ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ባደረጉበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ባደረጉበት ወቅት   (Vatican Media)

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ቅዱስ ዮሴፍ የእግዚአብሔርን ድምጽ ለይቶ የሚያውቅ ሕልም አላሚ ሰው ነበር አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ለሚገኙ ምዕመናን በየሣምንቱ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስትምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በጥር 18/2014 ዓ.ም ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከዚህ ቀደም በቅዱስ ዮሴፍ ሕይወት ዙሪያ ላይ ጀምረውት ከነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስ ዮሴፍ የእግዚአብሔርን ድምጽ ለይቶ የሚያውቅ ሕልም አላሚ ሰው ነበር ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስትምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ ቅዱስ ዮሴፍ ሕልም የነበረው ሰው እንደ ነበረ በሚያመልክተው ምስል ላይ ላተኩር እወዳለሁ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ እንደ ጥንት ሕዝቦች ባሕሎች፣ ሕልሞች እግዚአብሔር ራሱን የገለጠበት ዘዴ ተደርጎ ይወሰድ ነበር። ሕልሙ የእያንዳንዳችንን መንፈሳዊ ሕይወት ያመለክታል፣ እያንዳንዳችን ለማዳበር እና ለመጠበቅ የተጠራንበት ውስጣዊ ቦታ፣ እግዚአብሔር እራሱን የሚገለጥበት እና ብዙ ጊዜ የሚናገረን መንገድ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ነገር ግን በተጨማሪም በእያንዳንዳችን ውስጥ የእግዚአብሔር ድምፅ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብዙ ድምፆች አሉ ማለት አለብን። ለምሳሌ የፍርሃታችን ድምጽ፣ ከዚህ ቀደም የነበሩን ልምዶች፣ ተስፋዎች፤ እና እኛን ለማታለል እና ለማደናገር የሚፈልግ የክፉው ነገሮች ድምጾችም አሉ። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ድምጽ በሌሎች ድምፆች መካከል መለየት መቻል አስፈላጊ ነው። ዮሴፍ አስፈላጊውን ዝምታ እንዴት ማዳበር እንዳለበት እና ከሁሉም በላይ ደግሞ ጌታ በውስጡ በሚናገረው ቃል ፊት ትክክለኛ ውሳኔዎችን እንዴት ማድረግ እንዳለበት እንደሚያውቅ አሳይቷል። ዛሬ ራሳችንን ከእግዚአብሔር መገለጥ በፊት እንዴት ማድረግ እንዳለብን ለመረዳት እርሱን ዋና ገፀ ባህሪ ያላቸውን በወንጌል ያሉትን አራቱን ሕልሞች ብንወስድ መልካም ነው።

በመጀመሪያው ህልም (ማቴ. 1፡18-25) መልአኩ ዮሴፍ የማርያምን መፀነስ ሲያውቅ ለደረሰበት ድራማ መፍትሄ እንዲያገኝ ረድቶታል እንዲህም ብሎታል “እጮኛህን ማርያምን ወደ ቤትህ ለመውሰድ አትፍራ፤ የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ነውና። ወንድ ልጅ ትወልዳለች፤ ስሙንም ኢየሱስ ብለህ ትጠራዋለህ፤ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና” (ማቴ 1፡20-21) ። የሰጠው ምላሽ አፋጣኝ ነበር “ከእንቅልፍም በነቃ ጊዜ መልአኩ እንዳዘዘው አደረገ” (ማቴ 1፡24) በማለት ይናገራል። ብዙ ጊዜ ህይወት በማንረዳው እና መፍትሄ የማያገኙ በሚመስሉ ሁኔታዎች ውስጥ ይከተናል። በእነዚያ ጊዜያት መጸለይ ማለት ትክክለኛውን ነገር ጌታ እንዲያሳየን መፍቀድ ማለት ነው። እንዲያውም ብዙውን ጊዜ የመውጫ መንገድን የሚሰጠን ጸሎት ነው። ውድ ወንድሞች እና እህቶች ችግሩን ለመቋቋም የሚያስፈልገንን እርዳታ ሳይሰጠን ጌታ አንድ ጊዜ ችግር እንዲፈጠር አይፈቅድም።

