ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ሁሉንም ነገር በልባችን ውስጥ ይዘን እንድናሰላስል ማርያም ትርዳን አሉ!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የዓለማችን የማኅበረሰብ ክፍሎች ዘንድ 2021 ዓ.ም ተጠናቆ የ2022 ዓ.ም ዓዲስ አመት በታኅሳስ 23/2014 ዓ.ም መጀመሩ ይታወሳል። በተመሳሳይ መልኩ በዚሁ በጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር የ2022 ዓ.ም በእየ አመቱ የአዲስ አመት መጀመሪያ ላይ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ከአዲስ አመት በዓል ባሻገር ስለ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ከተደነገጉ አራት የእምነት እውነቶች መካከል በቀዳሚነት የሚገኘውና እ.አ.አ በ250 ዓ.ም አከባቢ ላይ የተደነገገው “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት ናት” የሚለውን የሚዘክረው የእምነት እውነት በዓል በታኅሳስ 23/2014 ዓ.ም በታላቅ መንፈሳዊነት ተክብሮ ማለፉ ይታወሳል።

ይህ በዓል በታኅሳስ 23/2014 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መሪነት በተካሄደውና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት ተከብሮ ማለፉን ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በወቅቱ ከሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 2፡15-21 ላይ ተወስዶ በተነበበውና መልአኩ ለእረኞች በተገለጸበት ወቅት ወደ ቤተልሄም እንዲሄዱ እና ሕጻኑን ኢየሱስን በከብቶች በረት ወስጥ በሚገኘው ግርግም ውስጥ ተኝቶ እንደ ሚያገኙት ነገራቸው “መላእክቱ ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ ከወጡ በኋላ እረኞቹ፣ “ጌታ የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንድናይ ወደ ቤተ ልሔም እንሂድ” ተባባሉ። እነርሱም ፈጥነው ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን፣ ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። ካዩም በኋላ፣ ስለ ሕፃኑ የተነገራቸውን ገልጠው አወሩ። ይህንንም የሰሙ ሁሉ እረኞቹ በነገሯቸው ነገር ተደነቁ፤ ማርያም ግን ይህንን ሁሉ በልቧ ይዛ ታሰላስል ነበር። እረኞቹም ሁሉም ነገር እንደ ተነገራቸው ሆኖ በማግኘታቸው፣ ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ። ስምንት ቀን ሆኖት የመገረዣ ጊዜው ሲደርስ፣ ከመፀነሱ በፊት መልአኩ ባወጣለት ስም ኢየሱስ ተባለ” በሚለው የእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው አስተንትኖ ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን የእግዚአብሔር እናት የሆነችው ማርያም ሁሉንም ነገር በልባችን ውስጥ ይዘን እንድናሰላስል ትርዳን ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ታዳሚዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በታኅሳስ 23/2014 ዓ.ም የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የዓለማችን ማኅበረሰቦች ዘንድ ከተከበረው የ2022 ዓ.ም አዲስ አመት ጋር ተያይዞ የተከበረውን “ማርያም የእግዚአብሔር እናት” መሆኑዋን በሚዘክረው አመታዊ በዓል ላይ ያሰሙትን ስብከት ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው አሰናድተናል እንድትከታተሉ ከወዲሁ እንጋብዛለን።

እረኞቹ “ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙት” (ሉቃስ 2፡16)። ግርግም ለእረኞች አስደሳች ምልክት ነው፡ ከመልአኩ የሰሙትን መልእክት ያረጋግጣል (ሉቃስ 2፡12 ይመልከቱ)፣ አዳኛችን የሚያገኙበት ቦታ ነው። ደግሞም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጎን ስለመሆኑ ማረጋገጫ ነው፡ በግርግም ውስጥ መወለዱ በእነርሱ ዘንድ በደንብ የሚያውቁት ነገር ነው፣ ስለዚህም ይህ ለነርሱ ቅርብ እና ጠንቅቀው የሚያውቁት ጉዳይ መሆኑን ያሳያል። ነገር ግን ግርግም ለእኛም አስደሳች ምልክት ነው፡ ኢየሱስ ከትንሽና ከድሆች በመወለድ ልባችንን ነካው ከፍርሃት ይልቅ ፍቅር ሰጠን። ግርግም እርሱ ለወደፊቱ ለእኛ ምግብ ሆኖ እንደ ሚመጣ አስቀድሞ ያሳያል። ድህነቱም ለሁሉም ሰው በተለይም በዳርቻ ላይ ላሉት፣ ለተጣሉት፣ በዓለም ላይ እንደ ሰው ለማይቆጠሩ ሁሉ መልካም ዜና ነው። እግዚአብሔር ወደዚያ ይመጣል፣ እርሱ በጣም አይቸኩልም፣ በግርግም ተኝቷል። በግርግም ተኝቶ የማየቱ ውበት ይህ ነው።

