ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ቅዱስ ዮሴፍ የማደጎ አባትነት ሙላትን አሳይቶን አልፏል ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ  እለት በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በታኅሳስ 27/2014 ዓ.ም ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከዚህ ቀደም በቅዱስ ዮሴፍ ሕይወት ዙሪያ ጀምረውት ከነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን “ቅዱስ ዮሴፍ የማደጎ ልጅ አባትነት ሙላትን አሳይቶን አልፏል ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት ይዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ዛሬ ቅዱስ ዮሴፍን እንደ ኢየሱስ አባት አድረገን በማሰብ በዚህ ጭብጥ ዙሪያ ላይ እናሰላስላለን። ወንጌላውያን ማቴዎስ እና ሉቃስ እርሱን እንደ ወላጅ አባቱ ሳይሆን እንደ ኢየሱስ ተነከባካቢ አድርገው ነው ያቀረቡት። ማቴዎስ ይህንን ይገልፃል "አባት" የሚለውን ቀመር በማስወገድ የኢየሱስ ቅድመ አያቶች ሁሉ በመዘርዘር በዘር ሐረግ ውስጥ ጥቅም ላይ ያውለዋል። ይልቁንም እርሱን “የማርያም ባል፣ ከእርስዋም ኢየሱስ የተወለደ፣ እርሱም ክርስቶስ የተባለው” በማለት ገልጾታል (ማቴ.1፡16)። በሌላ በኩል ሉቃስ ለሕዝቡ ኢየሱስ “የዮሴፍ ልጅ ይመስላቸው ነበር” በማለት ተንግሯል (ሉቃስ 3፡23)።

የዮሴፍን ተተኪ ወይም ህጋዊ አባትነት ለመረዳት በጥንት ጊዜ በምስራቅ አገራት ውስጥ የጉዲፈቻ ተቋም ከዛሬ የበለጠ የተለመደ እንደነበረ ማስታወስ አስፈላጊ ነው። በዘዳግም መጽሐፍ ውስጥ እንደተገለጸው በእስራኤል ሰለሚገኙ ስለ “ሌዋውያን” የተለመደ ጉዳይ ያሳስባል፡- “ወንድማማቾች በአንድነት ቢኖሩና ከእነርሱ አንዱ ወንድ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፣ የሟቹ ሚስት ከቤተ ሰቡ ውጭ ባል ማግባት የለባትም። የባሏ ወንድም ይውሰዳትና ያግባት፤ የዋርሳነት ግዴታውንም ይፈጽምላት። በመጀመሪያ የምትወልደውም ልጅ ስሙ ከእስራኤል ፈጽሞ እንዳይጠፋ በሟች ወንድሙ ስም ይጠራ” (ዘዳግም 25፡5-6) ይላል። በሌላ አነጋገር የዚህ ልጅ ወላጅ የባል ወንድም ነው ማለት ነው፣ ነገር ግን ህጋዊው አባት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ሟች ሆኖ ይቀራል፣ ይህም አዲስ ለተወለደ ልጅ ሁሉንም በዘር የሚገኙ መብቶችን ሁሉ ይሰጣል። የዚህ ህግ አላማ ሁለት ነበር፡ የሟቹን የትውልድ ሐረግ ወይም ዘር እና ንብረቱን መጠበቅ ነው።

ዮሴፍ የኢየሱስ አባት እንደመሆኑ መጠን ሕጋዊ እውቅና በመስጠት በልጁ ላይ ስም የመጫን መብቱን  ተጠቅሟል።

በጥንት ዘመን ስም የአንድን ሰው ማንነት አጠቃላይ ይዘት የሚገልጽ ነበር። ስም መቀየር ራስን መለወጥ ማለት ነው፣ ልክ እንደ አብራም ስሙንም እግዚአብሔር ወደ “አብርሃም” እንደ ለወጠው፣ ትርጉሙም “የብዙ ሕዝቦች አባት” ማለት ነው፣ “የ” ይላል የዘፍጥረት መጽሐፍ፣ እርሱ “የብዙዎች አባት” ይሆናል ይላል። ይህ ሁኔት በተመሳሳይ መልኩ በያዕቆብ ላይ ተከስቷል፣ እሱም “እስራኤል” የተባለ ሲሆን  ፍችውም “ከእግዚአብሔር ጋር የሚታገል” ማለት ነው፣ ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ጋር በመታገል በረከቱን እንዲሰጠው አስገድዶ ነበርና (ዘፍ. 32፡29፤ 35፡10)።

ነገር ግን ከሁሉም በላይ፣ አንድን ሰው ወይም አንድ ነገር መሰየም ማለት አዳም ለእንስሳት ሁሉ ስም ሲሰጥ እንዳደረገው በስሙ ላይ ያለውን ሥልጣን ማረጋገጥ ማለት ነው (ዘፍ. 2፡19-20)።