የዮሴፍ ሁለተኛ ግልጽ ሕልም የተከሰተው የሕፃኑ የኢየሱስ ሕይወት አደጋ ላይ በወደቀበት ጊዜ መጣ። “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልጋልና ተነሣና ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ” የሚለው መልእክት ግልጽ ነው (ማቴ 2፡14) ። ዮሴፍ ያለምንም ማመንታት ታዘዘ፡- “በሌሊትም ተነሣ ሕፃኑንና እናቱንም ይዞ ወደ ግብፅ ሸሸ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ” (ማቴ. 2፡ 15-16)። በህይወት ውስጥ ህልውናችንን ወይም የምንወዳቸውን ሰዎች ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ አደጋዎች ያጋጥሙናል። በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ፣ መጸለይ ማለት እንደ ዮሴፍ ዓይነት ድፍረት የሚሰጠንን ድምፅ ማዳመጥ፣ ሳንሸነፍ ችግሮችን መጋፈጥ ማለት ነው።

በግብፅ ዮሴፍ ወደ ቤት መመለስ የሚችልበትን ምልክት ከእግዚአብሔር ዘንድ ጠበቀ፣ እናም ይህ የሦስተኛው ሕልም ይዘት ነው። መልአኩም ሕፃኑን ሊገድሉት የፈለጉት እንደሞቱ ገለጸለት እና ከማርያምና ​​ከኢየሱስ ጋር ወጥቶ ወደ ትውልድ አገሩ እንዲመለስ አዘዘው (ማቴ. 2፡19-20) ። ዮሴፍ “ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል ምድር ገባ” (ማቴ 2፡ 21) ። በዳግም ጉዞው ግን “በአባቱ በሄሮድስ ፈንታ አርኬላዎስ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ ወደዚያ መሄድን ፈራ” (ማቴ 2፡ 22) ።

እነሆ አራተኛው መገለጥ፡- “ይህንንም በሕልም በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ አገር ፈቀቅ ብሎ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ ሄደ” (ማቴ 2፡22-23) ። ፍርሃት የህይወት አካል ነው እና ጸሎታችንንም ይፈልጋል። እግዚአብሔር በፍጹም ፍርሃት እንደማይኖረን ቃል አልገባልንም፣ ነገር ግን በእሱ እርዳታ፣ ለውሳኔዎቻችን መመዘኛ አይሆንም። ዮሴፍ ፍርሃት አጋጥሞት ነበር፣ ነገር ግን እግዚአብሔር በዚህ ውስጥ መራው። የጸሎት ኃይል ብርሃንን ወደ ጨለማ ሁኔታዎች ያመጣል።

በሕይወት ክብደት የተጨቆኑ እና ተስፋ ለቆረጡትም ጭምር መጸለይ የማይችሉትን ብዙ ሰዎችን በዚህ ሰዓት እያሰብኩ ነው። ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር፣ ብርሃንን፣ ብርታትን እና እርዳታን ለማግኘት ራሳቸውን እንዲከፍቱ ቅዱስ ዮሴፍ ይርዳቸው።

ጸሎት ግን ረቂቅ ወይም ንጹሕ የሆነ የውስጥ ምልክት ፈጽሞ አይደለም። ሁልጊዜ ከበጎ አድራጎት ጋር በማይነጣጠል ሁኔታ የተቆራኘ ነው። የጌታን መልእክት ለመረዳት የምንችለው ጸሎትን ለባልንጀራችን ካለን ፍቅር ጋር ስናዋህድ ብቻ ነው። ዮሴፍ ጸለየ እና ፍቅርም ነበረው፣ እናም በዚህ ምክንያት ሁል ጊዜ የህይወት ፈተናዎችን ለመጋፈጥ የሚያስፈልገውን ነገር ይቀበላል። ራሳችንን ለእርሱና ለአማላጅነቱ አደራ እንስጥ።

እንጸልይ 

ሕልምን የምታልም ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ!

መንፈሳዊ ሕይወትን በሚገባ መኖር እንችል ዘንድ አስተምረን።

እግዚአብሔር ራሱን የሚገልጥበት እና የሚያድነን በውስጣችን በሚገኘው ቦታ ነው።

መጸለይ ከንቱ ነው የሚለውን አስተሳሰብ ከእኛ አስወግድ፣

እያንዳንዳችን ጌታ ከሚያሳየን ነገር ጋር እንድንመሳሰል እርዳን።

አስተሳሰባችን በመንፈስ ብርሃን ይብራ።

በእርሱ ብርታት ልባችን ይበረታል። ፍርሃታችንም በምሕረቱ አዳነ።

አሜን።

26 January 2022, 11:13