ለወላዲተ አምላክ ማርያም ግን እንዲህ አልነበረም። “በግርግም ውስጥ የተፈጠረውን ያልተጠበቀ ነገር” መታገስ ነበረባት። እርስዋም ከእረኞቹ በፊት በዳዊት ዙፋን እንደ ሚቀመጥ የተናገራት የመልአኩን ታላቅ መልእክት ተቀብላለች፣ መልእክቱ እንዲህ ይል ነበር “እነሆ፤ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል” (ሉቃስ 1: 31-32)። እናም አሁን በእንስሳት መመገቢያ ውስጥ ልጇን ማስቀመጥ ነበረባት። የንጉሱን ዙፋን እና የድሆችን በረት እንዴት ማስታረቅ ይቻላል? የልዑል ክብርን እና በከብቶች በረት ውስጥ ያለውን መከራ እንዴት ማስታረቅ ይቻላል? የአምላክ እናት እንዳልተመቻት አድርገን እናስብ፣ እናት ልጇ ሲሰቃይ ከማየት የበለጠ ምን ይከብዳታል? የተስፋ መቁረጥ ስሜት አለ። ማርያም በዚህ ነገሩ ሁሉ ፊት ብሶቷን ብትገልጽ እና ብታማርር ልንወቅሳት አንችልም። ነገር ግን እርሷ ልቦናዋን አላጣችም። በነገሩ አልተበሳጨችም፣ ነገር ግን ዝም ማለትን መረጠች። ቅሬታዋን በተመለከተ የተለየ መንገድ ትመርጣለች፣  ቅዱስ ወንጌል እንደ ሚለው "ማርያም በበኩሏ ይህን ሁሉ ነገር በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር" (ሉቃስ 2፡19) ይለናል።

ከእረኞቹና ከሕዝቡ የተለየ አሠራር ነው። እነርሱ ያዩትን በሙሉ ተናግረዋል፣ በእኩለ ሌሊት የተገለጠው መልአክ ስለ ሕፃኑ የተናገረውን ቃል በሙሉ ለሌላ ሰዎች ተናግረዋል፣ ሕዝቡም እነዚህን ነገሮች በሰሙ ጊዜ ተገረሙ (ሉቃስ 2፡18 ተመልከት) ይለናል ቅዱስ ወንጌል፣ ቃላትና መደነቅ። በሌላ በኩል ማርያም አሳቢ ትመስላለች። በልቧ ውስጥ ሁሉንም ነገር ይዛ ታሰላስል ነበር። እነዚ በውስጣችንም የምናገኛቸው ሁለት የተለያዩ አመለካከቶች ናቸው። የእረኞች ታሪክ እና መገረም በእምነት ጅምር የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል። እዚያ ሁሉም ነገር ቀላል እና ቀጥተኛ ነው፣ ወደ ሕይወት በሚገቡት የእግዚአብሔር አዲስነት ደስተኞች ነን፣ በሁሉም ረገድ አስደናቂ ድባብን ያመጣል። የማርያም የማሰላሰል ዝንባሌ እምነቷ መጎልመሱን የሚያሳይ መግለጫ ነው። ገና አሁን የተወለደ እምነት ሳይሆን ነገር ግን እየጎለመሰ የሚሄድ እምነት ነው። ምክንያቱም መንፈሳዊ ፍሬያማነት በፈተና ውስጥ ያልፋል። ከናዝሬት ጸጥታ እና በመልአኩ ከተቀበለችው የድል ተስፋዎች - ጅማሬዋ - ማርያም አሁን በቤተልሔም ጨለማ በረት ውስጥ ትገኛለች። እግዚአብሔር ግን ለዓለም የሚሰጥበት ቦታ ነው። እናም ሌሎች በግርግም ውስጥ በተከሰተው ነውር በሚመስለው ነገር ሲጋፈጡ፣ ሌሎች ደግሞ በተስፋ መቁረጥ ሊወሰዱ ነበር፣ እሷግን ይህንን አላደረገችም፣ በማሰላሰል ትጠብቃለች።