ዮሴፍ ይህንን አስቀድሞ ያውቃል ለማርያም ልጅ ስም አስቀድሞ በእግዚአብሔር መዘጋጀቱን የሚያውቅ ሲሆን "ኢየሱስ" "ጌታ ያድናል" ማለት ነው የሚል መጠሪያ በመልአኩ እንደተገለጸው “ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ሁሉ ያድናቸዋል” (ማቴ 1፡21)። ይህ የዮሴፍ የተለየ ገጽታ አሁን በአባትነት እና በእናትነት ላይ እንድናሰላስል ያስችለናል።

አባት ወይም እናት ለመሆን ልጅን ወደ ዓለም በማምጣት መውለድ ብቻ በራሱ በቂ አይደለም። "አባቶች አባት ሆነው የተወለዱ ሳይሆን ነገር ግን ከተወለዱ በኋላ የአባትነት መብት ያገኙ ናቸው። ሰው አባት የሚሆነው ልጅን ወደ አለም በማምጣት ብቻ ሳይሆን ያንን ልጅ የመንከባከብ ሀላፊነቱን በመወጣት ነው። አንድ ሰው ለሌላው ሕይወት ኃላፊነት ሲወስድ በሆነ መንገድ ለዚያ ሰው አባት ይሆናል” (በላቲን ቋንቋ Patris corde ፓትሪስ ኮርዴ ‘የአባት ልብ’ ከሚለው ሐዋርያዊ መልእክት የተወሰደ)። በጉዲፈቻ መንገድ ሕይወትን ለመቀበል በመፍቀድ ራሳቸውን ክፍት የሚያደርጉ ሰዎችን ሁሉ በተለየ መንገድ አስባለሁ። ዮሴፍ ይህ ዓይነቱ ትስስር ሁለተኛ ደረጃ የሚሰጠው ነገር እንዳልሆነ ያሳየናል፤ በኋላ የታሰበ አይደለም። የዚህ ዓይነቱ ምርጫ ከፍቅር ዓይነቶች መካከል አንዱ ነው፣ እናም የአባትነት እና የእናትነት መገለጫ ነው። በዓለም ላይ ስንት ልጆች አንድ ሰው እንዲንከባከባቸው እየጠበቁ ናቸው! እናም ስንት ባለትዳሮች አባት እና እናት ለመሆን ይፈልጋሉ፣ ነገር ግን በስነሕይወታዊ (በባዮሎጂያዊ) በሆኑ ምክንያቶች ይህን ማድረግ አይችሉም፣ ወይም ምንም እንኳን አስቀድመው ልጆች ቢወልዱም የቤተሰቦቻቸውን ፍቅር ለሌላቸው ለማካፈል ይፈልጋሉ። የጉዲፈቻ መንገድን ለመምረጥ ልጆችን የመቀበል "አደጋ" ለመጋፈጥ መፍራት የለብንም። በዚህ ረገድ ተቋማቱ በቁም ነገር በመከታተል ነገር ግን አስፈላጊውን አሰራር በማቃለል በዚህ ረገድ ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁ እንደሚሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ፣ ብዙ ቤተሰብ የሚፈልጉ ልጆች እና የብዙ ባለትዳሮች ህልም እውን ሊሆን የሚችለው በዚሁ መንገድ ነው።

ማንም ሰው ከአባታዊ ፍቅር ትስስር እንደተነፈገ እንዳይሰማው እጸልያለሁ። ቅዱስ ዮሴፍ ጥበቃውን ያድርግላቸው ለወላጅ አልባ ሕፃናትም ረድኤትን ይስጣቸው። ልጅ መውለድ ለሚፈልጉ ጥንዶችም እርሱ አማላጅ ይሁንላቸው።

ስለዚህ እንጸልይ፡-

ኢየሱስን በአባትነት ፍቅር የወደድከው ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ፣

አባት እና እናት እንዲኖራቸው የሚመኙ፣ ነገር ግን ቤተሰብ ለሌላቸው ብዙ ልጆች ቅርብ ሁን።

ልጅ መውለድ የማይችሉ ጥንዶችን ደግፍ፤

በዚህ ስቃይ ውስጥ ሆነው የበለጠ እቅድ ማውጣት ይችሉ ዘንድ እርዳቸው።

ማንም ሰው መኖሪያ ቤት፣ ትስስር፣እርሱን ወይም እርሷን የሚንከባከብ ሰው እንዳያጣ (እንዳታጣ)፣

ራሳቸውን በራሳቸው ሕይወት ውስጥ ብቻ ቆልፈው በራስ ወዳድነት መንፈስ የሚኖሩትን ሁሉ ልባቸውን ለፍቅር ይከፍቱ ዘንድ ፈወሳቸው። አሜን።

05 January 2022, 11:54

በቅርብ ጊዜ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የተደረገው ግንኙነት

ሁሉንም ያንብቡ >