣ የቱም ማኅበረሰብ የትምህርት ኃላፊነትን ሊተው እንደማይችል እና ብዙ ጊዜ ለትምህርት ማስፋፊያ የሚመደብ የበጀት መጠን ጥቂት እንደሆነ ገልጸው፣ በትምህርት ላይ የሚውል መዋዕለ ንዋይ ለወደፊት ማኅበራዊ ሕይወት እድገት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

በአውሮፓዊያኑ አዲስ ዓመት መግቢያ ዕለት ያስተላለፉትን መልዕክት የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሥራ ሰላምን በመገንባት እና በመጠበቅ ረገድ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፣ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ብዙ ሰዎች ከሥራ ገበታ መወገዳቸው ኪሳራን፣ ብዝበዛን እና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ማስከተሉን ገልጸው፣  ቀውሱ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚወድቁ ሰዎችን ቁጥር ከፍ እንዲል ማድረጉንም ገልጸዋል። በመሆኑም በብሔራዊ፣ ክልላዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም ተዋናዮች መካከል የላቀ ትብብር ሊኖር እንደሚገባ ቅዱስነታቸው አሳስበው፣ ቀጣዮቹ ዓመታት የመልካም ሕይወት ጊዜ እንደሚሆኑ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በቅድስት መንበር እውቅና የተሰጠው የዲፕሎማሲ ቡድን

በአሁኑ ጊዜ ከቅድስት መንበር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው 183 አገሮች መኖራቸው ሲነገር፣ ይህም የአውሮፓ ኅብረትን እና የማልታ ሉዓላዊ ሠራዊት ማኅበርን የሚጨምር መሆኑ ታውቋል። የአውሮፓ ኅብረት እና የማልታ ሉዓላዊ ሠራዊት ማኅበርን ጨምሮ 87 የኤምባሲ ቻንስለሮች በሮም ከተማ እንደሚገኙ ሲታወቅ፣ ከቅድስት መንበር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው የአረብ ሀገራት ሊግ፣ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ኮሚሽን እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሺን ቢሮዎችም በሮም ከተማ ውስጥ እንደሚገኙ ታውቋል።

15 January 2022, 16:09