ይህን አመለካከት ከእግዚአብሔር እናት እንማራለን፣ በማሰላሰል መጠበቅ። ምክንያቱም እኛ ደግሞ አንዳንድ “በግርግም ውስጥ የተፈጠሩትን ነውር የሚመስሉ ነገሮችን” ልንሸከም ይገባናል። ሁሉም ነገር በጥሩ ሁኔታ እንደሚሄድ እና ከዚያም ጸጥ ካለው ሰማይ ውስጥ እንደ ሚመጣው መብረቅ ያልተጠበቀ ችግር እንደሚመጣ ተስፋ ማድረግ ይኖርብናል። እናም በሚጠበቀው እና በእውነታው መካከል የሚያሰቃይ ግጭት ይፈጠራል። የወንጌል ደስታ አንድ ሰው ሲራመድ በሚያገኘው አስቸጋሪ ሁኔታ ሲፈተሽ በእምነትም ይከሰታል። ዛሬ ግን የአምላክ እናት ከዚህ ተጽእኖ እንድንጠቀም ታስተምረናለች ። ይህ ጉዳይ አስፈላጊ መሆኑን ታሳየናለች፣ ወደ ግብ ለመድረስ ጠባብ መንገድ፣ መስቀል ከሌለ አንድ ሰው እንደገና ሊነሳ አይችልም። ለበለጠ የበሰለ እምነት ሕይወትን የሚሰጥ እንደ የሚያሠቃይ ልደት ነው።

ነገር ግን ይህንን እርምጃ እንዴት መውሰድ እንደሚቻል፣ በምናባዊ እና በእውነቱ መካከል ያለውን ግጭት እንዴት ማሸነፍ ይቻላል? ልክ እንደ ማርያም በማድረግ መጠበቅ እና ማሰላሰል ይኖርብናል። በመጀመሪያ ማርያም በውስጧ ታሰላስል ነበረ እንጂ ተስፋ አልቆረጠችም። እየሆነ ወይም እየተከሰተ የሚገኘውን ነገር ለመግፋት አልፈለገችም። ያየችሁን እና የሰማችሁን ሁሉ በልቧ ውስጥ አስቀምጣ ታሰላስል ነበር። መልአኩ እንደነገራት እና እረኞቹ የነገሯትን የሚያምሩ ነገሮች ሁሉ ላይ ታሰላስል ነበር።ነገር ግን ለመቀበል የሚከብዱ ነገሮች ነበሩ፡- ከጋብቻ በፊት የመፀነስ አደጋ፣ አሁን የወለደችበት በረት ውስጥ ያለው ሁኔታ ሁሉ ያሳስቧት ነበር። በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ሆና ማርያም ታከናውን የነበረችው ነገር ቢኖር ሁሉንም ነገር በልቧ ውስጥ ይዛ ማሰላሰል ነበር። ሕይወቷን ሜካፕ ለመቀባት እና አስመስላ ለመኖር ሳይሆን ሁሉንም ነገር ተቀብላ በውስጧ ይዛ ታሰላስል ነበር።

እናም ከዚያ በኋላ ሁለተኛው አመለካከት አለ፣ በማሰላሰል መጠበቅ። በወንጌል የተጠቀሰው ግስ የነገሮችን መጠላለፍ ያነሳሳል፡- ማርያም የተለያዩ ልምዶችን ታወዳድራለች፣ የተሸሸጉትን የተደበቀ ክሮች ታገኛለች። በልቧ ውስጥ፣ በጸሎቱ ውስጥ ይህን ያልተለመደ ታላቅ ነገር በስውር ታካሂድ ነበር፣ መልካም እና መልካም ያልሆኑ ነገሮችን ታገናኛለች፣ አንድ ታደርጋቸዋለች እንጂ አታለያያቸውም። ስለዚህም የእግዚአብሔርን አተያይ ሙሉ ትርጉሙን ትረዳለች። በእናትነት ልቧ የልዑል ክብር በትሕትና መገድ እንደ ሚረጋገጥ ተረድታለች። እግዚአብሔር በግርግም ማረፉ ያለበትን የድኅነት እቅድ ይቀበላል። አቅመ ደካማ እና በተመሳሳይ መልኩም የሚያንቀጠቀጥ መለኮታዊ ልጅን አይታለች፣ እናም አስደናቂውን የታላቅነት እና የትንሽነት መለኮታዊ መጠላለፍን ተቀበለች።

በልብ ውስጥ ነገሮችን ይዞ በመጠበቅ እና በማሰላሰል ውጥረትን የሚያሸንፈው ይህ ሁሉን አቀፍ እይታ የእናቶች እይታ ነው። ብዙ እናቶች የልጆቻቸውን ሁኔታ የሚቀበሉበት እይታ ነው። ተጨባጭ እይታ ነው፣ ​​ተስፋ የማይቆርጥ፣ በችግሮች ጊዜ ሽባ የማይሆን፣ ነገር ግን በሰፊ አድማስ ውስጥ የሚያስቀምጡት ልዩ እይታ ነው። የታመመ ወይም የተቸገረ ልጅጃቸውን የሚንከባከቡ እናቶች ፊት ወደ አእምሮዬ ይመጣል። ሲያለቅሱ የተስፋ ምክንያቶችን እንዴት እንደሚያሳድጉ የሚያውቁ ዓይኖቻቸው ውስጥ ምን ያህል ፍቅር አለ! የእነርሱ የንቃተ-ህሊና እይታ ነው፣ ​​ያለመሳሳት ሳይሆን፣ ነገር ግን ከህመም እና ከችግሮች ባሻገር ሰፋ ያለ እይታን፣ እንክብካቤን፣ ፍቅርን ተስፋን ያድሳል። እናቶች የሚያደርጉት ይህ ነው፡ እንቅፋቶችን እና ግጭቶችን እንዴት ማሸነፍ እንደሚችሉ ያውቃሉ፣ ሰላምን እንዴት ማስፈን እንደሚችሉ ያውቃሉ። ስለዚህም መከራን ወደ አዲስ እድል መለወጥ እና ዳግም መወለድ እና ማደግ የሚችል እድሎች ለመለወጥ ችለዋል። እነሱ ያደርጉታል፣ ምክንያቱም እንዴት ነገሮችን በልባቸው ይዘው ማቆየት እንደሚችሉ ስለሚያውቁ፣ የህይወት ክሮች አንድ ላይ እንዴት እንደሚቀመጡ ያውቃሉ። በጣም ብዙ የሆኑትን የክፍፍል ክሮች በማነፃፀር የኅብረት ክር ለመሸመን የሚችሉ ሰዎች ያስፈልጋሉ።

አዲሱ ዓመት በእግዚአብሔር እናት ምልክት ይጀምራል። የእናቶች እይታ እንደገና ለመወለድ እና ለማደግ መንገድ ነው። እናቶች ሴቶች ዓለምን መበዝበዝ ሳይሆን ሕይወትን ይመለከታሉ፣ በልብ በመመልከት፣ ህልም እና ተጨባጭነት በአንድነት ለመጠበቅ፣ ማክሮባልባዊ የሆኑ ሐሳቦቻችንን ተግባራዊነታቸውን በመለካት እና ረቂቅነትን በማስወገድ ልከናወን እንደ ሚችል ያስረዱናል። እናቶች ህይወት ሲሰጡ ሴቶች ደግሞ አለምን ሲጠብቁ ሁላችንም እናቶችን ለማስተዋወቅ እና ሴቶችን ለመጠበቅ መሥራት ይኖርብናል። በሴቶች ላይ ምን ያህል ጥቃት አለ! ይበቃል! ሴትን መጉዳት ከሰው ልጅ ስጋ ወስዶ ሰው የሆነውን እግዚአብሔርን ማስቆጣት ነው።

በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ላይ ራሳችንን በዚህች ሴት ጥበቃ ሥር እናድርግ፣ እናታችን የሆነች የእግዚአብሔር እናት እንድትጠብቀን እንማጸናት ። ሁሉንም ነገር እንድንጠብቅ እና እንድናሰላስል እርሷ በአማላጅነቷ ትርዳን፣ ፈተናዎችን ሳንፈራ፣ ጌታ ታማኝ እንደሆነ እና መስቀሎችን ወደ ትንሳኤ እንዴት እንደሚለውጥ በሚያውቅ በደስታ እርግጠኝነት ውስጥ እንድንጓዝ እርሷ ትርዳን። ዛሬም የእግዚአብሔር ሰዎች በኤፌሶን እንዳደረጉት ወላዲተ አምላክ የሚለውን ማዕረግዋን ሦስት ጊዜ እየደጋገምን እንጥራት።

01 January 2022, 14:39